የሃገሪቱን ፖለቲካዊና ማህበራዊ ተቋማትን ለማናጋት ተንቀሳቅሰዋል የተባሉ ተከሳሾች ጥፋተኛ ተባሉ

  • PDF

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 23/2005 (ዋኢማ) - የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 4ኛ የወንጀል ችሎት የአል- ሸባብና የአልቃይዳ አባል በመሆን የሃገሪቱን ፖለቲካዊና ማህበራዊ ተቋማትን ለማናጋትና የሃይማኖት ግጭት ለመክፈት ተንቀሳቅሰዋል በተባሉ 10 ተከሳሾች ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ አሳለፈ።

ተከሳሾቹ 1ኛ አቶ ሃሰን ጃርሶ ፣ 2ኛ አቶ መሃመድ ቃሲም ፣ 3ኛ አቶ ዑመር ሙሳ ፣ 4ኛ አቶ አብዲ ሽኩር ፣ 5ኛ አቶ በሽር ሃጅ እና ሌሎች በአካል ያልቀረቡ 6 ግለሰቦች ናቸው።

ተከሳሾቹ የሃገሪቱን መሰረታዊ ፣ ፖለቲካዊ ፣ ህገ መንግስታዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተቋማትን ለማናጋት ፥ ወይም ለማፍረስ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት በተፈረጀው እና ፤ ራሱን አል ሸባብ ብሎ በሚጠራው ቡድን እና አልቃይዳ በተባሉ አሸባሪ ቡድኖች ውስጥ አባል በመሆን ፥ ቀንና ወሩ ባልታወቀበት በ2000 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ ሶማሊያ ሞቃዲሾ ውስጥ በሚገኙ በተለያዩ ማሰልጠኛ ቦታዎች ለሽብር አላማ ማስፈጸሚያ የሚሆን ወታደራዊ ስልጠናዎች በመውሰድ ተከሰዋል።

ከአልሸባብ እና ከአልቃይዳ የተሰጣቸውን ተልዕኮ በመቀበል ወደ ኢትዮጵያ በህገ ወጥ መንገድ በመግባት ፥ ሃይማኖትን እንደ ሽፋን በመጠቀም ግጭት ለመፍጠር የሚያስችል ስለ ጦር መሳሪያ አጠቃቀምና የአባላት መመልመያ ማንዋል በማዘጋጀት እና በመመልመል ግጭት ለመቀስቀስ በማቀድ መዘጋጀታቸውን የቀረበባቸው ክስ ያስረዳል።

ለዚህ የሽብር አላማ ማስፈጸሚያም የሎጅስቲክስ ፣ የስልጠና ቦታ እና ገንዘብ ማግኘት እንዲችሉ ከአልሸባብ እና ከአልቃይዳ አመራሮች ጋር በኢ ሜይል መልዕክት ተለዋውጠዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።

ለአብነትም 1ኛ ተከሳሽ አቶ ሃሰን ጃርሶ በ2001 ዓ.ም ኬንያ ናይሮቢ ውስጥ  ፥ ሳቢጥ በተባለ ግለሰብ ተመልምሎ ሶማሊያ ውስጥ የሚገኙ ወንድሞቻችንን ማገዝ አለብን በማለት ከሌሎች ግብረ አበሮቹ ጋር በመሆን ፤ ትጥቅ በማሟላት በለደወየኒ በተባለ ቦታ እና በሌሎችም አካባቢዎች ከሌሎች ሃገራት ዜጎች ጋር ወታደራዊ ስልጠና የወሰደ ነው።

በ2003 ዓ.ም መጨረሻም በሞቃዲሾ ከተማ ከሶማሊያ የሽግግር መንግስት ፣ ከኡጋንዳ እና ከብሩንዲ ሰላም አስከባሪዎች ጋር ተዋግቷል።
ሃሰተኛ የኢትዮጵያ መታወቂያ አሰርቶ ወደ ኢትዮጵያ በመግባት ፥ ቀደም ሲል ከገቡ የሽብር ቡድኑ አባላት ጋር በመሆን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን እንቅስቃሴ ለአልቃይዳ ሪፖርት በማድረግ ፥ ገንዘብ እንዲላክ በመንቀሳቀስና የጦር መሳሪያ እንዴት ማግኘት እንደሚቻል መረጃ መለዋወጡ በክሱ ላይ ተመልክቷል።

በተከሳሾቹ ላይ 6 አይነት ክሶች የተመሰረቱ ሲሆን ፥ ከ1ኛ ተከሳሽ በተጨማሪ በሌሎችም ተከሳሾች ላይ የቀረቡ ክሶች ተደምጠዋል።
በዚህም ተከሳሾቹ አለም አቀፍ አሸባሪ የሆኑትን የአልቃይዳ እና የአል ሸባብን ተልዕኮ ለማስፈጸም ፥ ከሶማሊያ ወደ ኢትዮጵያ በመግባት ፤ ግጭት በመቀስቀስ ፣ አባላትን በመመልመል እና በማደራጀት ፣ ስልጠና በመስጠት ፣ በውጭ ሃገር ተወካይ በማስቀመጥ ፣ ገንዘብ በማሰባሰብ ፣ በህዝብ ላይ ጥፋት እንዲፈጸም ተንቀሳቅሰዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።

ከሳሽ አቃቤ ህግም ያሉትን የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን በማቅረብ ለችሎቱ አስደምጧል።
ከተከሳሾች ውስጥ 1ኛ ተከሳሽ ድርጊቱን በከፊል አምኖ  በከፊል ክዶ ሲከራከር ፥ ከ2ኛ እስከ 5ኛ ያሉ ተከሳሾች ድርጊታቸውን ክደው ተከራክረዋል።

ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን ክርክር ተመልክቶ 5ኛ ተከሳሽ አቶ በሽር ሃጅን በነጻ ሲያሰናብት ፥ በቀሩት 10 ተከሳሾች  ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ አስተላልፏል።

ፍርድ ቤቱ የቅጣት ውሳኔ ለማስተላለፍ ለጥር 7 ቀን 2005 ዓ.ም ቀጠሮ መያዙን ፋና ዘግቧል።