የሰብአዊ መብት ጥሰትን የሚያበረታታ ሽልማት

  • PDF

ኢብሳ ነመራ

“በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ጥሰት ይፈፀማል” የሚል ልቦለድ በመድረስ የሚታወቀው ሂዩማን ራይትስ ዎች የተባለው የሰብአዊ መብት ተሟጋች ነኝ ባዩ ድርጅት ሰሞኑን ለአራት ኢትዮጵያዊያን “ጋዜጠኞች” ሽልማት መስጠቱን ነግሮናል፡፡ ሽልማቱ ሃሳብን ለመግለፅ አርበኝነት የተሰጠ መሆኑንም እንዲሁ ነግሮናል፡፡

ተሸላሚዎቹ “ጋዜጠኞች” በሽብርተኝነት ወንጀል ጥፋተኛ ተብለው ቅጣት የተወሰነባቸው እስክንድር ነጋ፣ ውብሸተ ታዬ፣ ርዕዮት ዓለሙና በሌለበት ተከሶ ቅጣት የተላለፈበት መስፍን ነጋሽ ናቸው፡፡

እነዚህን አራት ግለሰቦች ኢትዮጵያዊያን ያውቋቸዋል፡፡ አብዛኛው ኢትዮጰያዊ ያሚያውቃቸው ግን በጋዜጠኝነታቸው ሳይሆን በሽብረተኝነት ወንጀል ተጠርጥረው ከተከሰሱና በዚሁ መጥፎ ተግባራቸው ቅጣት ከተወሰነባቸው በኋላ ነው፡፡

ሂዩማን ራይትስ ዎች ለአራቱ ሰዎች ሽልማቱን ሊሰጥ የቻለበትን ምክንያት ሲገልፅ፣ “በኢትዮጰያ ሃሳብን የመግለፅ ነጻነት እንዲጎለብት ላደረጉት አስተዋፅኦ ነው፤” ብሏል፡፡ አያይዞም “እነዚህ የታሰሩና የተሰደዱ ጋዜጠኞች ያላቸውን ቁረጠኝነትና በአሁኒቷ ኢትዮጵያ ያለውን አስከፊ ሁኔታ ያሳያሉ፤ የገጠማቸው አስከፊ ሁኔታ የመናገር መብት ባልተፈቀደበት አገር በነጻነት መናገር የሚያስከፍለውን ዋጋም ያሳያል፤” ብሏል፡፡

ይህ እንግዲህ ሸላሚው ሂዩማን ራይትስ ዎች ኢትዮጵያን በተመለከተ ያለውን አቋም ያመለክታል፡፡ ወደ እውነታው ስንመለስ ግን ሂዩማን ራይትስ ዎች ከያዘው አቋም የተለየ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

ከ20 ዓመታት በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ ሀሳብን የመግለፅ ነፃነት ወይም የፕሬስ ነፃነት የሚባለው ጉዳይ እንኳን በህግ ሊረጋገጥ ስሙንም ማንሳት አስፈሪ ነበር፡፡ በዘውዳዊው ስርአት ንጉሰነገስቱንና ስርአቱን ከማወድስ ሃሳብ ወጣ ያለ ሃሳብ ማቅረብ እንደነገር ፍለጋ ነበር የሚቆጠረው፡፡ ንጉሰ ነገስቱ እና መሳፍንቱ ከሚፈልጉት ነገር ውጭ መናገር የንጉሰ ነገስቱን ክብር እንደመንካት ነበር የሚቆጠረው፡፡ የንጉሱን ክብር ነክተሃል በሚል በዋዛ የሚታለፍም አልነበረም፣ ያስግዛል፣ ያሳስራል፣ ያስገድላል፡፡

እናም በወቅቱ የነበሩት ጋዜጦች፣ መፅሄቶች፣ መፃህፍት፣ ቲያትሮች፣ ዘፈኖች ኢትዮጵያዊያንን ከሰው በታች አድርጎ የሚቆጥረውንና ሰብአዊ ክብራቸውን ያዋራደውን ዘውዳዊ ስርአት የሚያወድሱና ዘላለማዊነትን የሚመኙ ነበሩ፡፡

