ክትባት የሚያሻው የሞተር ወረርሽኝ በጌዴኦ

  • PDF

ዮናስ

አንድ ጉዳይ ገጥሞኝ ወደ ጌዴኦ ዞን በመጓዝ ላይ እገኛለሁ፡፡ መነሻዬ አዲስ አበባ ሲሆን መድረሻዬ ደግሞ የጌዴኦ ዞንን ርዕሰ መዲና ዲላ ተሻግሬ ሁለተኛዋን ከተማ ይርጋጨፌንም ሰንጥቄ ሀገረማርያም መንገድ ላይ ካለችው የኮቾሬ ወረዳዋ  ሃማ ቀበሌ   ነው፡፡ 

እንደገመትኩትም መንገዴ የማናቸውንም ሰው ቀልብ በሚስብ ነገር  የተሞላው፡፡     ከዲላ መዳረሻ ጩኮ ከተማ ጀምሮ እስከ ፍስሃ ገነት ባለው መንገድ ላይ መልዓከ ሞት ለጉድ አፉን ከፍቶ እየተመላለሰ ነው፡፡ በመልዓከ ሞት የመሰልኩት የወረርሽኝ ጉዳይ   ሞተር ብስክሌት ነው፡፡ መልዓከ ሞትን በጌዴኦ አስገራሚ በሆነ ሁኔታ ተመልክቼዋለሁ። በዚያ ቅጽበት ደግሞ የሞተር ብስክሌት ትዝታዬ በህሊናዬ ላይ መጥቶ ስለነበር የመልዓ ሞቱ አስከፊነት ይበልጡኑ እየሰቀጠጠኝ መጣ፡፡

ጌዴኦና መልዓከ ሞትን እንደገና ወደኋላ፣ ወደ ሞተር ብስክሌት ትዝታዬ፣ የተመሰቃቀለ ስሜት ላይ እያለሁ መልዓከ ሞት አንዱን ሊጎርሰው ከአፉ ላይ አድርሶ መለሰው፡፡ እንደገና ወደኋላ ተመልሼ ነጎድኩ፡፡

ትዝታ አንድ

የስራውን ዓለም ሀ ብዬ የጀመርኩት በጉራጌ ዞን ገደባኖ ጉታዘር ወለኔ ወረዳ ምክር ቤት ነው፡፡ የዛሬ 9 ዓመት ግድም፡፡ ከወረዳዋ ዋና ከተማ መሃል ዓምባ በ4ቱም አቅጣጫዎች ወደሚገኙት 34 ቀበሌዎች የሚንቀሳቀሱ የሴክተር መስሪያ ቤት ሰራተኞች ሁሉ ሞተር ብስክሌት የግድ ይላቸዋል፡፡ በሶስት ምክንያት፡፡ የመጀመሪያው ምክንያት አብዛኞቹ ቀበሌዎች ከመሃል ዓምባ በአማካይ ወደ መቶ ሜትር ርቀት ላይ መገኘታቸው ጉዞው በእግር የማይቻል በመሆኑ ሲሆን ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ያሁኑን ባላውቅም በእኔ ጊዜ መኪና መግባት የማይቻልባቸው ቀበሌዎች ከ34ቱ ቀበሌዎች ቢያንስ ከ20 በላይ መሆናቸውና መኪና ይደርስባቸዋል የሚባሉትም ቢሆኑ ግማሽ መንገድ ድረስ ብቻ መሆኑ ነው፡፡

