ድብድብ ነው እንዴ?

  • PDF

ከደጉ አበበ
ኢትዮጵያዊያን ትንሿ ንግስታችን ይሏታል፡፡ በቅርብ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው የስፖርት ጋዜጠኛ ደምሴ ዳምጤ ከአቦሸማኔ ጋር ያመሳስላታል፡፡ የተግባር ሰው ሲሉ ያቆላምጧታል፡፡ ብርቋ አትሌታችን ጥሩነሽ ዲባባ ገና በለጋ ዕድሜዋ ነበር በአለም የኦሎምፒክ አደባባይ የአገሯን ባንዲራ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ በማድረግ የዓለምን ህዝብ ቀልብ የገዛችው፡፡ ከውድድር በፊት ብዙ መናገር የማትፈልገው ቆራጧ አትሌታችን በለንደን ኦሎምፒክ ዋዜማ በገጠማት ህመም ምክንያት በኦሎምፒክ መሳተፍ አለመሳተፏ ህዝቡን ከዳር ዳር ነበር ያስጨነቀው ቆራጧ አትሌታችን ግን ህመሙን ችላ ለመወዳደር ስትወስን ያለችበትን ሁኔታ ለማወቅ በጥያቄ ያላፋጠጣት ሚዲያ አለ ለማለት ያስቸግራል፡፡ ከሁሉም ጥያቄዎች አትሌቷን ያስደመማት ግን የኬንያዋ ሯጭ ፉከራና ቀረርቶ ምን ይመስላል የሚለው ነበር፡፡ ጉዳዩ እንዲህ ነው ጥሩነሽ በመታመሟ ምክንያት ባገኘችው አጋጣሚ ውጤት የቀናት ኬንያዊት ስለኦሎምፒክ መግለጫ ስትሰጥ “ጥሩነሽን አልፈራትም” ድሉ የኔ ነው በማለት ነው፡፡ ታዲያ ይህች “የአልፈራትም” አባባል ለጋዜጠኞች የምትመች ነበርና ከግራና ከቀኝ ንግስቷን ማፋጠጥ ጀመሩ፡፡
የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የስፖርት ጋዜጠኛ ነበር እንዲህ ሲል ለጀግናዋ አትሌት ጥያቄ ያቀረበላት፡፡ የኬንያዋ አትሌት ቼርዬት ጥሩነሽን አልፈራትም ብላለች እንዴት ታይዋለሽ? ብርቋ አትሌታችን ቁርጥ ያለ መልስ ነበር የሰጠችው፡፡ ድብድብ ነው እንዴ? በውድድር ከሆነ ሜዳ ላይ እንገናኛለን ተግባራችን ውጤታችንን ይወስናል የሚል፡፡ በቃ ይኸው ነው የሰራ የለፋ በተግባር ያሳየ ያሸንፋል፡፡

