የመገናኛ ብዙሃንና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎችን አቅም ማጎልበት ጠቀሜታው የጎላ መሆኑ ተጠቆመ

  • PDF

ድሬዳዋ፤ ታህሳስ 23/2005(ዋኢማ) - የአስተዳደሩን የትኩረት አቅጣጫዎች፣ እቅዶችና ግቦች ወደ ነዋሪው ለማውረድና የህዝቡን ተሳትፎ ለማሳደግ የመገናኛ ብዙሃንና የህዝብ ግንኙነት ባለሞያዎችን አቅም ማጎልበት ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን የድሬዳዋ አስተዳደር የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ አስታወቀ።

የአስተዳደሩ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ምስራቅ ወርቁ ዛሬ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከዋልታ ኢንፎርሜሽን ህዝብ ግንኙነት ማዕከል ጋር በመተባበር የተዘጋጀውን የሚዲያና ህዝብ ግንኙነት ስልጠናን ባስጀመሩበት ወቅት እንደተናገሩት፤ የመገናኛ ብዙሃንና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎችን አቅም በማሳደግ አስተዳደሩ የሚያካሂዳቸውን ሁለንተናዊ የልማት ስራዎችና አቅጣጫዎች ወደ ነዋሪ ለማድረስ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል።

ለስድስት ተከታታይ ቀናት በሚሰጠው ስልጠና 155 የአስተዳደሩ የኮሙኒኬሽን ዘርፍ ኃላፊዎች፣ ኮሙዩኒኬተሮችና የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የተሳተፉ ሲሆን፤ በአዲሱ የመገናኛ ብዙሃንና የሚዲያ አላባውያን ልማታዊ ሚዲያ፣ ኮሙኒኬሽንና የኢትዮጵያ ህዳሴ፣ የህዝብ ግንኙነት ተግባራት፣ መርሆዎችና የልማት ጋዜጠኝነት በሚሉ ርዕሶች ዙሪያ የስልጠናው ይዘት ያተኩሯል ብለዋል።

ሰልጣኞችም ለስልጠናው ተገቢውን ትኩረት በመስጠትና ከስልጠናው በኋላም ያገኙትን እውቀት ወደ ተግባር በመተግበር የአስተዳደሩን ህዳሴ ለማረጋገጥ የበኩላቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

ዋልታ ኢንፎርሜሽንና ህዝብ ግንኙነት ማዕከል ዘንድሮ ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ጋር የተቀናጀ የህዝብ ግንኙነት የትብብር ስራዎች እያከናወነ ሲሆን፤ በዚህም ለከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ስልጠና እንዲሁም የህዝብ ግንኙነትና የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች አቅም ለማሳደግ የተለያዩ ስልጠናዎችን እየሰጠ ይገኛል።

እንዲሁም የአስተዳደሩን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሁኔታ የሚዳስሱ ዘጋቢ ፊልሞችን፣ የአስተዳደሩን እቅድ የሚያስተዋውቁ የቴሌቪዥን አጫጭር ማስታወቂያዎችና የአስተዳደሩን የትግበራና የህዝብ ስሜቶችን የሚገመግሙ ጥናቶችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ የዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘገባ ያስረዳል።