ሌላውና ሶስተኛው ምክንያት  መኪና እንኳ ሊያስገቡ የሚችሉ መንገዶች በህዝብ ተሳትፎ አንዳንድ ቀበሌዎች አካባቢ ቢሰራም ወረዳው ከ2 መኪና በላይ የሌለው መሆኑ ሞተር ብስክሌት ለሰራተኞቹ ባይፈልጉትም የግድና የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ ያም ሆኖ የተሟላ እና ሁሉም በፈለገው ሰዓትና ከስራው ፕሮግራም ጋር ተያይዞ ሞተር ብስክሌት ማግኘት መከራ ነው። ስለሆነም አንዱ ከአንዱ እየተዋሰና አንዱ በአንዱ ላይ እየተፈናጠጠ ስራውን ማከናወን የተለመደና የሰራተኛው የኑሮው አንድ አካል ነው፡፡
ሌላው ደግሞ የገደባኖ ጉታዘር ወለኔ ወረዳ ወጣ ገባ ተራራማና ለእግር ጎዞም ያልተመቸ መሆኑ ተጨምሮ ማናቸውም የሞተር ብስክሌት አሽከርካሪዎች ያልሰለጠኑና መንጃ ፈቃድ የሌላቸው መሆኑ፤ ሞተር ብስክሌቱ የመበላሸት ሁኔታ ላይ እንኳ ቢሆን ስለሰርቪስ አሰጣጥና ችግሮቹ የሚያውቅ አለመኖሩ በወረዳዋ ያለው የሞተር ብስክሌት መልዓከሞት በሌሎቹ ላይ የበላይነትን እንደያዘ ነበር ወረዳዋን የመተዋወቅ እድል የገጠመኝ፡፡

ስለሆነም ከላይ በጠቀስኳቸው ምክንያቶች እኔም አንዳንዴ እራሴ በማሽከርከር ምናልባትም መንገዱ ፈታኝ ወደሆነበት አካባቢ ደግሞ ተፈናጥጬ ስራዬን ማከናወን ግዴ ነበርና እኔና ሞተር ብስክሌትም ተዋወቅን፡፡ ታድያ በወረዳው በቆየሁባቸው ሁለት ዓመታት ውስጥ 3 ጊዜ አካባቢ የመገልበጥ አደጋ ቢያጋመኝም መልዓከ ሞት ጨርሶ ሳይውጠኝ ተርፌያለሁ፡፡ ታድያ አንዱ በተገለበጠና በተረፈ ቁጥር በወረዳው የሚወራው ወሬ መልዓከ ሞት ጨርሶ ስለሰለቀጣቸው ቀደምት ሰራተኞች ነው፡፡ እገሌ ከዚህ በፊት የሰው አጥር ላይ ተገልብጦ ሽቦው ተሰክቶበት ነው ህይወቱ ያለፈው፡፡ እገሌም ተገቢውን ጥንቃቄ ሳያደርግ (ሄልሜትና ጃኬት) ሳይለብስ በተደጋጋሚ ማሽከርከሩ ለነፋስ አጋለጠውና ሞት ቀደመው፡፡እገሌም ሞተር ተበጥሶ ከተራራው ወደ ዳንሼ ገደል ተወርውሮ ነው የሞተውና የመሳሰሉቱ ወሬዎች አይለመደኝም  እንድንል ቢያስገድደንም ያለሞተር ስራና ሰራተኛ የማይሆን በመሆኑ መልዓከሞተ የሚወስዳቸውን እያየን ከመጸለይና ይጠብቀኝ ከማለት በስተቀር ሌላ አማራጭ አልነበረንም፡፡

የሆነ ሆነና እኔና ገደባኖ ጉታዘር ወለኔ ወረዳ ከሁለት ዓመታት በኋላ በመለያየታችን የሞተር ብስክሌቱ መልዓከሞትም ተፋታኝ፡፡ ቢሆነም ግን ዛሬ ደግሞ በጌዴኦ ያንን መልዓከሞት በእጅጉ ልቆና ጨምሮ አየሁት፡፡