ለዛሬው ጽሁፌ መነሻ የሆነኝ ወቅትና አጋጣሚ እየጠበቀ በአገር ውስጥ ህዝብ እንዲሸበር የተጀመረው ልማት ዴሞክራሲ ፍጥነቱን እንዲቀንስ የአገሪቱ ገፅታ እንዲበላሽ ያላሰለሰ ጥረት የሚያደርገው የአሜሪካ ሬዲዮ የአማርኛ ክፍል የባህርይ ልጆቹ ከሆኑት የመድረክ አመራሮች ጋር ያደረገው ቃለ ምልልስ አብርቄ አትሌታችን ቃለ ምልልስ ጋር ስለተመሳሰለብኝ ነው፡፡
የሬዲዮ ጣቢያው የምሽት እንግዳ የተከበሩ አቶ ተመስገን ዘውዴ ነበሩ፡፡ በተቃዋሚ ፓርቲ አመራርነታቸውና በቀድሞ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልነታቸው ህዝቡ በደንብ ያውቃቸዋል፡፡ መንግስት ሰላምን ዴሞክራሲንና ልማትን ያፋጥናል፣ ወጣቱን ሴቶችን ከጥገኝነትና ከድህነት ያላቅቃል፣ በሚል በጥናት የተደገፈ ፖሊሲ በማውጣት ለተግባራዊነቱ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን፣ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችንና ህዝቡን ያወያያል፡፡ በዚህ ጊዜ ቀድመው ፖሊሲውን በመቃወም የሚስተካከላቸው የለም፡፡ ይህ ባህርያቸው በህዝቡ ዘንድ በግልፅ ስለሚታወቅ አቶ ተመስገን ምን ብለው ይሆን? ይባልላቸዋል፡፡ ጥሩውን በመቃወም አገርንና ህዝብን የሚጎዳ ነገር በመደገፍ ይታወቃሉ፡፡ ለዚህ ይመስላል ቁጥር አንድ የሬዲዮ ጣቢያው እንግዳ በመሆን የተመረጡት ቃለ ምልልሱ የሚያተኩረው ዘንድሮ ስለሚካሄደው የአዲስ አበባ እና የአካባቢ ምርጫ ነበር አቶ ተመስገን እንዲህ በማለት ነበር፦ ንግግራቸውን የጀመሩት የመድረክ አመራር ተወዳድሮ ማሸነፍ የሚችል ስብስብ ነው፡፡ ኢህአዴግ ይህንን ስለሚያውቅ ከሌሎቹ ፓርቲዎች ጋር ሲወያይ መድረክን አግልሎታል፡፡ ለምን ቢባል ኢህአዴግ መድረክን “ስለሚፈራው” በማለት ገለፃቸውን ይደመድማሉ፡፡
እዚህ ላይ አቶ ተመስገንን መጠየቅ የምፈልገው ነገር ቢኖር ኢህአዴግ መድረክ አገለለው የሚለውን አገላለፅ ነው እኔም ሆንኩ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያውቀው መድረክ የምርጫ ስነ ምግባር ህጉን አልፈርምም ማለቱንና ራሱን ከውይይት ማግለሉን ነው፡፡ ታዲያ አነጋገርዎ ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮሃል ከሚለው ጋር አይመሳሰልብዎትም? ሌላው ስለፍራቻ ያነሱት ነው ምርጫ 2000 ያስታውሳሉ ብዬ እገምታለሁ ካስታወሱ ታዲያ ኢህአዴግ የሚፈራው ለምን ይሆን? ምንም ሳይፈጠር ሟሟረቱን ምን አመጣው፡፡ ምርጫ የሚያሸንፍ ስብስብ ፓርቲያችሁ ካለው የምርጫ ስነ ምግባሩን በመፈረም ከሌሎች ፓርቲዎች እኩል ውይይቱ ላይ ላለመካፈል ያገዳችሁ ምን ይሆን? የምርጫ ሂደቱን ጥላሸት በመቀባት መጨረሻ ላይ ብለን አልነበረም ወይ? ለማለት ከሆነ አካሄዳችሁ የተበላ ዕቁብ ነውና ካሁኑ ራሳችሁን ብታስተካክሉ፡፡ ሌላው የዚሁ ሬዲዮ ጣቢያ እንግዳ የመኢአድ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ወንድም አገኝ ደነቀ ነበሩ እሳቸው አልፎከሩም የምርጫ ህጉን ባለማወቅ ይመስለኛል ከውጭ ለጋሽ ሀገራት ነው እርዳታን የጠየቁት፡፡

እንዲህ በማለት ነበር አስገራሚ ንግግራቸውን የጀመሩት፡፡ ከምርጫው በፊት ሊመለሱ የሚገቡ ጥያቄዎችን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ጀምሮ ለፍትህ ቢሮዎች እንዲሁም ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ላደረጉት የለጋሽ አገራት ቡድን (DAG)ን ጨምሮ ለተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ብናቀርብም ውጤቱን አላየንም በመሆኑም የተጠቀሱት አካላት ጥያቄያችንን ካልመለሱ ምርጫውን ረግጠን እንወጣለን፡፡ በማለት ነበር ክስረታቸውን ሳያፍሩ የነገሩን፡፡ እዚህ ላይ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ያልተረዱት ነገር ያለ ይመስለኛል ለወደፊቱ ከጠቀማቸው አንድ ሁለት ልበልላቸው ዴሞክራሲ የአንድ ጀንበር ውጤት አይደለም በየጊዜው እየዳበረ ህዝቡ ውስጥ እየሰረፀ የሚሄድ ነው ለዚህ ደግሞ መሳካት መንግስትም ሆነ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚኖራቸው ድርሻ ትልቅ ነው፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች መጀመሪያ በውስጣቸው ድርሻ ዴሞክራሲያዊ አሰራርን በማዳበር አደረጃጀታቸውን በማጠናከር ለህዝቡ አርአያ መሆን የግድ ይላቸዋል፡፡ በመቀጠል የዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገለጫ የሆኑትን ተግባራት ለይተው በማውጣት አባላቶቻቸውን ያሰለጥናሉ ፓርቲው አመራሩና አባላቱ ራሳቸውን ካበቁ በኋላ ህዝቡ የዴሞክራሲ ስርዓት መርሆዎችን እንዲያውቅ እንዲያከብር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን አገራዊ ድርሻቸውን ይወጣሉ፡፡

