ኢትዮጵያ የበካይ ጋዝ መጠንን ዜሮ ለማድረስ እየሰራች ነው

  • PDF

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 23/2005 (ዋኢማ) - የተባበሩት መንግስታት ደርጅት በኳታር ዶሀ ባደረገው የአየር ንብረት ጉባኤ ላይ ይፋ እንዳደረገው በአለማችን ወደ አየር የሚለቀቁ በካይ ጋዞች በአስደንጋጭ ሁኔታ ጨምረዋል፡፡

የአፍሪካ ህብረትም የተለያዩ ሀገራት ርዕሳነ ብሔሮች የሚገኙበት በጉዳዩ ላይ የሚመክር መፍትሄ አፈላላጊ  ኮሚቴ አቋቁሞ  ወደ ስራ የገባ ሲሆን ፥ የቀድሞው የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር መለሰ ዜናዊ ለሁለት ጊዜያት ኮሚቴውን በመምራት አፍሪካ የጉዳቷን እንድትካስ ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡

በውጤቱም  አረንጓዴ የገንዘብ ቋት የተሰኘ ተቋም ተቋቁሞ  ፥ እስከ ተጠናቀቀው አመት 30 ቢሊየን ዶላር ለሀገራቱ እንዲሰጥ እንዲሁም እ.ኤ.አ እስከ 2020 የገንዘቡ መጠን ፥ 100 ቢሊየን ዶላር እንዲደርስ መታቀዱን የኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዳይሬክተር ዶክተር ተወልደ ብርሀን ገብረእግዚአብሄር ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያም ለዘርፉ ትከረት በመስጠት የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ተግብራ እየተንቀሳቀሰች ሲሆን ፥ በአራት አቅጣጫዎች የተቀመጠው ይህ ትግበራ ሀገሪቱ በ2015 ወደ አየር የሚለቀቀውን የካርበን መጠን 0 የማድረስ እቅዷን ለማሳካት ያግዛል፡፡
ዶክተር ተወልደ ብርሀን እንደሚሉት ልቀቱን ለመቆጣጠር ዛፍ ከመትከልና የደን ሀብቱን ከመጠበቅ ባለፈ ሀገሪቱ የኤሌከትሪክ ሀይል ምንጯን ከታዳሽ የሀይል ምንጮች ብቻ እንድታመርት ይጠበቃል፡፡

ከ2007 ዓ.ም በኋላም በኢትዮጵያ ከጄኔሬተር የሚመነጭ የሀይል አቅርቦት እንዳይኖር ለማድረግ ፥ ማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎችን ማስፋፋት ፣ የትራንስፖርት ዘርፉንም ከነዳጅ ጥገኝነት ወደ ኤሌክትሪክ ሀይል መቀየር ሌላው የትግበራው አካል መሆናቸውንም ነው ዶክተር ተወልደ ብርሀን የገለጹት።

አገሪቱ እስካሁን ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተገናኘ በሰራችው ስራ ያገኘቻቸውን  ድጋፎች ፥ በቀጣይም በተሻለ ሁኔታ ለማግኘት አሳማኝ የስራ እቅድ በማቅረብ ለመስራት ታቅዷል ብለዋል።

የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታው አቶ ስለሺ ጌታሁን በበኩላቸው ፥   ለዚህ አቅድ መሳካት ዋነኛ መሳሪያ የሆነው የደን ሀብትን መንከባከብ ላይ ህብረተሰቡን ያሳተፉ ስራዎች ተጠናክረው  እንደሚቀጥሉ ፋና ዘግቧል።