የኢኮኖሚ ዕድገቱን ለማስቀጠል ሰፊ ጥረት እየተደረገ ነው-ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 25/2005(ዋኢማ)- ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ያስመዘገበችውን ባለ ሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማስቀጠል በርካታ ተግባራት እያከናወነች መሆኗን የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር አስታወቁ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ትናንት ምላሽ በሰጡበት ወቅት እንዳስታወቁት ኢትዮጵያ በየዓመቱ 11 ነጥብ 4 በመቶ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማስመዝገብ ያስቻላትን ትክክለኛ መስመር በማጠናከርና የተለያዩ ተግባራት በማከናወን የኢኮኖሚ ዕድገቱን ቀጣይነት ታረጋግጣለች፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አዲስ ዘመን ጋዜጣን ዋቢ አድርጎ እንደገዘበው ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ያስመዘገበችውን ባለሁለት አሃዝ ዕድገት ሳይቀበለው የቆየው የዓለም ባንክ እውነታውን ተረድቶ መቀበሉን እንደ በጎ ጅምር ጠቅሰውታል፡፡

በኢትዮጵያ የግብርናው ዘርፍ ምርታማነት በየጊዜው እያደገ መምጣቱን ያወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዚህ ምስጢሩ አርሶ አደሮቹ ዘመናዊ አሰራርና ቴክኖሎጂን እንዲጠቀሙ በመደረጉ ነው ብለዋል፡፡ በኢንዱስትሪው ዘርፍ በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ የአገር ውስጥና የውጭ ባለኃብቶች ሥራቸውን በሚገባ እያከናወኑ እንደሚገኙ አመልክተዋል፡፡
ለዚህ አጋዥ የሚሆን የኢንዱስትሪ ዞን የማቋቋሙ ተግባር እየተከናወነ ነው፡፡ ኢትዮጵያ መሰረተ ልማትን በማስፋፋት ረገድ በአፍሪካ ትልቁን ስፍራ እንደያዘች ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ጠቁመው ይህን የማስፋፋት ተግባር በርካታ የኅብረተሰብ ክፍልን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በአገሪቱ የተለያዩ ግዙፍ ፕሮጄክቶች እየተከናወኑ ሲሆን ከነዚህ ውስጥም የታላቁ የሕዳሴ ግድብ በዋንኛነት በታቀደው መሰረት ሥራው እየተፋጠነ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡

በተመሳሳይም የባቡር ፕሮጄክት ተግባራዊ እየተደረገ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የስኳር ፐሮጄክቶች በዲዛይን ወቅት ባጋጠመ ችግር ምክንያት የአራትና የአምስት ወራት ጊዜ መዘግየት መስተዋሉን አመልክተዋል፡፡
ያም ሆኖ ፕሮጄክቱ ከታቀደው ጊዜ በላይ ብዙም ሳይቆይ ለማጠናቀቅ ሌት ተቀን እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የዋጋ ግሽበት ወደ 15 በመቶ እንደወረደ መረጃዎች ቢያመላክቱም ምግብ ነክ ምርቶች ላይ ትርጉም ያለው ቅናሽ አልታየም ተብሎ ለተነሳው ጥያቄ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽ የዋጋ ግሸበቱ ከወር ወር እየቀነሰ መምጣቱን ሁሉም ሊገነዘበው እንደሚገባው ገለጸዋል፡፡
መንግሥት የዋጋ ግሸበቱን ለማርገብ በርካታ እንቅስቃሴ ሲያደርግ እንደነበር አስታውሰው የተጀመረው እንቅስቃሴም ወደፊትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡ ከምግብ ሰብል አኳያ ሲታይ የጤፍ ምርት በአማካይ ወደ 10 በመቶ ዕድገት እያሳየ መምጣቱን የገለጹ ሲሆን ያም ሆኖ የተጠቃሚው ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ለእህል ምርት እጥረት ማጋጠም እንደ ምክንያት ሊነሳ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ የነዳጅ ዋጋ መጨመር ለዋጋ ግሽበቱ በፍጥነት አለመቀነስ አስተዋጸኦ ማድረጉን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ጠቁመው የዋጋ ግሸበቱን ለማርገብ መንግሥት እጁን አጣጥፎ እንዳልተቀመጠ በድጋሚ አረጋግጠዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከሶማሊያና ከኤርትራ በስተቀር ከጎረቤት አገሮች ጋር በንግድ ትስስር እየፈጠረች መሆኗን ገልጸዋል፡፡ በተለይ በመንገድ፣ በባቡር፣ በኤሌክትሪክ ኃይልና በቴሌኮም የአገለግሎት ዘርፎች ግንኙነት ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ስለመሆኑ አብራርተዋል፡፡
እንድ ኢዜአ ዘገባ በአገር ውስጥ የሕዝቡን የመኖሪያ ቤት እጥረት ለመፍታት በርታ ተግባራት እየተከናወኑ ሲሆን መኖሪ ቤቶቹም ከጊዜ ወደ ጊዜ ጥራታቸው እየጨመረ መመጣቱን አስታውቀዋል፡፡ በግንባታ ሂደት ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ማስገኘቱም የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ እንዲለወጥ ማስቻሉም ተናግረዋል፡፡ መሬትን በሕገ ወጥ መንገድ የያዙትን አስመልክቶ ለተነሳው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ በወረራ የተያዘ መሬት ይመለሳል፤ በሕገ ወጥ እንደተያዘ ሁሉ ወደ ሕጋዊነት የማምጣት ሥራ ይከናወናል ብለዋል፡፡