የጤናው መስክ ስኬት

  • PDF

አለምነህ  እያሱ
ኢትዮጵያ በጤናው መስክ መንግስት በሰጠው ልዩ ትኩረት በመከላከል ላይ ያተኮረ የጤና ፓሊሲ በመከተሏ ባለፋት 20 ዓመታት እጅግ ከፍተኛና ሥር ነቀል ለውጥ አስመዝግባለች፡፡ የኢትዮጵያ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በሀገሪቱ ውስጥ አንጋፋ አድሜ ካስቆጠሩ የሚኒስቴር መ/ቤቶች አንዱ ሲሆን በኢትዮጵያ መንግስት በጀት በለጋሾች ድጋፍና እገዛ አቅሙ በፈቀደ የሕዝቡን ጤና ለመጠበቅና ለመንከባከብ የበኩሉን ጥረት አድርጓል፡፡ ብሔራዊ ኃላፊነቱም የከበደ መሆኑ ይታወቃል፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ በንጉሡም ግዜ ሆነ በደርግ ዘመን የነበሩት የመንግስት ሆሰፒታሎች በቁጥር የታወቁና አነስተኛ ነበሩ፡፡ የሕክምና ሙያ ትምህርት የሚሰጠው በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ወይንም በጎንደር ዮኒቨርስቲ ብቻ ነበር፡፡ እንደዚህም ሁኖ ኢትዮጵያ ውስጥ የተማሩና የተመረቁ ዶክተሮች፤ የጤና መኮንኖች፤ ነርሶችና ፤ጤና ረዳቶች ቁጥር ከሕዝቡ እድገትና ከሀገሪቱ ቆዳ ሰፋት አንፃር ሲታይ እዚህ ግባ የሚባል ዓይነት አልነበረም፡፡

ከጤና ጥበቃ ሚ/ር ሌላ ለሠራዊቱ የጦር ሜዳ ግዳጅ ሲባል ለሕክምና ባለሙያዎች  በጦር ኃይሎች ጠቅላይ ሆሰስፒታል ለጤና ረዳቶች ስልጠና ይሰጥ ነበር፡፡ እነዚህ በሀገሪቱ የተለያዩ ጦር ክፍሎች ለሚሰማራው ስራዊት ለዶክተሮችና ነርሶች ረዳት በመሆን የነፍስ አድን የመጀመሪያ እርዳታ ስራ ላይ ተሰማርተው የሚያገለግሉ ነበሩ፡፡በአሁኑ ሰአት ደረጃውን አሳድጎ ይገኛል፡፡

ሀገሪቱ ለፍታና ደክማ በከፍተኛ ደረጃ ያስተማረቻቸውና ያገለግሉኛል ያለቻቸው የሕክምና ዶክተሮች በአስተዳደር ችግር ፣ በደመወዝ ማነስ፤ ሩቅ ስፍራ ገጠር ሄዶ ሕዝቡን ለማገልገል ፈቃደኝነት ከማጣትም አንፃር የተሻለ ክፍያ ፍለጋ ኢትዮጵያን እየለቀቁ በብዛት ተሰደዋል፡፡ ሀገሪቱ ባላት አቅም የደመዎዝ ጭማሪ ብታደርግም ችግሩ ሙሉ በሙሉ ተቀርፋል  ለማለት አይቻልም፡፡እንደ ደንቡ ከሆነ  ቢቸገሩም ቅድሚያ ሕዝብንና ሀገርን ማገልገሉ ይቀድም ነበር፡፡ ወጥተው የቀሩም ብዙ ናቸው፡፡
ያስተማረችንን ሀገራችንንና ሕዝባችንን ጥለን የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ሰደት አንሄድም፡፡ እንደ ሕዝቡ እየኖርን፤ እንሰራለን፤ አናገለግላለን ያሉት ደግሞ በሀገሪቱ የትኛውም ቦታ በመሰማራት ታላቅ ተግባር አከናውነዋል፡፡ ዛሬም እየሰሩ እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ በተለይ እሰከ ደርግ ውድቀት በየክልሉ ከተማና ገጠር ያለው የጤና አገልግሎት እጅግ በጣም ውስንና የባለሙያ፤ የህክምና መሳሪያ፣ የመድኃኒትም ችግር የነበረበት በመሆኑ የሕክምና አገልግሎት ማግኘት የሚገባው ወገን ባለማግኘቱ ሕብረተሰቡ ከባድ ጉዳት ላይ ወድቆ ነበር፡፡ባለሙያና ሕክምና ሊኖር ቢችል ሊድኑ የሚችሉ ዜጎች ሕክምና በማጣት ሕይወታቸው አልፏል፡፡