በአጠቃላይ ሃሳብን የመግለጽ ነጻነት ተግባራዊ የሚሆንበት የፕሬስ ነጻነት ህጋዊ እውቅና ተነፍጓቸው ቆይተዋል፡፡

ይህን የተካው የጥቂት ወታደሮች አምባገነን ስርአትም በተመሳሳይ ሁኔታ ሃሳብን ለመግለፅ ነጻነት ሕጋዊ እውቅና የነፈገ ነበር፡፡ በዚህ ስርአት በርካቶች ሃሳባቸውን ስለገለጹ ብቻ ታስረዋል፣ ተደብድበዋል፣ ተገድለዋል፣ የደረሱበት ሳይታወቅ የቀሩትም አያሌዎች ናቸው፡፡ እንኳን ሃሳብን በይፋ መግለጽ ሌሎች የገለፁትን ሃሳብ ማዳመጥ፣ ማንበብ፣ … አይቀጡ ቅጣት ያስቀጣ ነበር፡፡ ይህ የቅርብ ግዜ ትዝታችን ነው፡፡ እንግዲህ ኢትዮጵያዊያን በዚህ አኳኋን አንደበታችን ተለጉሞ፣ ጆሯችን ተደፍኖ፣ አይናችን ተጋርዶ ኖረናል፡፡

ይሁን እንጂ ከ20 ዓመታት በፊት የአንደበታችን ልጓም፣ የጆሯችን ማሸጊያ፣ አይናችን ላይ የነበረው መጋረጃ ወልቀው ተጣሉ፤ ወድቀው ደቀቁ፡፡

ይህ የሆነው የደርግን ውድቀት ተከትሎ የተመሰረተው የሽግግር መንግስት እንደ ሕገመንግስት ይተዳደርበት በነበረው ቻርተር ላይ ሃሳብን የመግለጽ ነጻነት በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በመከበሩና በዚሁ መሰረት በ1983 ዓ.ም የፕሬስ ነጻነት አዋጅ በመውጣቱ ነው፡፡

ይህን ተከትሎ በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ግዜ በሁሉም ጉዳዮች ላይ - ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ መፅሄቶች፣ ጋዜጦች፣ መፃህፍት በአንድ አፍታ ፈሉ፡፡ ህዝቡም የቀረቡለትን እነዚህን የህትመት ውጤቶች ሳያማርጥ የረሃቡን ያህል አነበባቸው፤ የቻለው ገንዘቡ ሳያሳሳው እየገዛ ያልቻለው ደግሞ እየተዋሰ፡፡ ያኔ የነበረውን ሁኔታ ያሰተዋለ ሃሳባችንን የመግለጽ መብት ተነፍጎን ምን ያህል ታፈነን እንደነበረ፤ ምን ያህል ሃሳብ ተጠምተን እንደነበር መገንዘብ ይችላል፡፡

ይሁን እንጂ እንዲህ እንደ አሸን የፈሉ ሁሉም መጽሄቶችና ጋዜጦች ሃሳብን የመግለጽ መብት መከበር መድረሻ የሆነውን የዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ፣ ሰላምና ልማት የሚያጎለብቱ አልነበሩም፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩብትን መብት ያስከበረውን፣ ሃሳብን የመግለጽ መብትና ነጻነት ያረጋገጠውን ስርአት ለማጥፋት ሕዝብን በሕዝብ ላይ፣ ሃይማኖትን በሃይማኖት ላይ የሚያስቆጣና የሚያስነሳ ይዘት የነበራቸው ጽሁፎች የሚያወጡ ነበሩ፡፡

ጋዜጦቹና መጥሄቶቹ ራሳቸውን “ነጻ ፕሬስ” ብለው ሳይሆን “ተቃዋሚው ፕሬስ” ብለው ነበር የሚጠሩት፡፡ በመሰረቱ ተቃዋሚ ፕሬስ የሚባል ነገር የለም፤ አንድ የህትመት ውጤት ወይ ነጻ ፕሬስ ነው አለያም አንድ አመለካከትና አቋም ያለው ቡድን ልሳን ነው፡፡

