የጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች በመለስ ራዕይ የእቅዱን ስኬት እያመላከቱ ነው፡፡

  • PDF

ዮናስ

የጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት በሃገራችን ያለውን የሥራ አጥነት ችግር በመቅረፍ ሠፊ መሠረት ያለው ልማታዊ ባለሃብት የሚያፈራ ለቀጣይ የኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ግንባታ መሠረት የሚጥል፣ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዳችን ዋነኛ መዘውር በመሆን በከተሞች ልማታዊ ፖለቲካል ኢኮኖሚን በመገንባት ፈጣን እድገትን የሚያረጋገጥና ህዝብንም በላቀ ደረጃ የልማቱ ተጠቃሚ የሚያደርግ ዘርፍ በመሆኑ መንግስት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ የሚሠራበትና ልዩ ድጋፍ የሚያደርግለት ዘርፍ መሆኑን ታላቁ መሪያችን የነበሩት መለስ ዜናዊ በምርጫ 2002 አካባቢ በተደጋጋሚ ሲናገሩ አሠላለፋቸው ፀረ-ልማታዊ የነበሩት ወገኖችና የዜሮ ድምር ፖለቲካው መንደር ስብስቦች በጉዳዩ ላይ ብዙ የተሣለቁበትና ለጥቃቅን ተዋናዮች “ጥቃቅን ካድሬዎች” የሚል ታፔላም ሲለጥፉባቸው እንደነበር አይዘነጋም፡፡

ታላቁ መሪም ራዕያቸው ከድህነት መውጣና ድህነትን ማሸነፍ ነበርና ዘርፉ ከመካከለኛና ከረጅም ጊዜ አንፃር ሃገሪቱ ባላት ውስን ካፒታልና ቴክኖሎጂ በመጀመር ደረጃ በደረጃ የካፒታልና የቴክኖሎጂ አቅምን በማጠናከር በማያቋርጥ ፈጣን የዕድገት ዑደት ውስጥ በመገንባት ከፍተኛ ሚና መጫወት እንደሚችል ከብዙ ሃገሮች ተሞክሮ እና ከሃገራችንም ነባራዊ ሁኔታ በሚገባ የተረዱት ታላቁ መሪ በ2003 ዓ.ም ዘርፉን በተመለከተ አዲስ ስትራቴጂ በመንደፍ መሠረተ ሠፊ የሆነ ንቅናቄ እንዲፈጠር እና  ፀረ ልማታውያኑ ያሉት ሳይሆን ዘርፉ ዛሬ የደረሠበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ ሲዘከር የሚኖር አሻራቸውን አትመው አልፈዋል፡፡

ታላቁ መሪ ድህነትን ለማሸነፍ ያላቸውን ራዕይ ለማሣካት የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ወሣኝ ሚና እንደሚጫወቱ ያመኑት በተለያዩ እና ተጨባጭ በሆኑ አለም አቀፋዊና ሃገራዊ ምክንያቶች እንጂ መርዶ ነጋሪ የሆኑት ፀረ ልማታውያኑ እና ልሣኖቻቸው የነበሩት እነፍትህ አሁን ደግሞ አዲስ ታይምስ እንደሚሉት አይደለም፡፡ የነዚህን ፀረ ልማት ሃይሎች እና ልሳኖቻቸው መነሻ ምክንያት ወደኋላ የምመለስበት ይሆንና የታላቁን መሪ ተጨባጭና ምክንያታዊ የሆኑ ሁለት መነሻዎች መጀመሪያ ላስቀድም፡፡
ሁለቱም የታላቁ መሪ መነሻዎች ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎችን የተመለከቱ ሲሆን ሁለት መነሻ ነበራቸው ያልኩበት ምክንያት ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎቹን በዓለም አቀፍና በሃገራዊ ገጽታቸው ፈርጀን ብንመለከታቸው የበለጠ ግልጽ ይሆንልናል በሚል እሳቤ ነው፡፡

ከሁለት መቶ ዓመታት በፊት በእንግሊዝና በሌሎች የአውሮፓ አገሮች የተካሄደው የኢንዱስትሪ አብዮት  የዓለምን ክፍለ ኢኮኖሚ ባለቤትነትና  ይዞታ በሦስት ደረጃ (በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በንግድ)  ከፍሎት እንደነበር የታሪክ ሠነዶች ያመለክታሉ፡፡
የእነዚህ ክፍለ ኢኮኖሚ ባለቤትነትም እንደየሥርዓተ ማህበሩ የሚለያዩ ሲሆኑ እነዚህም እና ዋነኛ ተዋናዮቹ የመሬት ባለቤትና ገበሬው/አራሹ፣ የኢንዱስትሪው ባለቤትና ወዛደሩ/ላብአደሩ እንዲሁም ነጋዴውና ሸማቹ ናቸው፡፡