እናቶች በወሊድ ሕፃናት በሞት ተለይተዋል፡፡ ተገቢው የጠና መከላከልና ጥበቃ ትምህርት ስለማይሰጥ በተላላፊ በሽታ ያለቀውን ዜጋ ለመቁጠር ያስቸግራል፡፡ ከንፅህና ጉድለት የሚመጡት የኮሌራ በሽታ ታይፈስና ታይፎድ፣ ቀደም ስልም ሆነ በኃላ የፈንጣጣ በሽታና የወባ በሽታ ብዙ ኢትዮጵያውያንን ፈጅቷል፡፡ ጨርሷል፡፡

የመንግስት አቅም ውሱንነት፤ የባለሙያና የመድኃኒት እጥረት፣ በሩቅ ቦታዎች የሕክምና ጣቢያ አለመኖር፤ በወቅቱ ክትትል አድርጎ ለመታከም አለመቻል ፤ሕክምና ለማግኘትም  በከብት ጀርባ ረዥም ኪ- ሜትሮችን አቋርጦ መጓዝ፣ የንፁህ መጠጥ ውሀ አገልግሎት አለመስፋፋትና አለመኖር ፣ በዜጎች ላይ ትልቅ ጥፋት አድርሰዋል፡፡  በአዲስ አበባም ሆኑ በክልሎች ያሉት የመንግስት ሆስፒታሎች ቁጥር ውስንነት፤ የአገልግሎት አለመሟላት፤ የጥራት ጉድለት፤ በቂ የመኝታ አገልግሎት አለመኖር፤ በቀጠሮ መንገላታት በጤናው ዘርፍ ተጠቃሽ ችግሮች ናቸው፡፡ ቢሆንም መንግስት ለዘመናት የቆዩ ችግሮችን በአንዴ ለመቅረፍ ባይችልም የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም የችግሩን ደረጃ ለመቀነስ ችሏል፡፡

መንግስት ከጤናው አንፃር የወሰዳቸው እርምጃዎች
በተለይም ኢሕአዴግ በትረ መንግስቱን እንዳተረከበ በጤናው መስክ እንደመንግስት ያጋጠመው ትልቁ ብሔራዊ አደጋ  ኤይች አይቪ ኤድስ እንደ ሰደድ እሳት እየተዛመተ መላ ሀገሪቱን ማዳረሱ ነው፡፡  ለመጀመሪያ ግዜ ኢትዮጵያ ውስጥ መግባቱ የተነገረው ወይንም አንድ ሰው በምርመራ ተገኝ የተባለው በ1976 ዓ.ም ሲሆን ደርግ ብዙም ሳይቆይ በመውደቁ ይኽ ግዙፍ መንግስታዊ ኃላፊነት በኢሕአዴግ ላይ ነው የወደቀው፡፡ በዚህ ረገድ የዓለም አቀፍ ለጋሾች እርዳታ እንደተጠበቀ ሆኖ በብሔራዊ ደረጃ የኤች አይቪ ኤድስ ፓሊሲ ማውጣት፤ ሴክረተርያት ማቋቋም፤ በጤና ጥበቃ አማካኝነት በሁሉም ክልሎች በበሽታው ምንነትና የመተላላፊያ መንገዶችን ማስተማር ማሳወቅ፤ በሚዲያው መስክ መስራት ግዙፍ አስቸካይ ተግባራት ነበሩ፡፡ የዘመቻ ስራ ማካሄድ ፤  ሴሚኖሮችን ወርክሾፓችን ማዘጋጀት፤ የበሽታው ሰለባ ለሆኑት እርዳታ መድኃኒት የሚያገኙበትን መንገድ ማበጀት፤ በወቅቱ መድኃኒት ውድ ስለነበር በመጠነኛ ዋጋ የሚገኝበትን ማቀድ መተለም በስፋት በመከላከል ላይ የተመሰረቱ ስራዎችን መስራት  ቀዳሚ ተግባሩ ሆነ፡፡