በሚደረጉ ምርጫዎች ላይ በመሳተፍ ካሸነፉ አገር ይመራሉ ከተሸነፉ የመረጣቸውን ህዝብ ድምፅ ባገኙት አጋጣሚ ያሰማሉ፡፡ የገዥውን ፓርቲ ክፍተት በግልፅ በመንገር እንዲያስተካክል ይታገላሉ፡፡ በአገራዊ ጉዳዮች ላይ በሚያግባባቸው ጉዳይ አንድ በመሆን በማያምኑበት ጉዳይ ልዩነታቸውን በመያዝ ሰላማዊ ትግላቸውን ይቀጥላሉ ይህ በአለም ላይ የሚደረግ አካሄድ ነው፡፡
ምርጫ ውድድር ነው ጥሩ የሰራ ያሸንፋል ውሳኔ ሰጪው ህዝብ ነው መልሱ ከምርጫ ሳጥን በሚገኝ ውጤት ይታወቃል ከዚህ ውጭ የትኛውም አካል በአንድ ሉዓላዊ አገር የውስጥ ጉዳይ ገብቶ አይፈተፍትም፡፡ ምርጫው አገራዊ ነው ሿሚም ሻሪም የኢትዮጵያ ህዝብ ብቻ ነው፡፡ ወደ መኢአድ ምክትል ሊቀመንበር ቃለ ምልልስ ስንመጣ ግን የምናገኘው የተገላቢጦሹን ነው፡፡
የምርጫ ቦርድ አካላትን የመምረጥ፣ የስነ ምግባር ህግን የማርቀቅና የማፀደቅ፣ የምርጫ የጊዜ ሰሌዳን የማውጣት፣ አካሄዱን የመወሰን የመሳሰሉ አገራዊ ተግባራትን መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የለጋሽ አገራት ቡድንና ለተለያዩ አለም አቀፍ ድርጅቶች የመስጠት፡፡ በየትኛውም አገር ያልተሰማ ያልተደረገ አካሄድ ታዲያ እነዚህ አካላት ለጥያቄያቸው መልስ ባይሰጡ ይገርማል?

እርግጥ ነው የውጭ መንግስታት ኤምባሲዎቻቸው የለጋሽ አገራት ተወካዮችና አለም አቀፍ ድርጅቶች ምርጫውን በተመለከተ የራሳቸው አጀንዳ እንዳላቸው ይታወቃል፡፡ ሆኖም በአንድ ሉዓላዊ አገር ውስጥ ገብተው ምርጫ አስፈፃሚ መሆን እንደማይችሉ በግልፅ ያውቃሉ ለዚህ ነው መልስ የነፈጉት፡፡ ሌላው መልስ የነፈጉበት ጉዳይ ነው ብዬ የማምነው ከጥያቄያቸው አዲስ ነገር በማጣታቸው ይመስለኛል አመቱን በሙሉ በየኤምባሲዎቻቸው እየተገኙ የሚያላዝኑት ይህንኑ በመሆኑ ድክመታቸውን ተረድተውታል፡፡ እባካችሁ ተለወጡ ታደሱ አታሳፍሩን ምርጫ ህዝብን የማሳመን ጉዳይ ነው ህዝብ የሚያምነው በተግባር ነው በትክክለኛ ፖሊሲና ስትራቴጅ ነው ከዚህ ውጭ መንፈራገጥ ለመላላጥ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች የሚበጃቸውን አውቀዋል በማያዳግም መልኩ በ2000 ዓ/ም ምርጫ ውሳኔያቸውን አሳውቀዋል፡፡ ከምንም ተነስተው አይደለም የወሰኑት በተግባር ካረጋገጡት ተጠቃሚነታቸው ነው፡፡ ኢህአዴግ ባለፉት 21 ዓመታት አገሪቱ በማይታመን ሁኔታ እንድታድግ ትልቁን ሚና ተጫውቷል፡፡ ትናንት እንደሰው የማይቆጠሩ ህዝቦች የማንነት ጥያቄ በማይቀለበስ መልኩ በህገ መንግስቱ እንዲረጋገጥ አድርጓል በዚህም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በቋንቋቸው የመማር የመስራት የመዳኘት ባህላቸውን የማሳደግ የማስፋፋት በነፃነት እምነታቸውን መከተል አካባቢያቸውን የማስተዳደር በእኩልነት ከአገሪቱ ሀብት ተጠቃሚ መሆን ችለዋል፡፡