ታዲያ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተረጋገጠው ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት መከበር የወለዳቸው ፕሬሶች ይህን ስያሜ ለራሳቸው የሰጡት በነጻ ፕሬስ መርህ መሰረት በገለልተኝነት ስለማይሰሩ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ነጻ ፕሬስ አለመሆናቸውን የሚያሳይ ራሳቸው የሰጡት ምስክርነት ተደርጎ ሊቆጠር ይችላል፡፡

የዚህ ምክንያት አዲሱ የመንግስት ስርአት አፍላ በነበረበት ወቅት የታተሙትን ጋዜጦችና መፅሄቶች የወደቀውን ስርአት ሲያገለግሉ በነበሩ ልሂቃን የሚዘጋጁ መሆናቸው ነው፡፡ እርግጥ አድብተው የነበሩ የዘውዳዊው ስርአት ልሂቃንም ከቀድምቶቹ ባለመጽሄትና ባለጋዜጦች መሃከል ይግኙበት ነበር፡፡

ዘገባዎቻቸው የመናገርና የመጻፍ መብት ያስገኘላቸውን ዴሞክራሲያዊ ስርአት የበለጠ እንዲጠራና እንዲጎልብረቱና ሰላማዊ የስልጣን ሽግግርን የሚያበረታቱ አልነበሩም፡፡ ከዚህ ይልቅ በሰሜን፣ በምስራቅ … እከሌ የተባለ ጄነራል፣ ሚኒስቴር …(የቀድሞዎቹን ስርአት ሲያገለግሉ የነበሩ ጄነራሎችንና ሚኒስትሮችን ስም እየጠቀሱ)  የሚመራ ጦር ወደመሃል እየገሰገሰ ነው፣ የወያኔ መንግስት አበቃለት የሚል የፈጠራ ውዠንብር መንዛት ላይ የሚያተኩሩ ነበሩ፡፡

በማህበራዊ ጉዳይ ላይ ከሚያተኩሩት መሃከል ደግሞ በርካቶቹ የህብረተሰቡን ስነምግባርንና ባህል የሚጻረሩ፣ እንደጸያፍ የሚቆጠሩ አስነዋሪ ልቅ የሆነ ወሲባዊ ይዘት (pornographic) መልክ የነበራቸው ነበሩ፡፡

በተለይ ሕዝቡን በየቤቱ በቀጥታ የሚነካው ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ መጽሄቶችና ጋዜጦች ጉዳይ ህዝቡ ከሚታገሰው በላይ በመሆኑ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች  ሰላማዊ ሰልፍ እስከ መውጣት የዘለቀ ተቃውሞ ተካሂዶባቸው እንደነበረ እናስታውሳለን፡፡ እነዚህ ነጻ ፕሬስ በሚል የተቋቋሙ ጋዜጦችና መጽሄቶች ገሚሶቹ ሕዝብ አንቅሮ ተፍቷችው በኢትዮጵያ የፕሬስ ታሪክ ውስጥ አሳፋሪ ምልክት ትተው አልፈዋል፡፡

በዚህ መሃለ ሕግንና የሙያ ስንምግባርን አክብረው የሚሰሩ ጋዜጦችና መጽሄቶች ብቅ ብቅ ማለት ጀመሩ፡፡ እነዚህ ነጻ ጋዜጦች ስርጭት ሲጀምሩ በተቃዋሚው ፕሬስ ጦርነት ተከፍቶባቸዋል፡፡  ኃላፊነት በተሞላበት መንፈስ የጋዜጠኝነት ሙያ ተግባራቸውን በመፈፀማቸው የወያኔ ጋዜጦች የሚል ወሬ በመንዛት ነበር ሊያሸማቀቋቸው የሞከሩት፡፡

የተወሰኑት ማሸማቀቂያውን ፈርተው ከፍረጃው ነጻ ለመሆን ራሳቸውን በተቃዋሚው ፕሬስ አቅጣጫ ከረከሙ፡፡  ያለምንም መሸማቀቅ ግልጽ የነጻ ፕሬስ አቋም ይዘው የዘለቁም አሉ፡፡ እነዚህ የነጻ ፕሬስ መርህ ላይ የተመሰረቱት ጋዜጦች ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ እስካሁን መዝለቅ ችለዋል፡፡