አጋጣሚ ሁለት

በቅርብ ነው፡፡ ቢበዛ ከ1 እስከ 2 ወር አካባቢ ፡፡ እዚሁ አዲስ አበባችን በሚገኘው የብሄረሰቦች መንገድ ወይም በተለምዶ ስሙ የጎተራው ማሳለጫ መንገድ ላይ የተፈጠረ ክስተት ነው፡፡ ከክስተቱ ፍፃሜ በኋላ የተሰማው ተባራሪ ወሬ እንደሚጠቁመው የመልዓከ ሞቱ ሰለባ የሆነው ግሰብ ወደባህር ማዶ የምትገኘው እህቱ ካፌ ልክፈትልህና   እራስህን ቻል ትለዋለች፡፡ ይሄ መልዓከሞት ደግሞ "በጭራሽ፤ የማይሆነውን፣ ከማሳለጫው ላይ ቆሜ እየጠበኩት፣ ካፌ ብሎ ነገር ፈጽሞ የማይሞከር ነው" ሲል ግለሰቡን ይወተውተዋል፡፡ ውትወታውም ውጤታማ ይሆንና ግለሰቡ "ካፌ አያስፈልገኝም በሞተር ብስክሌት ይለወጥልኝ" ሲል እህትን ይማፀናል፡፡ እህቲቱም ርቃው የሰነበተችውን ወንድሟን ያስደሰተች መስሏት የተባለችውን ማድረግ፡፡

ስለቱ የሰመረው መልዓከሞት ደግሞ ወዳጁን ከማሳለጫው ላይ ቆሞ መጠባበቅ፡፡ ከእለታት በአንደኛው ጦሰኛ ቀን ልጅዬ ጓደኛውን አፈናጦ አፉን ከፍቶ ወደሚጠብቀው ወዳጁ ማሽከርከር፡፡ ከዚያም ከላኛው መተላለፊያ ላይ የተፈናጠረው ሞተር ጓደኛውን እዚያው አስቀርቶ አሽከርካሪን ከታችኛው አስፓልት ጋር ማላተም፡፡ መልዓከሞትም ጉዳዩን ጨርሶ እብስ፡፡ አሁንም ይህን እያስታወስኩ በጌዴኦ ዞን ከሚገኘው መልዓከሞት ጋር የተፋጠጡትን እያስተዋልኩ ነው፡፡

ተረት 3

የየትኛው ሀገር እንደሆነ ባይታወቅም በጥቅሉ ፈረንጅ “ልጅህን ከጠላኸው ሞተር ብስክሌት ግዛና ስጠው” ሲል ይተርታል የሚለውም ብሂል በህልናዬ ውስጥ ተሰንቅሯል፡፡

ይህ ተረት አሁን ይሆን እንዴ ወደሚል ጥያቄ ወሰደኝ። በጌዴኦ አብዛኘው ሞተር ብስክሌት ዘዋሪ ልጅና ህፃን በመሆኑ፡፡ ስለሆነም በዚህ ተረትና ከላይ የጠቀስኳቸውን እያንሰላሰልኩኝ የጌዴኦን ትይንት በደንብ ባለሁበት እንደጋዜጠኛም ሆነ እንደዜጋ አንድ ነገር ማለትና የጌዴኦ ወጣትን ሊሰለቅጥ ያንዣበበውን መልዓከሞት ማጋለጥ እንዳለብኝ ተገነዘብኩ፡፡ ምክንያቱም ማድረግ የምችለው ይህንኑ ስለሆነ ብቻ፡፡(በነገራችሁ ላይ ይህ ጉዳይ የጌዴኦ ብቻ ሳይሆን የአብዛኞቹ የደቡብ ክልል አካባቢዎች ትእይንት መሆኑን የተረኩላቸው ሁሉ ነግረውኛል)

ከጩኮ እስከ ፍሥሃ ገነት

ጉዞዬ ወደ ጌዴኦ ዞን እንደመሆኑ እነ ዝዋይን ሻሸመኔን እና ሃዋሳን ማቋረጥ አለብኝ፡፡ መስመሩን በተደጋጋሚ የተጓዝኩበት እንደመሆኑ ከቆቃ ጀምሮ እነ መቂ፣ ዝዋይ፣ ሻሸመኔ፣ ሃዋሳ፣ ቱላ፣ ይርጋለም፣አፖስቶ፣ዲላ እስከ ይርጋ ጨፌ ድረስ የንግድ እንቅስቃሴው የቀለጠ ነው፡፡ የተለያዩ የሸቀጣሸቀጥ ንግዶች እንደተጠበቁ ሆነው በተለይ የግብርና ምርቶች ይበልጡኑ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ እጅጉን በላቀ ደረጃ ደግሞ የጫትና የቡና ንግድ የመስመሩ መለያዎች ናቸው፡፡