በዚህ የሥራ ክፍፍልና የሃብት ባለቤትነት አዙሪት በሚፈጠር ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቅራኔዎች የተለያዩ ግጭቶች በዓለም ላይ ተከስተው አልፈዋል፡፡
አሁንም ስላለመቀጠላቸው ሳይሆን ስለመቀጠላቸው የሚያወሱ በርካታ የፖለቲካና የምጣኔ ሃብታዊ ተመራማሪዎች ያወጋሉ፡፡
የካፒታሊዝምና የሶሻሊዝም አይዶሎጂዎች በኢኮኖሚ የተለያዩ ህብረተሰቦችን እንወክላለን ብለው በመነሣት የለኮሱት እሣት እና የተፈጠሩትን ቀውሶች እዚህ ጋር ማስታወሱ ተገቢ ይሆናል፡፡ (ቻይና፣ ሩሢያ፣ ፈረንሣይና ምስራቅ አውሮፓን) እነዚህ ሁሉ ፖለቲካዊ ሽፋን ይኑራቸው እንጂ መንስኤዎቻቸው ኢኮኖሚያዊ መሆኑን ተመራማሪዎች በተጨባጭ ያረጋገጡትና በታሪክ  መዝገባቸው ከትበው ያኖሩት ጉዳይ ነው፡፡

እንዲሁም የኢኮኖሚ ግሎባላይዜሽንና የሌበራል ኢኮኖሚ ጽንሠ ሃሳብ እያስከተለ ያለውን ውጥረት እና መራራ ውጤቱንም ያልቀመሠ አዳጊና በማደግ ላይ ያለ አገር አለ ብሎ  መናገር ይከብዳል፡፡ በተለይም የአዳጊ ሃገሮች አዳጊ ኢንዱስትሪዎች (Infant Industries) አምርተው ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያደርጉት ውድድር ቀላል አይደለም፡፡ እነዚህ ሁሉ ግጭቶችና የተለያዩ የኢኮኖሚ አስተሣሠቦች አሁንም ለአለም ህዝቦች መፍትሄ ሆነው አልተገኙም፡፡

ስለሆነም ነው ይህ የኢኮኖሚ ይዘትና ሥርዓት አሁንም የግጭት መንስኤ ሊሆን የሚችለው የሰው ልጅ በተለይ ድሃው ህዝብ እራሱን ለማኖር በሚያደርገው ጥረትና ባለሃብቱ ደግሞ የበለጠ ለማደግ በሚያደርገው ጥረት መካከል የሚነሣ ቅራኔ ሊሆን ስለሚችል ነው፡፡ በዚህም ላይ በአለማችን ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል አለመኖሩ ደግሞ ብዙ ማሣያዎች አሉት፡፡ በአናቱም ሐብታም አገሮች ሸቀጦቻቸውን በየትኛውም የዓለም ክፍል መሸጥ እንዲችሉ ግሎባላይዜሽን ይፈቅዳል፡፡
በዚህ መሠረት አገራዊ የኢንዱስትሪዎችና የእደ ጥበብ ውጤቶች ምርት ከነዚህ በቴክኖሎጂ ካደጉ አገሮች ምርቶች ጋር በራሣቸው ገበያና በዓለም ገበያ ላይ እንዴት ተወዳዳሪ መሆን እንደሚችሉ ያለውን ውጣውረድና ትግል መገመት አያዳግትም፡፡ ይህ ነው እንግዲህ አንደኛው በታላቁ መሪ ራዕይ በአዲስ ስትራቴጂና ለሁለገብ አገራዊ ጠቀሜታ የተደራጀው የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት መነሻ፡፡

