መንግሥት የመኖሪያና የመሥሪያ ቤቶችን ግንባታ ምቹነት ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥቷል

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 25/2005(ዋኢማ)- መንግሥት በአገሪቱ እየተገነቡ ያሉትን የመኖሪያና የመሥሪያ ቤቶችን ግንባታ ምቹነት ለማረጋገጥ ትኩረት መስጠቱን የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ዴኤታ ገለጹ።

ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ኃይለ መስቀል ተፈራ ትናንት እንደተናገሩት መንግሥት እንደ ሌሎቹ የልማት ተቋማት ለሥራና ለኑሮ ምቹ አካባቢዎችን ለመፍጠር ትኩረት ሰጥቶ በመንቀሳቀስ ላይ ነው።ግንባታውንም በስፋት እያካሄደ ይገኛል።

ግንባታው የፕሮጀክቶቹን ባህሪና ጠቀሜታ አቅምንና ፍላጎት እንዲሁም ለአገር ገጽታ ግንባታ ትኩረት በሚሰጥ አቅጣጫ እየተከናወነ መሆኑንም አስረድተዋል። ''ለሕዝብ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ግንባታ ዘመናዊ፣በቴክኖሎጂ የተደራጁ፣ተደራሽና የግልጸኝነት መርሆ አካተው እንዲሰሩ የሚያስችሉ አሰራሮችን ተግባራዊ እያደረግን እንገኛለን''ብለዋል።

በአገሪቱ እየተመዘገበ ያለው ፈጣን ልማት በተለይ በመሠረተ ልማትና በማህበራዊ ልማት ረገድ ተጨማሪ ፍላጎት እየፈጠረ መምጣቱን ሚኒስትር ዴኤታው አመልክተው፣መልካም አስተዳደርን ለመገንባት በሚከናወነው የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደት ምቹ ዕይታን መፍጠር አንዱ ተግባር መሆኑንም ተናግረዋል።

በአገሪቱ በአሁኑ ወቅት የግንባታው ኢንዱስትሪ በፍጥነት እየተስፋፋ ቢሆንም፤ከግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች አንጻር ሲታይ ግን አሁንም ሰፊ የገበያ ጉድለት እንደሚታይ አቶ ኃይለመስቀል ገልጸዋል።

አገር በቀል የሥራ ተቋራጮች በዘርፉ ያላቸውን አቅም በማጎልበት፣በልማታዊ አቅጣጫ እየተመሩና እየተደገፉ በኢትዮጵያ ህዳሴ የሚኖራቸውን ተሳትፎ ማሳደግ እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።

መንግሥት የምህንድስናና የአርክቴክት ሙያ ተወዳዳሪ ሆኖ እንዲወጣ ለማድረግ ባለሙያዎችን በማፍራትና በሥራው ግንባር ቀደም ተሳታፊ በማድረግ እገዛ እንደሚያደርግላቸውም ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ከአምስት ሺህ በላይ በግንባታ የተሰማሩ ኩባንያዎች፣ከ300 በላይ የምህንድስናና የማማከር ድርጅቶችና 45ሺህ የምህንድስና ባለሙያዎች እንደሚገኙም ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል ሲል የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።