ይህ የትክክለኛ ፖሊሲ ውጤት ነው ኢህአዴግ ከህዝብ አብራክ የተገኘ ድርጅት እንደመሆኑ መጠን የህዝቡን ብሶት ችግር ስቃይ በቅርበት ያውቃል፡፡ ለዚህ ነው ትልቁ ጠላታችን ድህነት ነው ብሎ በማወጅ ህዝብን ከጎኑ ያሰለፈው፡፡ የፀረ- ድህነት ትግሉ ውጤት ነው፡፡ ዛሬ ኢህአዴግ የህዝብ ለህዝብ የቆመ እንዲባል ያደረገው፡፡ ትግሉ ከድህነት በታች የነበረውን አርሶ አደርና አርብቶ አደር ነፃ ለማድረግ ከገጠር ነበር የተጀመረው የአገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ በመረዳትና በመተንተን የትኩረት አቅጣጫን በመለየት ነበር፡፡ የተመረጠው ግብርናን ማዕከል ያደረገ የምጣኔ ሀብት ፖሊሲ ነው፡፡ ጉልበትን በብዛት በመጠቀም የአርሶ አደሩን ማሳ በዘመናዊ ግብአቶች አሟልቶ ምርታማነትን ከፍ ማድረግ፡፡ በመላ ሀገሪቱ ያሉትን አርሶ አደሮች ማዕከል ያደረገው ይኸ አሰራር በአጭር ጊዜ ውጤት በማስገኘቱ አርሶ አደሩ ራሱንና ቤተሰቡን ማስተዳደር ከመቻሉም በላይ ጥሪት ቋጥሮ ወደ ሌላ የስራ መስክ እንዲሰማራ አድርጎታል፡፡

ለዘመናት የከብት ጭራ እየተከተለ ከቦታ ቦታ ሲንከራተት ለነበረው አርብቶ አደርም ኢህአዴግ የፈፀመው ተግባር ከልቡ አይወጣም፡፡ አርብቶ አደሩ ይከተለው የነበረውን ኋላ ቀር አሰራር በመቀየር ነበር ውጤታማ ያደረገው፡፡ አርብቶ አደሩ በአንድ ቦታ ተወስኖ ብዛትን ሳይሆን ጥራትን ማዕከል ያደረገ የአረባብ ዘዴ እንዲከተል ምርታማ የሆኑ ግብአቶችን በማቅረብ ባለሙያ በአካባቢው በመመደብ ድጋፍ እንዲያገኙ አድርጓል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አርብቶ አደሩ ለምርቱ ተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ የወቅቱን የአለም ገበያ ዋጋ በቅርበት የሚከታተልበትንና ምርቱን በተገቢው ዋጋ እንዲሸጥ ስርዓት ዘርግቷል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን አርብቶ አደሩ በሚኖርበት አካባቢ ተያያዥ የእርሻ ስራዎች ላይ እንዲሳተፍ አማራጭ በማሳየት አርብቶ አደሩ ለራሱና ለቤተሰቡ የሚሆን ምርት በማምረት ከጥገኝነት እንዲላቀቅ ትልቅ ስራ ሰርቷል፡፡ የአርብቶ አደሩና አርሶ አደሩ መለወጥ የአኗኗር ዘዴውንም እንዲቀይር አስችሎታል፡፡ ጎጆ በቆርቆሮ ቤት፣ ኩራዝ በመብራት፣ መደብ በፋሚሊ አልጋና በሶፋ ተተክቷል፡፡ የጋማ ከብቶችም በመኪና የተተኩበት አካባቢ በስፋት ይታያል፡፡ ለውጥ ተጨባጭ ለውጥ የሚታይ የሚዳሰስ ለውጥ ኢህአዴግ አርሶ አደሩና አርብቶአደሩ ከሀብት ክፍፍሉ ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ተጠቃሚ እንዲሆን ልዩ ልዩ ተግባራትን ከውኗል፡፡ ለሶስት ቀበሌ አንድ ትምህርት ቤት በማቋቋም የአርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ልጆች ከአካባቢያቸው ከቤተሰባቸው ሳይርቁ ቤተሰባቸውን እየረዱ በቋንቋቸው እንዲማሩ አድርጓል፡፡ ይህ ፖሊሲ ግብርናው በተማሩ አርሶ አደሮችና አርብቶአደሮች እንዲመራ መንገዱን ከፍቷል ለግብርናው ዘርፍ በፍጥነት መለወጥም ትልቁን ድርሻ ተጫውቷል ሌላው ለኢህአዴግ የህዝቡን አመኔታ ያተረፈለት ተግባር የጤናው ዘርፍ ነው፡፡ እንኳን በገጠር በከተማም እዚህ ግባ የሚባል አደረጃጀት ያልነበረውን የህክምና ዘርፍ ስር ነቀል ለውጥ በማድረግ ህብረተሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን አድርጓል፡፡ በየገጠሩ የጤና ኬላዎችን በማቋቋም አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ጤንነቱ ተጠብቆ አምራች ዜጋ እንዲሆን አስችሎታል፡፡ ዛሬ በቃሬዛ ተሸክሞ የህክምና መስጫ መፈለግ ለገጠሩ አርሶ አደርና አርብቶ አደር ታሪክ ሆኗል፡፡