ጩኮ በሲዳማ ዞን ስር የምትገኝና ወደ ጌዴኦ ዞን መቃረቢያ ላይ የምትገኝ ከተማ ነች፡፡ በሃዋሳና ዙሪያዎቿ ሞተር ብስክሌትና ብስክሌት የተለመዱና የከተማዋ መገለጫዎች እንደሆኑ ብገነዘብም ከሞተር ብስክሌት ጋር የተጣባው ያ ቀደም ብዬ ያስተዋወቅኳችሁ መልዓከ ሞት በሃዋሳና በዙሪያዋ ብዙም ስጋት አይደለም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ሁሉም በሃዋሳ የሚገኙ የሞተር ብስክሌቶች ቀርቶ ብስክሌቶቹም ሳይቀር ታርጋ(የሰሌዳ ቁጥር) ያላቸውና አሽከርካሪዎቹም በስልጠና በቅተው ፍቃድ ያላቸው ሲሆኑ የሚያሽከረክሩትም ለራሳቸውና ለግላቸው አገልገሎት መሆኑ ነው፡፡

ሌላውና ሁለተኛው የመልዓከ ሞቱ ስጋት ያለመሆን ምክንያት የሃዋሳና ዙሪያዋ የትራንስፖርት አገልግሎት የተሸፈነው በባለሶስት እግር ተሽከርካሪዎች (ባጃጆች) ሲሆን የሃዋሳ ከተማ አስፓልት ጥራትና ሜዳማነት እንዲሁም የተሽከርካሪዎች ዝግታና የህግ አስከባሪዎች (ትራፊኮች) በተጠንቀቅ መሆን ስጋቱን ያወርደዋል፡፡

ከጩኮ ጀምሮ ያየሁት ሁኔታ ግን ከዚህ ቀደም ያላየሁትና አዲስ የሆነብኝ ከመሆኑም በላይ መስመሩ የጭነት አይሱዙዎች ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከሞተር ብስክሌቶቹ መብዛት ጋር የመልዓከ ሞቱን አስፈሪነት ዘግናኝ ያደርገዋል፡፡

ዕለተ አርብ ረፋድ ላይ ወደፍስሃ ገነት ባደረግሁት ጉዞ ግርታ ውስጥ ነበርኩና  ዝም ብዬ መመልከት ነበር ስራዬ፡፡ መንገዱ ሁሉ በሞተር ብስክሌቶች ተወሯል፡፡ አብዛኞቹ አሽከርካሪዎች ደግሞ ከአስራዎቹ እስከ 20 በሚገመት እድሜ ላይ የሚገኙ ሲሆን አንዳቸውንም ሄልሜትና ወፈር ያለ ንፋስ መከላከያ አጥልቀው ያልተመለከትኩኝ ሲሆን ይበልጡኑ የገረመኝ ደግሞ አንዳቸውም እንኳ የሰሌዳ ቁጥር (ታርጋ) የሌላቸው መሆኑ ነው፡፡

ከነዚሁ ሞተር ብስክሌቶችና አሸከርካሪዎቻቸው ጋር መኪናችን በጡሩንባ (ክላክስና) በዝግታ እየተናበበች ብትሄድም የበለጠ ቀልባችንን የሳበውና ትኩረታችንን ሁሉ የወሰደው ደግሞ በእያንዳንዱ ሞተር ብስክሌት ላይ ከአሸከርካሪው በተጨማሪ ሁለትና ሶስት ሰዎች ተፈናጠው መመልከታችን ነው፡፡ በዚህ ብቻ ቢያበቃ ጥሩ በነበረ፣   ከሰዎቹ ጋር እስከ 25 ኪሎ ግራም የሚደርስ እህልና ሌሎችም ሸቀጦች ተደርበው መጫናቸው ነው፡፡

