ጠ/ሚ ኃይለማርያም የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነትና ደህንነት ፖሊሲ ስትራቴጂካዊ ትኩረቱ በጎረቤት ሀገራት ላይ መሆኑን ገለፁ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 24/2005 (ዋኢማ) - የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነትና ደህንነት ፖሊሲ አሁንም ስትራቴጂካዊ ትኩረቱ በጎረቤት ሀገራት ላይ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከውጭ ግንኙነት ጋር ተያይዞ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነትና ደህንነት ፖሊሲ አሁንም ስትራቴጂካዊ ትኩረቱ በጎረቤት ሀገራት ላይ መሆኑን ገልፀዋል ፡፡

ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራቱ ጋር ባላት ግንኙነት በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚያዊ ትስስር በመፍጠር እና የጋራ ሰላምን የማረጋገጥ ስራው በምን ደረጃ ላይ ይገኛል በሚል ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄም ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ፣ የሀገሪቱ የውጭ ግንኙነትና ደህንነት ፖሊሲ አሁንም ሰትራቴጂካዊ ትኩረቱ በጎረቤት ሀገራት ላይ ነው ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ምስራቅ አፍሪካ በኃይል አቅርቦት እና በሌሎች መሰረተ ልማቶች ይበልጥ እንዲተሳሰር ጥረቷን አጠናክራ ቀጥላለችም ብለዋል ፡፡

ከሁለት አስርት አመታት በኋላ ሶማሊያ ዛሬ የሰላም አየር እየተነፈሰች ትገኛለች፡፡ ሀገሪቱ አዲስ ህገ መንግስት አፅድቃለች፡፡ አዲስ ፓርላማ አውጃለች፡፡ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ አካሂዳለች እንዲሁም አሸባሪው ቡድን አልሸባብም ሙሉ በሙሉ በመደምሰስ ላይ ነው፡፡ በሶማሊያ የተገኘው ሰላም እንዳይቀለበስ ኢትዮጵያ ከሶማሊያ መንግስት ጋርም ይሁን በምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ኢጋድ በኩል የምታደርገው ድጋፍ ይቀጥላል ነው ያሉት፡፡

ሱዳን እና ደቡብ ሱዳን 90 በመቶ የሚሆነው አለመግባባታቸውን ሊፈታ የሚችል ስምምነት ባለፈው መስከረም ተፈራርመዋል፡፡ ስምምነቱ ሳይተገበር ሶስት ወር ሆኖታል ያሉት ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ሀገራቱ ወደ ተግባር እንዲገቡ ቀሪ የድህረ ሪፈረንደም ጉዳዮችም በስምምነት እንዲቋጩ ኢትዮጵያ የሚጠበቅባትን ታደርጋለች ብለዋል፡፡

እንደ ኢሬቴድ ዘገባ የኤርትራን መንግስት በተመለከተም ኢትዮጵያ ላላፉት አመታት ስታራምድ የቆየችውና ሁሌም ለሰላም ዝግጁ የመሆን ፖሊሲ ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት፡፡