ወደሁለተኛው የታላቁ መሪ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት መነሻ ስንመጣ ያው እንደቀደመው ሁሉ ኢኮኖሚያዊ ቢሆንም ፈርጁ ግን ሃገራዊ ነው፡፡
በሃገራችን ባለፉት ተከታታይ ዓመታት የታየው ባለሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ እድገት ድርሻ የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ 41.56 በመቶ፣ 45.57 በመቶ የአገልግሎት ዘርፉ ድርሻ ሲሆን 12.87 በመቶ የሆነውን ድርሻ የሚይዘው ደግሞ የኢንዱስትሪው ክፍለ ኢኮኖሚ እንደሆነ በታላቁ መሪና በህዳሴው መሃንዲስ መሪነት የተቀመረው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ሠነድ የሚያመለክት ሲሆን ዘግይቶም ቢሆን ይህንኑ ሃቅ የዓለም ባንክ ከሠሞኑ ባወጣው ሪፖርት አረጋግጧል፡፡

የአንድ አገር የእድገት ደረጃ የሚለካው የኢንዱስትሪው ክፍለ ኢኮኖሚ ለአገራዊ ኢኮኖሚ ዕደገት ካለው ድርሻ አንፃር እንደሆነ ይታወቃል፡፡
እንደ ኢትዮጵያ ባሉት አዳጊ አገሮች ደግሞ አብዛኛው የኢንዱስትሪ ዘርፍ በጥቃቅን፣ አንስተኛና በመካከለኛ የእድገት ደረጃ  የሚገኙ ሲሆኑ ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች በጣት የሚቆጠሩ ናቸው፡፡
በዚህም መነሻ ለመካከለኛና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች መሠረት የሚሆኑት የጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች  ልማት ትኩረት ተሠጥቶ በትክክለኛው  ልማታዊ አስተሣሠብ እንዲመራ በታላቁ መሪ ፊት አውራሪነት ስትራቴጂ ተቀርጾለት አሁን ያለበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡

የዘርፉ ልማት የሥራ አጥነትና የድህነትን ችግሮች መቅረፊያ ዋና መሣሪያ ከመሆኑም በላይ በሃገሪቱ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል እንዲኖር የሚያስችል እንደሆነ በማመንና ይህንኑ ለማረጋገጥ የዘርፉ ልማት ለዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ መሣካት የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ልማቱን የሚያፋጥኑ የድጋፍ ማዕቀፎችን ለመተግበር የሚያስችል አቅምና ግንዛቤ መፈጠሩ አሁን ያለውን እና የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅዱን ስኬት የሚያመላክቱ ውጤቶችን አስገኝቷል፡፡

የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን ልማት በሃገራችን ተግባራዊ ማድረግ ያስፈለገበትን መነሻዎች በዚህ መልኩ ከተመለከትን ታዲያ ለምንድነው ለዘርፉ የተለየ ትርጉም መስጠት ያስፈለገው? የሚለውን ጥያቄ መመለስ ቀላል ይሆናል፡፡ ይኸውም ዘርፉ ካለው ኢኮኖሚያ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጠቀሜታዎች አኳያ እና ከዜሮ ድምሩ ስብስብ አኳ ስንፈትሸው የሚገኘው ውጤት ይሆናል፡፡
ከፍተሻችን እና ከንጽጽራችን በፊት ግን በርግጥ ጥቃቅን እና አነስተኛ ማለት እንደስሙ ትንንሽ ማለት ነው?  የአዲስ ታይምሶቹ አላጋጮችና አሽሟጣጮች ተመስገንና አቤ ቶክቸው እንደሠየሙት ጥቃቅን ካድሬዎች ማለትስ ነው? ወይስ ሃገራዊ ፋይዳ ያለው ትርጓሜ? የሚለውን እንመልከት፡፡

የጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች በተለያዩ አገሮች እንደየኢኮኒሚ እድገታቸው የተለያዩ ትርጉሞች ያሉት ሲሆን በሚያንቀሳቅሱት የካፒታል መጠን፣ በዓመታዊ ሽያጫቸው፣ በቴክኖሎጂ ደረጃቸው፣ በሚሠማሩበት ንዑስ ዘርፍ እንደሚመዘኑና ትርጓሜ እንደሚሠጣቸው የምጣኔ ሃብታዊ ትርክቶች ያረጋግጣሉ፡፡
በዚሁ መሠረት እና ዓለም አቀፋዊ መነሻ ጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የነጠላና የወል ምጣኔ ሃብታዊ ትርጓሜ ተሠጥቷቸው በሥራ ላይ ውለዋል፡፡
በኢንዱስትሪ ዘርፍ (ማኑፋክቸሪንግ፣ ኮንስትራክሽን፣ ማእድን) የኢንተርፕራይዙን ባለቤትና የቤተሠብ አባላት ጨምሮ እስከ አምስት ሠዎች ቀጥሮ የሚያሠራ ወይም የጠቅላላ ንብረታቸው መጠን በዋጋ ከብር 100 ሺህ ያልበለጠ እና፤ በአገልግሎት ዘርፍ (ችርቻሮና ትራንስፖርት፣  ሆቴልና ቱሪዝም፣ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሊጂ እና የጥገና አገልግሎት) የኢንተርፕራይዙን ባለቤትና የቤተሠቡን አባላት ጨምሮ እስከ አምስት ሠዎች ቀጥሮ የሚያሠራ ወይም የጠቅላላ ንብረታቸው በዋጋ ከብር 50 ሺህ ያልበለጠ የሚለው ትርጓሜ የጥቃቅን ዘርፉን ብቻ የሚወክል እንደሆነ የሚጠቅሠው የጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት  ኤጀንሲ ድረ-ገጽ በኢንዱስትሪ ዘርፉ ከ6-30 ሰዎች ቀጥሮ የሚያሠራ ወይም የጠቅላላ ንብረታቸው መጠን በዋጋ ከብር አንድ መቶ ሺህ አንድ እስከ 1.5 ሚሊዮን ያልበለጠ እና በአገልግት ዘርፍ ከ6-30 ሰዎች በተመሣሣይ ቀጥሮ የሚያሠራና የጠቅላላ ንብረታቸው መጠን በዋጋ ከሃምሣ ሺህ አንድ እስከ ግማሽ ሚሊዮን ያልበለጠ የሚለውን ትርጓሜ ደግሞ የአነስተኛ ኢንተርፕራይዞች እንደሆነ ድረ ገጹ በግልጽ አስቀምጧል፡፡

በዚሁ መሠረት እነ ተሜ እና አቤ እንደሚሉት ለዘርፉና ለዘርፉ ተዋናዮች ድጋፍ እየተደረገ ያለው “ጥቃቅን ካድሬዎች” ስለሆኑ ሳይሆን ከላይ ከተሠጡት ትርጓሜዎች በመነሣት ነው፡፡ ይኸውም ኢንተርፕራይዞቹ እንደየደራጃቸው የተለያዩ ችግሮች ስላሉባቸው የካፒታል፣ የሠለጠነ የሰው ኃይል፣ የቴክኖሎጂና የመወዳደር አቅም ካላቸው ትልልቅ ኢንተርፕራይዞች ጋር ተለይተው በሚደረግላቸው ድጋፍ እንዲያድጉ፣ እንዲስፋፉ፣ በገበያ ውስጥ ተወዳዳሪ ሆነው እንዲቀጥሉ ስላስፈለገ ነው፡፡

ይህ ያስፈለገበትም ደግሞ የራሱና ከዚሁ ቀደም ብዬ ከጠቀስኩት እና ከታላቁ መሪ አገራዊ ኢኮኖሚን ከተመለከተው መነሻ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ይኸውም በሚደረግላቸው ድጋፍ ሠራተኞቻቸውን ይዘው ሥራ ውስጥ እንዲቆዩ፣ የሥራ ዕድል በብዛት እንዲፈጥሩ፣ ካፒታል እንዲያፈሩና ወደሚቀጥለው መካከለኛና ከፍተኛ/ ደረጃ ኢንዲሸጋገሩ፣ የውጭ ምንዛሬ እንዲያስገኙ ወይም ለዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዳችን ወሣኝ የሆኑትንና በውጭ ምንዛሬ የሚገቡትን እቃዎች በአገር ውስጥ እንዲያመርቱ በዚህም ለመካከለኛና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች መሠረት እንዲሆኑ፣ ልማታዊ ባለሃብት ሆነው በኢኮኖሚው እድገት ውስጥ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ፣ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል እንዲያሠፍኑ፣ የኪራይ ሰብሣቢነት አመለካከትንና ድርጊትን እንዲያከስሙ እና እንዲዋጉ፣ ለኢንዱስትሪው ክፍለ ኢኮኖሚ የሰለጠነ የሰው ኃይል ምንጭ እንዲሆኑና ከግብርና መር ኢኮኖሚ ልማት ወደ ኢንዱስትሪ መር የኢኮኖሚ ልማት ለመሸጋገር የበኩላቸውን እና  የላቀ ድርሻቸውን እንዲወጡ ለማስቻል እንጂ እነ አዲስ ታይምስ ለኒዮ ሊበራሉ ሃይል አቃጣሪ እንደሆኑት ሁሉ ለኢህአዴግ እንዲያቃጥሩ ተፈልጎ አይደለም፡፡