ጽነፈኛ ተቃዋሚ ፕሬሶቹ ገበያ የሌላቸው ቢሆኑም፣ የተወሰኑት ከዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ይልቅ ሕገመንግስታዊ ባልሆነ የኃይል መንግድ የመንግስት ስልጣን ለመመንተፍ በቋመጡ በውጭ አገራት እንዲሁም ሰላማዊ ካባ ለብሰው ለተመሳሳይ አላማ በሚንቀሳቀሱ አገር ውስጥ ባሉ ቡድኖች የገንዘብ ድጋፍ ስለሚደረግላቸው እየታተሙ መሰራጨታቸው ቀጥሏል፡፡

ምርጫ 97ን ተከትሎ የኢትዮጰያ ሕዝብ በምርጫ የሰጣቸውን የስልጣን ውክልና ከመቀበል ይልቅ ለምርጫ ባልተወዳደሩበትና ከገዢው ፓርቲ ውጭ የሆኑ ሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች ባሸነፉባቸው አካባቢዎችም “እኛ ነን ያሸንፍነው፣ ምርጫ ተጭበርብሯል” ብለው የማይጨበጥ ምክንያት በማቅረብ  በኃይል ስልጣን ለመመንተፍ የተደረገውን ሙከራ በማቀናጀትና በመምራት ረገድ ተቃዋሚ ፕሬሶቹ ትልቅ ድርሻ ነበራቸው፡፡

አመጹን ያቀደው ቡድን የጠነሰሰውን በኃይል መንግስትን የመጣል ሙከራ ለማስፈጸም የታወጀውን የክተት ጥሪ ያወጁት ተቃዋሚ ፕሬሶቹ ነበሩ፡፡ የአመጽ ጠንሳሾቹ ጥቂት በከተማ የሚኖሩ የዋሕ ደጋፊዎቻቸው ለአመጽ እንዲነሱ ያወጁትን ጥሪ ማስተላለፍ በራሱ ሕገ ወጥ ድርጊት ነው፡፡

የአመፅ ጥሪው ደጋፊዎቻቸው አደባባይ ወጥተው ሁከት እንዲያነሱ ከማድረግ በተጨማሪ የኢሕአዴግ ደጋፊዎች ናቸው ብለው ያሰቡዋቸው ሰዎችን ከማህበራዊ ኑሮና ከኢኮኖሚያዊ ግንኙነት እንዲያገሉ የሚጠይቅ ነበር፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ደጋፊዎቻቸው የተለያዩ መረጃዎችንና ሃሳቦችን ተመልክተው በራሳቸው ውሳኔ እንዳይንቀሳቀሱ እንደጋሪ ፈረስ እይታቸውን ጋረደው  በአመጽ አቅጣጫ ብቻ ለመንዳት እንዲያመቻቸው ደጋፊዎቻቸው ማንበብ፣ ማዳመጥና መመልከት የለባችውም ያሉዋቸውን ጋዜጦች፣ የሬዲዮ ጣቢያዎ እና ቴሌቪዥኖች ለይቶ የሚገልጥ ነበር፡፡

ታዲያ ነጻ ፕሬስ እንደሆኑ ሲነግሩን የነበሩት ተቃዋሚ ፕሬሶች ይህን ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ፤ መረጃ የማግኘትና የሌሎችን ሃሳብ የመጋራት መብት የሚጻረር አዋጅ ያለአንዳች ሃፍረት ተቀብለው አስተላልፈዋል፡፡ እንዳይነበቡ ከተባሉት ጋዜጦች በማከል የግል ጋዜጣም ይግኝበት ነበር፡፡

