የአዲስ አበባና የኒው ዴልሂ ከተሞች ግንኙነት መመስረቻ የፕሮጀክት ስምምነት ተፈራረሙ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 25/2005(ዋኢማ)-  በአዲስ አበባና ኒውዴልሂ ከተሞች መካከል በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ የእህትማማች ግንኙነት የሚመሰርትበት የፕሮቶኮል ስምምነት መፈረሙን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ፡፡

በከንቲባ ኩማ ደመቅሳ የተመራ የልዑካን ቡድን በሕንድ ኒውዴልሂ የሥራ ጉብኝት አድርጓል፡፡ ስምምነቱን የተፈራራሙት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ኩማ ደመቅሳና የሰሜን ኒውደልሂ ከተማ ከንቲባ ሚስ ሚራ አግራዋ ናቸው፡፡ ስምምነነቱ በሁለቱ ከተሞች መካከል በጥቃቅንና አነስተኛ፣ በጤና፣ በፓርኮች ልማትና አካባቢ ጥበቃ ዘርፎች እንዲሁም በማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ያስችላል፡፡

ሚስ አግራዋ ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡ ከንቲባ ኩማ የኒውዴልሂ ከተማ ዋና አስተዳዳሪ ከሚስ ሸይላ ዲክሽትን ጋር አዲስ አበባ ለንግድ፣ ለኢንቨስትመንትና ለቱሪዝም አመቺነት በመግለጽ እንዲጎበኟት ጋብዘዋቸዋል፡፡

ዋና አስተዳዳሪዋ በበኩላቸው በሁለቱ ከተሞች መካከል ያለውን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚሰሩ ተናግረዋል። የከንቲባ ኩማ ግብዣም ተቀብለዋል፡፡
የቡድኑ በከተማዋ የሚገኘውን ብሔራዊ የጥቃቅንና አነስተኛ ማዕከል ከጎበኘ በኋላ ከማዕከሉ እንቅስቃሴ በመነሳት አዲስ አበባ ከሕንድ የዳበረ ልምድ ማግኘት እንደምትችል ከንቲባ ኩማ ደመቅሳ ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ልማት ቢሮ ከማዕከሉ ጋር በመገናኘት የልምድ ልውውጥ ማድረግ እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡ ቡድኑ በኒው ደልሂ ከተማ ስላለው የፓርኮች ልማት ከሥራ ኃላፊዎች ማብራሪያ አግኝቷል፡፡

ከኒው ዴልሂ 250 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘውን ታሪካዊ ታጅ መሃልንም ጎብኝቷል፡፡ በአዲስ አበባና በኒው ዴልሂ የእህትማማች ከተሞች ግንኙነት የሚመሰረተውን የፕሮቶኮል ስምምነት እንዲፈረም በሕንድ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከፍተኛ አድርጓል፡፡ ከከተማዋ ሥራ አስኪያጅና ከንቲባ ጽሀፈት ቤት፣ ከጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ልማትና ጤና ቢሮዎች የተውጣጣው የልዑካን ቡድን በከተማዋ የነበረውን የአራት ቀናት የሥራ ጉብኝት አጠናቆ መመለሱን የአስተዳደሩ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮን ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል፡፡