የግብርና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችን አሰልጥኖ ወደ እያንዳንዱ የገበሬ ማሳ ያሰማራው የኢህአዴግ ፖሊሲ በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠሩ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችን በማሰልጠን በእያንዳንዱ አርሶ አደርና አርብቶ አደር ጓዳ እየገባ የበሽታ መከላከል ዘዴን እያስተማረ ነው፡፡ በመሰረተ ልማት በኩልም ፖሊሲው የገጠሩን ህዝብ ማዕከል ያደረገ በመሆኑ በብዙ አካባቢዎች የመኪና መንገድ፣ የንፁህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ የመብራትና የስልክ አገልግሎት እንዲሟላ ተደርጓል ኢህአዴግ የከተማው ህብረተሰብም በእኩል ተጠቃሚ የሚሆንበትን ፖሊሲ በማውጣት ለዕድገትና ለለውጥ የቆመ ፓርቲ መሆኑን አስመስክሯል፡፡

የከተማው ኗሪ የዘመናት ጥያቄ የነበረውን የቤት አቅርቦት ጥያቄ በፍጥነት በመመለስ የህዝብ ወገን መሆኑን አሳይቷል፡፡ በከተሞች የሚካሄደውን የኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታ ጎን ለጎን ለከተማው ወጣትና ሴቶች የስራ ዕድል ከመፍጠርም ጋር በማያያዝ ውጠት አስመዝግቦበታል፡፡ ድህነትን ከከተሞች ለማጥፋት ወጣቱና ሴቶች በጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራት በማደራጀትና ከቤቶች ልማት ጋር በማስተሳሰር በአጭር ጊዜ ውስጥ ራሳቸውን በመቻል ጥሪት እንዲቋጥሩ አድርጓል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራት በካፒታል፣ በማምረቻና መሸጫ ቦታ እጥረት ወደኋላ እንዳይቀሩ የማይክሮ ፋይናንስ ድርጅቶችን በማቋቋም የብድር አቅርቦት እንዲያገኙ አድርጓል፡፡ በከተሞች ያለው የመምረቻና መሸጫ ቦታዎች ፍላጎት ሳይገድበው ማህበራቱ የሚያመርቱበትንና የሚሸጡበትን ቦታ በነፃ በመስጠት ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍሉን ተግባራዊ አድርጓል፡፡
የከተማው ነዋሪ አኗኗር ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር አብሮ እንዲራመድ አዳዲስ አሰራሮችን ተግባራዊ በማድረግ ላይ ነው፡፡ የመሰረተ ልማት ግንባታ በሁሉም አካባቢዎች እንዲዳረስ አድርጓል፡፡ የመንገድ፣ የውሃ፣ የስልክ፣ የመብራት አገልግሎት እንዲዳረስ ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን ትልቅ ተግባር ተከናውኗል፡፡
ኢህአዴግ በፈጣን ሁኔታ እያደገ የመጣውን የአገሪቱን ምጣኔ ሀብት ለማስቀጠል ወሳኙ ኃይል ህዝብ መሆኑን ይቀበላል ለዚህም በሚያወጣው እያንዳንዱ ፖሊሲ ህዝብን ያሳትፋል በመልካም አስተዳደር ዙሪያ እዚህም እዚያም የሚታዩ ግድፈቶችን ከሕብረተሰቡ ጋር በመሆን ያስተካክላል ይኸ አካሄዱ ድርጅቱን የህዝብ አመኔታ እንዲያገኝ አስችሎታል፡፡