አሁንም በግልጽ መቀመጥ ያለበትና ግንዛቤ ሊያዝበት የሚገባው ጉዳይ የጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጠቀሜታቸውን ሲሆን እግረ መንገድም ከፖለቲካዊ ጠቀሜታዎቻቸው በመነሣት የፀረ ልማታዊ ስብስቡን መንደር መገንዘብ ያስችለናል፡፡
የኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎቻቸውን ከመለስ ራዕይ፣ ከትራንስፎርሜሽን እቅዱና ስኬቱን ከማመላከታቸው ጋር አያይዘን ስንመለከት የሃገር ውስጥ ጥሬ ዕቃና የሠው ኃይልን በስፋት እየተጠቀሙ ሲሆን በተለይ ለግብርና ምርት ዋጋ የገበያ መሠረት መሆናቸውን በማረጋገጥ ላይ ይገኛሉ፡፡ የአገር ውስጥ የተፈጥሮ ሃብትን (መሬት፣ ውሃ፣ እንጨት፣ ማዕድናት ወዘተ) ጥቅም ላይ እየዋሉ ሲሆን ለብዙ ሰዎች የሥራ ዕድልና ገቢን በመፍጠር ላይ ናቸው፡፡

ምርትና አገልግሎቶችን ከዳር ዳር በማድረስ የአገር ውስጥ ገበያን በማረጋጋት ላይ የሚገኙት እነዚህ ኢንተርፕራይዞች ምርታቸውን ኤክስፖርት በማድረግ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ደረጃም ላይ ደርሠዋል፡፡ በዚሁ ላይ ከውጭ የሚገቡ ሸቀጦችን እና ምርቶችን በማምረት ለእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዳችን ስኬት አስፈላጊ የሆነውን የውጭ ምንዛሬ በማዳን ላይ ናቸው፡፡
የቁጠባን ባህል በማዳበር ወደሚቀጥለው ደረጃ እራሣቸውን በማሸጋገር ብዙዎቹ ልማታዊ ባለሃብት እየሆኑ ሲሆን ለመካከለኛና ለከፍተኛ ኢንዱስትሪዎችም መሠረት በመሆን ፈጠራንና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማስፋፋት ላይ ይገኛሉ፤ (ከመከላከያ የብረታ ብረት እና ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን፣ ከግዙፍ የሥኳር ፋብሪካ ፕሮጀክቶች እና ከቤቶች ልማት ጋር ያላቸውን ትሥሥርና የመሠረትነት ውጤት እዚህ ጋር ያስታውሷል)
በቅርቡ በዓለም ባንክ ይፋ እንደተደረገው ሪፖርትም የአገሪቱን አጠቃላይ ገቢ (GDP) ድርሻ ከፍ ከማድረጋቸውም በላይ በሃገሪቱ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል እንዲኖር የተጠበቀባቸውን ሚና በአግባቡ በመወጣት ላይ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ እንግዲህ ከብዙ በጥቂቱ እና ዋና ዋና የተባሉት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎቻቸው ሲሆኑ ወደማህበራዊ ጠቀሜታዎቻቸው ስንመጣ፡-
የጥቃቅን እና አነስተኛ ተቋማት ሰውን በማቀራረብ አብሮ የመስራት ባህል እንዲዳብር ከማድረጋቸውም ሌላ የተደራጀና መብትና ግዴታውን የሚያውቅ ማህበረሠብ ከመፍጠር አኳያ ሚናቸው ከፍተኛ መሆኑ በተጨባጭ እየታየ ነው፡፡

በዚህ ረገድ ከፍኛ ሚና እየተጫወቱ መሆኑ እንደ ሃገር ፋይዳውን የሚያጎላና የሚያስደስት ነው፡፡ ምክንያቱም በዚህ መልኩ የተደራጀ ህብረተሠብ ደግሞ ማህበራዊ ተሣትፎውና ለሰላም ያለው ፍላጎት፣ ሠርቶ የመኖር ሠላማዊ እንቅስቃሴ ፍላጎት ከፍኛ በመሆኑ ነው፡፡ ብጥብጥን፣ ወንጀልን፣ ሌብነትን፣ ኪራይ ሠብሣቢነትንና ሙስናን ይከላከላል፡፡ በህግና በሕጋዊ ሥርዓት ብቻ መኖርን ያዳብራል (ይህ ደግሞ ለእነ ተመስገን እና የአዲስ ታይምስ ስብስቦች ራስ ምታት በመሆኑ የ”ጥቃቅን ካድሬነት” ታፔላ መለጠፋቸው ቢያሳዝን እንጂ አይገርምም)
የእነዚህ ኢንተርፕራይዞች ልማት ማህበራዊ ጠቀሜታ በዚህ ብቻ አያበቃም፡፡ የህብረተሰቡ የመማር፣ ጤናውን የመጠበቅ የተሻለ የመኖሪያ ቤትና አካባቢ ፍላጎት ይጨምራል፣ ያድጋል በዚህም ለማህበራዊ አገልግሎቶች የሚከፍለውም የገቢ ምንጭ ይኖረዋል፡፡