ኤች አይቪ ኤድስ በአፍሪካ ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ በመዛመቱ ኢትዮጵያ ከዚህ የተለየች አልነበረችም፡፡ ከሌሎች ሀገሮች ልምድና ተሞክሮ ለመውሰድም ጥረት ተደርጓል፡፡ ብዙ የተማሩ ወጣት ሴትና ወንዶች በበሽታው ረግፈዋል፡፡ ሕፃናት ያለአባት እናትያለአሳዳጊ፤ አሮጊትና ሽግማግሌዎች ያላጧሪ  ቀርተዋል፡፡ ኤች አይቪ ኤድስ ሁሉንም የሕብረተሰብ ክፍል አዳርሷል፡፡ በተለይም አፍላ ጉልበት ያለው ወጣት ላይ የበሽታው በፍጥነት መዛመት በአስፈሪ ሁኔታ ቀጠለ፡፡ብዙ አምራች ወጣት ኃይል፤ ተማረው አስተማሪው፤ የመንግስት  ሰራተኞ፤ ሾፌሩ፤ ገበሬው፤ ላብአደሩ፤ ወታደሩ፤ ዶክተሩ፤ ምሁሩ፤ በብዛት ረገፈ፡፡

ሀገርን ባዶ አድርጎ የሚያስቀር ትውልድን የሚያረግፍና የሚያጠፋ በሀገር ላይ የታወጀውን የኤች አይቪ ጦርነት ለመግታት መንግስት ለሊት ከቀን ሰራ፡፡ በየስፈሩ፤ በየመንዳሩ ፤ በየእድሩ በቀበሌ፤  በከፍተኛ፤ በወረዳ፤ በየመንገስት መ/ቤቱ በቅርብና ሩቅ ገጠሮች በአርሶአደሩና በአርብቶ አደሩ በአጠቃላይ በስፊው ሕዝብ ውስጥ የማስተማርና የማሳወቅ ሰፊ ስራዎችን አከናወነ፡፡

በሚዲያው በኪነት ባለሙያዎች በደራሲያን አማካኝነት በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ኮንደም በብዛት ተሰራጨ፡፡ በአነስተኛ ዋጋም ለሕዝቡ እንዲዳረስ ተደረገ፡፡ የፈቃደኝነት ምርመራ እንዲያደርግ ሕዝቡ ተበረታታ፡፡ ኤች አይቪ ፓዘቲቭ ከሆኑ አናቶች ወደ ሕፃናት እንዳይተላለፍ የሚያስችል ሕክምና ተግባራዊ ሆነ፡፡ ምርመራው በነፃ እንዲሰጥ የምስክር አገልግሎትም እንዲያገኙ ተደረገ፡፡ መገለል እንዳይደርስባቸውም ግንዛቤ  የማስጨበጥ ሰፊ ስራ  ተሰራ፡፡ በየቦታው ክበቦች ተቋቋሙ፡፡

መንግስት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ የኤች አይቪ ኤድስ ስርጭት መስፋፋትን ለመግታት ታላቅ ርብርብ አደረገ፡፡ የብሔራዊ ኤች አይቪ ኤድስ ሴክረታሪያት ፅ/ቤት ራሱ  የሚመራው በሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ ነው፡፡ በጠ/ሚሩ ጽ/ቤት የሚመራው የኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የመጨረሻውን ታላቅ ተጋድሎ አደረገ፡፡