በአስፓልት መንገድ ላይ ያላበቃው ትዕይንት ፍስሃገነትን ወደ ቀኝ ተገንጥዬ ወደ ገባሁበት የኮቸሬ የገጠር መንደርና መንገዶችም  ቀጥሏል፡፡
ቅዳሜ አመሻሹን ጉዳዬን ጨርሼ እየተመለስኩ ነው፡፡ አንድ ክስተት የበለጠውኑ ቀልባችንን ገፈፈው ።ከፊታችን አንድ አይሱዙ ይጓዛል፡፡  አንድ የሞተር ብስክሌት ደግሞ ብጣቂ ቲሸርት በለበሰ አሽከርካሪ  ሌሎች ሁለት ግለሰቦችን አፈናጣ ደርባን አለፈች፡፡ እኛን በደረበችበት ፍጥነት አይሱዙውን ለመደረብ ያደረገችው ጥረት ግን ከመልአከ ሞት ጋር ፊት ለፊት አፋጠጣት፡፡ አይሱዙው ከፊቱ የተቦረቦረ መንገድ ያጋጥመውና መሪውን ወደ ቀኝ ይዘውራል። ደርባ በማለፍ ላይ ያለችው ሞተርና ሞተርኛ ደግሞ ከአይሱዙው  ጎን ይገኛሉ፡፡

አይሱዙ ላይ የተጫነው መልአከሞት ወደቀኝ ሲመጣ ሞተሯና ሞተረኛው ከተሳፋሪዎቹ ጋር የሚገቡበት ጉድጓድ የሚያተርፋቸው መልአክ ከወዴት ይምጣ። ባወጣ ያውጣኝ ሞተረኛው በተመሳሳይ ወደ ቀኝ መሪውን በመዘወር አጠገቡ ያለው አጥር ላይ ተገልብጦ አፉን ከከፈተው መልአከ ሞት ለጥቂት አመለጠ፡፡

ጉዳዩ የሁለት ቀን ቀልባችንን ይዞት ነበርና ከጓደኞቼ ጋር ስለጉዳዩ በጣሙን አወራን።    እንደ አጋጣሚም ሊፍት የሰጠነው የኮቼሬ ወረዳ የካቢኔ አባል አብሮን ነበርና በጉዳዩ ላይ ብዙ ነገር ተወያየን፡፡ ቢያንስ ስንት ሞተር ብስክሌት በእነሱ ወረዳ ላይ ብቻ እንደሚኖር ላቀረብነው ጥያቄ ከ2 ሺህ የማያንስ የሚል ምላሽ አገኘን፡፡ ማነው ገዝቶ የሚሰጣቸው ለሚለው ጥያቄያችንም የቡና ንግድ ሲደራ ወላጆች ለልጆች መጀመሪያ የሚያደርጉት ሞተር ብስክሌት መግዛት ነው የሚል ሁለተኛ ምላሽ ተሰጠን፡፡ መንጃ ፍቃድ እንዳላቸው ላቀረብነው ጥያቄም በዲላና በይርጋ ጨፌ ከተሞች ላይ የሞተር ብስክሌት መሸጫ ቦታዎች እንጂ ማሰልጠኛ የለም የሚል ምላሽ በማሰለስ ተሰጠን፡፡