ለአካባቢ ጥበቃና ለንጽህና ያለው አመለካከት ይዳብራል፣ አካባቢውን ያፀዳል፣ ያለማል፣ ፀጥታውን ይቆጣጠራል፡፡
ለትምህርት የደረሡ ህፃናት ሁሉ ወደ ትምህርት ቤት ይሄዳሉ፣  ህፃናት የቤተሠቦቻቸውን ገቢ ለመደጎም አይባክኑም፣ ቤት አልባነት፣ ጎዳና ተዳዳሪነት፣ ዝሙት፣ ወንጀል፣ የአካባቢ ብክለት፣ ተላላፊ በሽታዎች/ ኤድስን ጨምሮ ይወገዳሉ፡፡ የእድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅዱ ስኬት አመላካች የማዕዘን ድንጋዮችና የምዕተ ዓመቱ የልማት ግቦች ስኬት ጠቋሚዎች ከነዚህስ በላይ ከወዴት ይገኛል?

የዜሮ ድምር ስብስቡ ሽሙጥና ታፔላ መነሻ የሆነውና የሚልቀው ደግሞ አሽሙረኞቹ ካላቸው የአቋራጭ መንገድ ሥልጣን ፍለጋና የትርምስ አባዜ ጋር የሚጋጨው የኢንተርፕራይዞቹ ፖለቲካዊ ፋይዳና በተጨባጭ ተግባራዊ እየሆነ ያለው ፖለቲካዊ ጠቀሜታዎቻቸው ናቸው፡፡ ይኸውም የራሱ ገቢ ያለውና የተደራጀ ህብረተሰብ መብትና ግዴታውን ከማወቅም አልፎ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሂደት ውስጥ የነቃ ተሣትፎ የሚኖረው ከመሆኑና ይኸውም በተጨባጭ እየታየ ያለ እና የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱን ስኬት ከማመላከቱ ጋር የተያያዘ መሆኑ ነው፡፡
እነዚህ ኢንተርፕራይዞች በታላቁ መሪ ትልምና ራዕይ መደራጀት ሃይል መሆኑን ተገንዝበው የተለያዩ ፀረ ልማት እና ፀረ ዴሞክራሲያዊ አመለካከቶችን በመገምገም  እየጣሉ መሆናቸው ለዜሮ ድምሩ ስብስባ  መንደርተኞች እንቅልፍ የሚነሣ ጉዳይ ሆኗል፡፡

በመለስ ራዕይ ተግባራዊ እየሆነ ያለውና የጥቃቅን እና አነሥተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት በሥርዓቱ ውስጥ መልካም አስተዳደር እንዲሠፍን እያደረገ ነው፡፡  ተዋናዮቹም መሪዎቻቸውን ለመምረጥም ሆነ ለመመረጥ የበኩላቸውን ድርሻ እየተወጡ ሲሆን ፀረ ዴሞክራሲያዊ አካሄዶችን በመቆጣጠር ፖለቲካዊ አመራርን መስጠትም መቀበልም ችለዋል፡፡ የአነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች መንደር የግርግርና ትርምስ መነኻሪያ ሳይሆን ሚዲያዎችን የሚከታተል፣ የሚያነብ፣ በአካባቢ አስተዳደራዊ ጉዳዮች የሚሣተፍ፣ ስለውጪው ዓለም ልዩነት፣ አንድነትና ግንኙነት የተረዳ፣ ሃሣቡን የሚያካፍል፣ አዎንታዊ አመለካከቶችን Positive Attitude) በሚያዳብር ህብረተሰብ የተሞላ መንደር ነው፡፡ ይህ ደግሞ የመለስ ራዕይና በመለስ ራዕይ የተገኘ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱን የስኬት ጎዳና የሚያመላክት ድል ነው፡፡