በዚህ አኳኋን ከላይ የተገለጸውን ዴሞክራሲያዊ፣ ሰላማዊና ህጋዊ ያልሆነ  እንዲሁም ሃሳብን የመግለጽ ነጻነትን መንፍስ የሚቃረን አካሄድ ሲከተሉ ከነበሩ ጋዜጦች መሃከል አሁን ሂዩማን ራይትስ ዎች “ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ አርበኛ” ብሎ የሸለመው እስክንድር ነጋ የሚያዘጋጀቸውና የሚያሳትማቸው ጋዜጦች ይገኙበታል፡፡

ያም ሆነ ይህ ተቃዋሚ ፕሬሶቹ ስልጣንን በኃይል ለመመንተፍ ከሞከረው ቡድን ጋር ሆነው የመሩት እንቅስቃሴ በጥቂት የአገሪቱ ከተሞች እጅግ በጣም ጥቂቶች ከተሳተፉበት ሁከትነት ሳያልፍ ተጨናገፏል፡፡ ከዚያም በኋላ ግን በነጻ ፕሬስ ሽፋን በህግ ወጥ መንገድ ስልጣን ለመያዝ በሚሹ በተለይ በውጭ አገር በሚኖሩ ቡድኖችና ግለሰቦች ስፖንሰርነት የሚንቀሳቀሱ ጋዜጦች ቀጥለዋል፡፡ በመሰረቱ እነዚህ ጋዜጦች የስፖንሰር አድራጊዎቹ ቡድኖች ልሳኖች ናቸው እንጂ ነጻ ፕሬሶች አይደሉም፡፡

ወደዋናው ጉዳይ ስንመለስ አሁን ሂዩማን ራይትስ ዎች የተሰኘው ድርጅት “ሃሳብን የመግለጽ ነጻነትን ለማጎልበት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሲሰሩ ነበር” በሚል የሸለማቸው “ጋዜጠኞች” በፍርድ ቤት ቅጣት ተወስኖባቸው በማረሚያ ቤት የሚገኙት በጋዜጣቸው ላይ በጻፉት ወይም በተናገሩት ሃሳብ ምክንያት ሳይሆን በሽብርተኝነት ወንጀል ነው፡፡ ክሳቸው ፍርድ ቤት ቀርቦ ጥፋተኛ ለመባልና ለቅጣት ውሳኔ ያበቃቸው ማስረጃም ይህንኑ የሚያመለክት ነው፡፡

እዚህ ላይ አንድ መነሳት ያለበት ነገር በተለየ እስክንድር ነጋ፡ ውብሸት ታዬና ርዕዮት ዓለሙ (ጋዜጠኛ ሳትሆን መምህር ነች) ክስ ተመስርቶባቸው ስለተገኘባቸው ማስረጃ እንደተገለጸ የቀረበው ተቃውሞ “የተገኘው መረጃ ትክክል አይደለም” የሚል ሳይሆን “ማስረጃው የተገኘበት መንገድ ሕገ መንግስታዊ አይደለም” የሚል ላይ የሚያተኩር ነበር፡፡

ይህም በተከሳሾቹ ላይ የቀረበው ማስረጃ በተለየ በኢንተርኔትና በስልክ ካደረጉት የመልዕክት ልውውጥ ተጠልፎ የተገኘ መሆኑን መነሻ ያደረገ ነበር፡፡ የማስረጃዎቹን ትክክለኛ መሆን ወይም አለመሆን ጉዳየ ትተው፣ ማስረጃው የተገኘበት መንገድ ላይ አተኩረው የተቃወሙት ግለሰቦችና ድርጅቶች በአስረጂነት የጠቀሱት የሕገ መንግስቱን አንቀጽ 26 ንኡስ አንቀጽ 2 ነበር፡፡

ይህ የህገ መንግስት አንቀጽ “ማንኛውም ሰው በግል የሚጽፋቸውና የሚጻጻፋቸው፣ በፖስታ አማካኝነት የሚልካቸው ደብዳቤዎች፣ እንዲሁም በቴሌፎን፣ በቴሌኮሚዩኒኬሽንና በኤሌክትሮኒክ መሳሪያዎች የሚያደርጋቸው ግንኙነቶች አይደፈሩም” ይላል፡፡