ኢሕአዴግም እንደ ፓለቲካ ግንባር ይኽን ትውልድ ገዳይና አምራቹን ኃይል እየቀጠፈ የሚገኘውን በሽታ ለመግታት በፓለቲካ ድርጅቶች በኩል የማስተማሩ የማሳወቁ ግንዛቤ የማስጨበጡ ስራን ልዩ ትኩረት ሰጥቶት ተንቀሳቅሳል፡፡   በዚህ ታላቅ ርብርብ በአጭር ዓመታት ውስጥ በአፍሪካ ቀንድና ሆነ የኤች አይቪ ኤድስ ስርጭት አስከፊ ከሆነባቸው የሰብ ሰሀራ አገሮች ውስጥ ኢትዮጵያ ስርጭቱን በመግታት ረገድ ቀዳሚ ሀገር ሆነች፡፡ ይህ ለውጥ የመጣው ሕብረተሰብ በቂ ግንዛቤ በመጨበጡ ነው፡፡ በዚህም የተጠቂውንና የሟቾቸን ቁጥር መቀወነስ ተቻለ፡፡ መድኃኒትንም ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት ለታመሙት እንዲዳረስ ተደረገ፡፡

በኢትዮጵያ የጤና መረጃዎች ስታትስቲክስ እንደሚያሳየው ዓመታዊ የሕዝብ እድገት  ቁጥር 2.7% ሲሆን፡  አማካኝ የአንድ ሰው እድሜ 47/49 ነው፡፡ በጤናው ዘርፍ የተመዘገበው አንዱ ትልቁ ለውጥ የእናቶችንና የሕፃናትን ሞት መቀነስ መቻሉ ነው፡፡
ለዚህም በእርግዝና ወቅት ማስተማር፤ በወሊድ ወቅት የሚከሰትን ችግር በሕክምና ባለሙያ መከላከል፤ እናቶች ፈጥነው ሕክምና ወዳለበት ቦታ እንዲደርሱ በማድረግ ረገድ   በመንግስት የጤና ባለሙያዎች በሆስፒታልና በጤና ጣቢያዎች ሰፊ ትምህርት ተሰጥቷል፡፡

ሌላው በመንግስት በኩል ትኩረት  ተሰጥቶት በመላው ሀገሪቱ የተሰራውና ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበው የወባንና የሳንባ ነቀርሳ በሽታን ተላላፊነትና ስርጭት ለመግታት የተሰራው ሲሆን በዚህም ረገድ ከፍተኛ ውጤት ተመዝግቦአል፡፡ የወባ ስርጭት አለባቸው ተብለው በሚገመቱ ቦታዎች መድኃኒቱን በመርጨት ለዜጎችም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የወባ መከላከያ አጎበሮችን በነፃማደል ተችሏል፡፡ አከፋፍሏል፡፡ በተለይም የሰምጥ ሽለቆ አካባቢና በረሀ ጠቀስ ስፍራዎች ለወባ ማቆርና የመራቢያ ረግራጋማ ስፍራዎች፤  መቀፍቀፍያ ምንጭ በመሆናቸው በመድኃኒት መርጨት መቆጣጠር ተችሏል፡፡

የጤና አገልግሎትን ሩቅ በሆኑ የገጠር ቦታዎች ለማዳረስ በተዘረጋም የጠና ፓኬጅ ፕሮግራም መሠረትባለሙያዎች በተገኘው መጓጓዣ በመሄድ የገጠሩ ሕብረተሰብ  ስለጤና እንክብካቤና አጠባበቅ ስለእርግዝና፤ የወሊድ መከላከያ፤ ያለእድሜ ጋብቻ፤ በሴቶች ላይ ሰላለው ተፅዕኖ የሴቶች ግርዛት ጎጂ ባህል መሆኑን፤ ስለሽንት ቤት አጠቃቀም፤ ንፁህ ውሀ መጠቀም ለጤና ጠቃሚ መሆኑ፤ ስለኤች አይቪ ኤድስ ምንነት፤ እንዴት መከላከል እንዳለባቸው፤ የኮንዶም አጠቃቀም ግንዛቤ ሌሎችንም መሠረታዊ ትምህርቶችን ጨምሮ ለገበሬው፤ ለአርብቶ አደሩ፤በአጠቃላይ ለህዝቡ  የመንግስት የሕክምና ባለሙያዎች ሰፊ ትምህርት ሰጥተዋል፡፡ ከፍተኛ ለውጥም ተመዝግቧል፡፡ መንግስት በጤና ኤክስቴንሽን  ፕሮግራም ሕብረተሰብን ለማደረስ ሰፊ እንቅስቃሴ አድርጓል፡፡