ትንሽ እንደተጓዝን እነኚህኑ መንጃ ፈቃድ የሌላቸውና የገደባኖ ጉታዘር ወለኔ ወረዳ ትዝታዬን ያመጡብኝ ያልሰለጠኑ አሽከርካሪዎችን ቆሞ የሚመለከት የትራፊክ ፖሊስ አገኘን፡፡ ወረድንና ምን እየተሆነ ነው ስንል ጥያቄ አቀረብን፡፡ ጉዳዩን በተመለከተ ብዙ እንደተባለና ብዙ የውይይት መድረኮች ከወላጆች ጋር  ተዘጋጅተው እንደነበር   አጫወተን፡፡ ምን መፍትሄ ተገኘ? ምንስ ስምምነት ተደረገ? ስንለው ወላጆች ጉዳዩን ሊመጣ ከሚችለው አደጋ ጋር ሳይሆን ያያያዙት ስራ ከመፍጠር ጋር ነው አለን፡፡ ስራ ፈጠራ የሚለውን መርህ ያለአግባብና ህገወጥ በሆነ መንገድ በመጠቀም ብቻ አያበቁም ያለን ህግ አስከባሪ አብዛኛው ሰው የሞተር ብስክሌት ባለቤት ከመሆኑ ጋር በተያያዘና እኛም የዚሁ ህብረተሰብ አካል ከመሆናችን ጋር በተገናኘ ልንከሳቸው ስንሞክር የእገሌ ልጅ ልጄ ሰርቶ እንዳይበላ ምቀኛ ሆነበት የሚሉ ማህበራዊ ጉዳቶችን ያደርሱብናል የሚል ምላሽ ሰጠን፡፡

በእርግጥም ጉዳዩ በህግ አስከባሪውም ዘንድ አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል እኛም እናምናለን፡፡ ግን እስከመቼ? እኔ ጥናት አላደረኩም እንጂ  የጌዴኦ ሆስፒታሎችና ጤና ተቋማቶች መዝገብና አልጋ ቢፈትሹ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡ አንድ ሁለት የአካባቢውን አሳዛኝ አጋጣሚዎች ከሰማሁት ላካፈላችው፦

ደግነቱ ዋናው ጎዳናና አስፖልት ላይ አለመሆኑ በጀ እንጂ ክስተቱ አስደንጋጭ ነው፡፡ አንዲት እናት ልጇን እንዳዘለች ሞተር ላይ ትፈናጠጣለች ገና ከመቀመጧ መሆኑም በጃት መሰለኝ ጉዞዋን ጨርሳ ስትወርድ ልጇ ጀርባዋ ላይ የለም። ከኋላ ሾልኮ ወድቋል፡፡ የደነገጠው ሞተረኛም በፍጥነት እናቲቱን ይዞ ወደኋላ ሲከንፍ መነሻው የነበረው ቦታ ላይ ልጅ በጀርባው ተንገዋሎ ከልጅ አምላኩ ጋር ተገኘ፡፡

ሁለተኛው ገጠመኝ ግን የከፋ ነው። ሁለት ተሳፋሪ በጫነ ሞተር ብስክሌት ላይ ልጇን አዝላ ከመሀል ተፈናጣ የነበረች እናት ስትወርድ ልጁ በመታፈን ይሁን በነፋስ ለጊዜው ባልታወቀ ምክንያት ጀርባዋ ላይ የተገኘው ይህቺን አለም ተሰናብቶ ነው፡፡

ታዲያ የጌዴኦ ዞን ምን ይጠብቃል? በርግጥ ከዞኑ በላይ ጉዳዩ የህብረተሰቡ ይመስለኛል፡፡ በሁለቱም በኩል መሆን ያለበት ካልሆነ በጌዴኦ ያንዣንበበው መልአከሞት እና ወረርሽኝ ክትባት ካላገኘ እንደፈረንጆቹ ተረት ሳይጠሏቸው በገዙላቸው የሞተር ብስክሌት ወላጆች ልጅ አልባ ፣ ዞኑም አምራች ሃይል የሆኑ ዜጎቹን በአሰቃቂ ሁኔታ የሚያጣበት ሁኔታ እሩቅ እንደማይሆን መገንዘብ ይቻላል፡፡ እኔ ለመነሻ ይህቺን ብያለሁ። ጉዳዩን በሚገባ የምታውቁትና ምናልባትም በአጠገቡ መሆናችሁ ሊከልላችሁ ይችላልና ቆም ብላችሁ በማጤን የየራሳችሁን ሃሳብ ሰንዝሩበት፣ ሞግቱበት፤ ከብዙ ሙግትና ሃሳብ መወርወር በኋላም ቢያንስ አደጋውን ጨርሶ የሚያቆም እንኳ ባይሆን ሊቀንስ የሚችል መፍትሄ ሊመጣ ይችላል፡