ኢህአዴግ በህዝብ ኃያልነት ያምናል፣ ህዝቡን ያከብራል፣ ያዳምጣል፣ ተግባራዊ ምላሽም ይሰጣል፡፡ ያለ ህዝቡ ተሳትፎ አገሪቱ አንድ ስንዝር እንደማትራመድም ያውቃል ለዚህ ነው ታላቁ መሪ ታጋይ መለስ ታላቁን የህዳሴ ግድብ ግንባታ መጀመር ሲያበስሩ የምንተማመነው በህዝባችንና በሀገራችን ሀብት ብቻ ነው ያሉት ይህ በህዝብ የማመን ስሜት የእሳቸው ብቻ ሳይሆን የድርጅቱም ነው ውጤትም ተገኝቶበታል፡፡ ህዝቡ በፈጣን ሁኔታ እያደገ የመጣው የአገሪቱ ምጣኔ ሀብት ተቀባይነታችንን፣ ተሰሚነታችንን፣ ገፅታችንን፣ እየቀየረው መምጣቱን ተገንዘቧል፡፡ ለዚህም የድርሻውን ለመወጣት ቃል ገብቷል ይህንንም የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ባረፉበት ወቅት አሳይቷል፡፡ ህዝብና መንግስት ህዝብና ኢህአዴግ አንድ ሆነዋል፡፡ አገሪቱን አንድ ሆነን እናሳድጋለን ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በጊዜ የለኝም መርህ ተመርተው ድህነትን ታሪክ ለማድረግ አንድነታቸውን ከምን ጊዜውም በበለጠ ሁኔታ አጠናክረዋል፡፡ ጊዜው የተግባር ነው ታግሎ ያታገለ መርቶ ድህነትን ያሻገረ ፓርቲ ተመራጭ የሆነበት፡፡
በአሁኑ ሰዓት ዓለም በምጣኔ ሀብት ቀውስ ውስጥ ተዘፍቃ ዜጎች የመኖር ህልውናቸው ጥያቄ ውስጥ ገብቷል፡፡ ዜጎች ሌት ተቀን በሰላማዊ ሰልፍ መንገዶቻቸውን እያጨናነቁ ነው፡፡
አገራቸውን ከውድቀት ህዝባቸውን ከችግር ማውጣት ያልቻሉ ፓርቲዎችና መሪዎቻቸው አልቻልንም ብለው ስልጣናቸውን እያስረከቡ ነው፡፡ ይህ ዕውነታ ለኢትዮጵያ ህዝብ መንግስትና ተቃዋሚ ፓርቲዎች ግልፅ ነው፡፡ የሰራ የለፋ ትክክለኛ አቅጣጫን ይዞ የሚጓዝ ህዝብና መንግስት ተመራጭና ውጤታማ መሆኑን፡፡ ያልሰራ በወሬና በአሉባልታ የሚነዳ በውጭ መንግስታት ላይ ጥገኛ የሆነ አገርንና ህዝብን የሚንቅ ፓርቲ ጥግ መያዙን፡፡ ለዚህ ነው ብርቋ አትሌታችን ውድድር የፍርሃት ሳይሆን የተግባር ውጤት ነው የተዘጋጀ የጨዋታውን ህግ ያወቀ በራሱ የተማመነ ተወዳዳሪ ያሸንፋል ሜዳውም ፈረሱም ይኸው በማለት በለንደን ኦሎምፒክ አለምን ባስደነቀ መልኩ ተፎካካሪዋን ድል በመንሳት የወርቅ አክሊል ያጠለቀችው፡፡ ውጤት የከባድ ስራ ሽልማት ነው በተግባር እንመን፡፡ መጪውን የአካባቢና የአዲስ አበባ ምርጫ በሰለጠነ አኳኋን እንወዳደር፡፡ ህዝቡ ይወስን፡፡ ተግባር ይወስን፡፡    ቸር እንሰንብት፡፡