ሶስተኛው የቡና ቀን በኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን ተከበረ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 22/2005 (ዋኢማ) - ሶስተኛው የቡና ቀን “የቡናን ምርታማነት በመጨመርና ጥራትን በመጠበቅ የመለስን ራዕይ እናሳካለን” በሚል መሪ ቃል በኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን ተከብሯል፡፡ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የመልካም አስተዳደርና ሪፎርም ክላስተር አስተባባሪና የሲቪል ሰረቪስ ሚኒትስትሩ አቶ ሙክታር ከድር በዓሉ ህብረተሰብ አቀፍ የቡና ልማት ንቅናቄን ለማጠናከር ያስችላል ነው ያሉት፡፡

ሀገሪቱ ከቡና ልማት በላቀ ደረጃ ተጠቃሚ እንድትሆን ለማስቻል ሰፊ እንቅስቃሴ በመካሄድ ላይ ነው፡፡ በዚህም በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ በቡና ልማት ዘርፍ የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት ተስፋ ሰጪ ምልክቶች እየታዩ መሆናቸውን የገለፁት አቶ ሙክታር ቀጣዩ ትኩረት ይህንን መልካም ጅምር አጠናክሮ ማስቀጠል ነው ብለዋል፡፡

እንደ አቶ ሙክታር ገለፃ “ አርሶ አደሩ ሁሉን አቀፍ የቴክኒክና የኤክስቴንሽን ድጋፍ እያገኘና ዘመናዊ የአመራረት ዘዴዎችን እየተጠቀመ ቡናን በስፋት እንዲያለማና የልፋቱ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማስቻል እንዲሁም የግል ባለሀብቱ በቡና ልማቱ ላይ በንቃት በመሳተፍ ጥራት ላለው የቡና ምርትና ምርታማነት ዕድገት የድርሻውን እንዲወጣ ለማስቻል የተጀመረው ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ ይቀጥላል”

የቡና ግብይት ስርዓቱን ዘመናዊና ቀልጣፋ ለማድረግም መንግስት ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡ በቡና ልማትና ኤክስፖርት ላይ የተሰማሩ አርሶ አደሮችና ባለሃብቶች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላትም የዘርፉን አቅድ ለማሳካት ከመቼውም በበለጠ ተቀናጅተው እንዲሰሩ አሳስበዋል፡፡

የጅማ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ስዩም ኢታና በዓሉ የቡና ልማት ምርታማነትን በማሳደግና ጥራቱን በማስጠበቅ ሀገሪቱ የምታገኘውን ገቢ ለማስፋት ያለመ ነው ብለዋል፡፡ የዞኑ አርሶ አደሮች በአንድ ሄክታር በአማካይ እስከ ሰባት ኩንታል ቡና እንደሚያመርቱ የገለፁት አቶ ስዩም ግንባር ቀደም አርሶ አደሮች በሄክታር ከ15 ኩንታል በላይ ማምረት ችለዋል ነው ያሉት፡፡

ይህን ተሞክሮ ወደ ሌሎች አርሶ አደሮች በማስፋት ምርታማትን ለማሳደግ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ዘላለም ጀማነህ እንደገለፁት በክልሉ በ2004 ዓ.ም ከ380 ሺህ ቶን በላይ ቡና ተመርቷል፡፡ እንደ አቶ ዘላለም ገለፃ አሁን በክልሉ በስምንት ዞኖች 750 ሺህ ሄክታር መሬት በቡና ተሸፍኗል፡፡ በክልሉ የቡና ልማትና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ በቅንጅት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ናቸው፡፡

በቡና ቀን በዓሉ ላይ በቡና ልማት የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ አርሶ አደሮች ባለሀብቶችና ልዩ ልዩ አካላት ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡

እንደ ኢሬቴድ ዘገባ ላለፉት ሶስት አመታት በክልል ደረጃ ብቻ ሲከበር የቆየው የቡና ቀን የቡና ልማትና ግብይቱ ዋንኛ ተዋንያን ውጤታማ ተሞክሮዎቻቸውን እንዲለዋወጡ በማስቻል ዘርፉን ለማሳደግ እንደሚያስቸል በመታመኑ ከቀጣዩ አመት ጀምሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ እንደሚከበር ይጠበቃል፡፡