በሀገሪቱ ያለውን ስር የስደደ የባለሙያዎች ችግር ለመፍታት በንጉሡም ሆነ በደርግ ግዜ ከነበሩት የተለየ የአስራር ዜዴ በመቀየስ፤ የግል ሆስፒታሎችና ክሊኒኮች እንዲሁም የግል የጠና ኮሌጆች በሀገሩቱ በብዛት እንዲቋቋሙና ጥራት ያለው የሕክምና ባለሙያ እንዲያፈሩ በማድረግ ሀገሪቱ ያለባትን የባለሙያ እጥረት ለመቅረፍ ብዙ ስራ ተሰርቷል፡፡
በዚህም መሠረት በመካከለኛ ደረጃ ያሉ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የሕክምና ባለሙያዎችን በማፍራት  ሕብረተሰቡን እንዲያገለግሉ ተደርጓል፡፡

የጤና ጥበቃ ባወጣው መሠረታዊ መመዘኛ መሠረት የሚቋቋሙት የግል ጤና ኮሌጆች በባለሙያም ሆነ ለተማሪዎች በሚሆኑ የመረጃ መሳሪያዎች ላብራቶሪዎችና በመሳሰሉት መሟላታቸውን፤ ተማሪዎችም በትምህርት ሚ/ር  መመዘኛ መሰረት መግባታቸውን ይቆጣጠራል፡፡ ጉድለት የተገኘባቸው እንዲያርሙ፤ ብቃት የሌላቸው ደግሞ ፈቃዳቸው እንዲሰረዝ ተደርጓል፡፡ አሁንም ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሕክምና ባለሙያ እጥረት ያለባት አገር ስትሆን በአሁኑ ጅምር በመንግስት የሕክምና ት/ቤትና ተቋማት ከሚመረቁት ውጭ በግሉ ዘርፍ ያሉትም የተመረቁትና ወደፊትም ተመርቀው ወደ ስራ ዓለም የሚስማሩት ችግሩን ለመቅረፍ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ያደረጋሉ ተብሎ ይታመናል፡፡
በኢትዮጵያ መንግስት ይዞታ ስር የሚገኙት  አብዛኛቹ የመንግስት ሆስፒታሎች ረዥም ዘመን ያገለገሉና በቂ መሳሪያም የሌላቸው፤ በሽተኞች ተኝተው የሚታከሙበት አልጋ ቁጥር ውስንነት፤ የአገልሎት ግዜያቸው የተላለፈ በመሆኑ፤ ሆስፒታሎቹን የማደስ በአዲስ መልክ የመስራትና የመገንባት የማስፋፋት ስራዎች እየተካሄዱ  ይገኛሉ፡፡

በግሉ የሕክምና ተግባር የተስማሩ ሆስፒታሎችና ክሊኒኮች ለሕክምና የሚጠይቁት ገንዘብ ከፍተኛ በመሆኑ አብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል የሚሄደው ወደ መንግስት ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች ስለሆነ እነዚሁኑ የመንግስት ሆስፒታሎችና የጤና ጣቢያዎች በፌደራልና በክልሎች ደረጃ አዳዲስ የመሰራትና የማስፋፋት በባለሙያና በመሳሪያ የማሟላት ስራዎች በመካሄድ  ላይ ናቸው፡፡ ይኸው ስራም ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

ኢትዮጵያ የሚሊኒየሙን የልማትነና የእድገት ግቦች ለማሳካት ከጀመረችውጉዞ አንፃር እንደሌሎች መስኮች ሁሉ ለጤናውም መስክ ልዩ ትኩረት ሰጥታ በመስራት አመርቂ ውጤቶች አስመዝግባለች፡፡ ጤናን ለሁሉም ለማዳረስ የተጀመረው ጥረት ወደፊትም በሰፋት ይቀጥላል፡፡ በጤናው መስክ ኢትዮጵያ ላስመዘገበቻቸው ግዙፍ እርምጃዎችና ለተገኘው መሰረታዊ ለውጥ የዓለም ጤና ድርጅት፤ ዮኔስኮ፤ የዓለም ምግብ ድርጅት፤ ሌሎችም ዓለም አቀፍ ተቋማት እውቅና ሰጥተዋታል፡ ፡ትልቅ የስኬት እርምጃም ነው፡፡