አሁን ሂዩማን ራይትስ ዎች ከሸለማቸው መሃከል የሚገኙት “ጋዜጠኞች” ላይ የተገኘው በሽብርተኝነት ድርጊት ውስጥ መሳተፋቸውን የሚያሳይ ማስረጃ፣ ጥፋተኝነታቸውን የሚያረጋግጥ ቢሆንም የተገኘበት መንገድ ተገቢ አይደለም ባዮች ናቸው፡፡ ከዚህ በመነሳት ለጠቅላይ ሚኒስትሩም ደብዳቤ የጻፉ ድርጅቶች እንደነበሩ እናስታውሳለን፡፡ ሆኖም ግለሰቦቹ ላይ የቀረበው ማስረጃ የተገኘበት መንገድ ሕገ መንግስታዊ መሰረት ነበረው፡፡

ከላይ በተጠቀሰው የሕገመንግስቱ አንቀጽ ንኡስ አንቀጽ 3 ላይ የሰፈረው ይህንኑ ያመለክታል፡፡ ንኡስ እንቀጹ “… አስገዳጅ ሁኔታዎች ሲፈጠሩና ብሄራዊ ደህንነትን፣ የህዝቡን ሰላም፣ ወንጀልን በመከላከል፣ ጤናንና የህዝብ የሞራል ሁኔታ በመጠበቅ ወይም የሌሎችን መብትና ነጻነት በማስከበር ኣላማዎች ላይ በተመሰረቱ ዝርዝር ሕጎች ” በሚል ተፈጻሚ የማይሆንበትን አግባብ አስቀምጧል፡፡

ዝርዝር ሕጉ ደግሞ በጸረ ሽብርተኝነት ሕጉ ላይ የተደነገገው ነው፡፡ የጸረ ሽብርተኝነት ሕጉ  የተወሳሰበና አደገኛ ከሆነው የሽብርተኝነት ወንጀል ጥቃት ሕዝቡንና ሕገመንግስታዊ ስርአቱን ለመከላከል ሲባል የህግመንግስቱ አንቀጽ 26 ንኡስ አንቀጽ 2 አተገባበር በንኡስ አንቅጽ 3 መሰረት እንዲሆን ይፈቅዳል ፡፡

ሂዩማን ራይትስ ዎች የሸለማቸው ጋዜጠኞች በምስጢር ተጠልፎ የተገኘ ማስረጃ ብቻ አይደለም የቀረበባቸው ማስረጃ፡፡ ተግባራቸውን የሚያረጋግጥ የሰው ምስክርም ቀርቦባቸዋል፡፡

ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር ውልው ክስ የተመሰረተባቸው፣ ጥፋተኛነታቸው በማሰረጃ ተረጋግጦ የቅጣት ውሳኔ የተላለፈባቸው ከላይ በተገለጸው መሰረት የሽብር ወንጀል ለማካሄድና ለማገዝ በፈጸሙት ድርጊት ነው፡፡ አንዳቸውም በሚያዘጋጁትና አምደኛ ሆነው በሚጽፉበት ጋዜጣ ላይ ባወጡት ጽሁፍ የሃሳብ ይዘት የተጠየቁ አይደሉም፡፡

ተሰደደ የተባለው የአዲስ ነገር ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ መስፍን ነጋሽም በውጭ አገር ጥገኝነት ለማግኘት እንዲያመቸው “ ደሕንነቶች ተከታተሉኝ …” ብሎ ውዥንብር ነዝቶ ከአገር ከወጣ በኋላ በሌለበት ነው የተከሰሰው፡፡ እሱም ቢሆን ግን አገር ቤት ሳለ ሲያዘጋጀው በነበረው ጋዜጣ ላይ በጻፈው ፅሁፍ ይዘት  ተከሶ አይደለም ቅጣት የተወሰነበት፡፡ ጥገኝነት ባገኘበት አገር ሆኖ ሽብርተኝነትን ለማገዝ በፈጸመው ድርጊት እንጂ፡፡ የቀረበበትም ማስረጃ ይህንነኑ ወንጀል የሚያመለክት ነው፡፡

እንግዲህ ሂዩማን ራይትስ ዎች  ለእነዚህ አራት “ጋዜጠኞች” ሽልማት የሰጠው በይፋ እንደገለጸው በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ሃሳብን የመግለጽ ነጻነት እንዲጎለብት ላደረጉት ጥረት አይደለም፡፡ የደርጅቱ ይይ ተግባር ዋነኛው ምክንያቱ ሃሳብን የመግለጽ ነጻንት ሳይሆን  ርዕዮት ዓለማዊ ነው፡፡

በስልጣን ላይ ያለው የኢትዮጵያ መንግስት የሚከተለው የፖለቲካል ኢኮኖሚ መርህ ልማታዊነት (developmentalism) መሆኑ ይታወቃል፡፡ ሂዩማን ራይትስ ዎችን ገንዘብ እያዘነቡ ስውር ዓላማ አስታጥቀው የሚያሾሩት ቡድኖችና ግለሰቦች ደግሞ አክራሪ የኒዮሊበራሊዝም አራማጆች ናቸው፡፡

እናም ኢትዮጵያ ከኒዮሊበራሊዝም አመለካከት የተለየ  የሆነውን ልማታዊነት ይዛ የኢኮነሚ እድገት ማስመዝገቧ፣ ዴሞክራሲን ማስፈኗ፣ ሰብአዊ መብቶችን ማስከበሯ ሂዩማን ራይትስ ዎችን በገንዘባቸው ላቆሙትና የህልውናው ምንጭ ለሆኑት አክራሪ ኒዮሊበራሊስቶች  አልተዋጠላቸውም፡፡ እንደ ርዕዮተ ዓለም ሽንፈት ነው የቆጠሩት፡፡

ስለዚህ ሂዩማን ራይትስ ዎች ኢትዮጵያ በዜጎቿና በአለም አቀፉ ማሕበረሰብ ዘንድ መጥፎ ገጽታ እንዲኖራት ሃሰተኛ ምስል እያቀረበ በአገር ውስጥ አመጽ የሚቀሰቀስበትን ሁኔታ የማመቻቸት ስልት እየተከተለ ይገኛል፡፡

ሂዩማን ራይትስ ዎች አሁን “ጋዜጠኞች” ያላቸውን ሰዎች የሸለመው ኢትዮጵያ ውስጥ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት አይከበርም በሚል ከዚህ ቀደም በየአጋጣሚው ሲቸከችከው የነበረው ልቦለዱ ትኩረት እንዲስብለትና የኢትዮጵያን ገጽታ የማቆሸሽ ዓላማው እንዲሳካ ለማድረግ ነው፡፡

ሂዩማን ራይትስ ዎች እውነት ሃሳብን የመግለጽ መብት ጉዳይ አሳስቦት፣ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሃሳብን በነሳነት ለመግለጽ መብት መጎልበት የሚሰሩ ጋዜጠኞች ጉዳይ አሳስቦት ዋነኛ አጀንዳው አድርጎት ቢሆን ኖሮ፣ ኤርትራ ውስጥ መሸለም የሚገባቸው በርካታ የታሰሩ፣ የተገደሉ፣ የደረሱበት የማየታወቅ ጋዜጠኞች ነበሩ፡፡ ይሄ ግን ግድ አልሰጠውም፡፡ ይህ ሁኔታ የሂዩማን ራይትስ ዎች ዓላማ ሰብአዊ መብት ያለመሆኑን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በሽብርተኝነት ወንጀል ተከሰው ጥፋተኝነታቸው በማስረጃ ተረጋግጦ የቅጣት ውሳኔ የተላለፈባቸውን አራቱን ግለሰቦች መርጦ መሽለሙ ለሽብርተኝነት ድርጊት እውቅና እንደመስጠትና እንደማበረታታት ይቆጠራል፡፡

ሽብርተኝነት ደግሞ አስከፊ የሰብአዊ መብት ጥሰት በመሆኑ ድርጅቱ እንደሚናገረው ለሰብአዊ መብት የቆመ ሳይሆን ስውር አላማውን ማሳካት እስከቻለ ድረስ የሰብአዊ ምብት ጥሰት እንዲፈጸም ከማበረታታት የማይመለስ መሆኑን ያረጋግጣል፡፡