ኮሚሽኑ በምሥራቃዊ የኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ገለልተኛ ሰላም አስከባሪ በሚሰማራበት ሁኔታ ላይ መከረ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 22/2005 (ዋኢማ) -  የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን በምሥራቃዊ የኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ገለልተኛ ሰላም አስከባሪ በሚሰማራበት ሁኔታ ላይ አዲስ አበባ ውስጥ መከረ።

በኮሚሽኑ የሰላምና ጸጥታ ኮሚሽነር አምባሳደር ራምታኔ ላማምራ ሰብሳቢነት በዚህ ሳምንት የተካሄደው ስብሰባ በአካባቢው ገለልተኛ የሆነ ዓለም አቀፍ ሰላም አስከባሪ ሠራዊት እንዲሰማራ በታላላቅ ሃይቆች አገሮችና በአፍሪካ ኅብረት የተደረሰበትን ስምምነት ተቀብሎታል።

በተለይም በአገሪቱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ካሰማራው ሰላም አስከባሪ ሠራዊት ለብቻው ተነጥሎ የሚሰራ ወይም በጋራ ተቀናጅቶ ይስራ የሚሉትን አማራጮችም ስብሰባው ተመልክቷቸዋል።

በተለይም በተቀናጀ መልኩ የሚከናወነውን እንቅስቃሴ በፋይናንስና በሎጂስቲክ ለማጠናከር አለበለዚያም የአፍሪካ ኅብረት ሰላምና ጸጥታ ኮሚሽን አካል ሆኖ እንዲዋቀር የሚሉትን ጉዳዮች ማጤኑን ኮሚሽኑ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የላከው መግለጫ ያመለክታል።

የስብሰባው ተሳታፊዎች ኮሚሽኑ ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት በሚኒስትሮች ደረጃ የሚሳተፉበት ስብሰባ ታኅሣሥ 30 ቀን 2005 እንዲጠራ ጠይቀዋል።በዚህም ለችግሩ ያሉት አማራጮች የሚታዩበትና ተጨባጭ የሚሆኑ ውሳኔዎች እንደሚተላለፉበት እምነታቸውን ገልጸዋል።

የዑጋንዳ የመከላከያ ሚኒስትር ዶክተር ክሪስፐስ ኪዮንጋ በኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ መንግሥትና በአማጺው የኤም 23 ቡድን መካከል በካምፓላ የተደረገው ድርድር ላይ ገለጻ አድርገዋል።ተሳታፊዎች ለድርድሩ ያላቸውን ድጋፍ የገለጹ ሲሆን፣ድርድሩ ፈጥኖ እንዲጠናቀቅ ፍላጎታቸው መሆኑን ተናግረዋል።

እንደ ኢዜአ ዘገባ ስብሰባው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና በአካባቢው አገሮች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማሻሻል ጠቀሜታው ከፍተኛ መሆኑንም ገልጿል።

በስብሰባው ላይ የአካባቢው አገሮችና ሌሎች የአፍሪካ ኅብረት አባል አገሮች፣አህጉራዊ ድርጅቶች፣የአፍሪካ ኅብረት አጋሮች ተሳትፈዋል። ስብሰባው የተጠራው ኮሚሽኑ በአገሪቱ ወቅታዊ ጉዳይ አስቸኳይ ስብሰባ እንዲጠራ ታኅሣሥ 1 ቀን ባስተላለፈው ጥሪ መሠረት መሆኑንም ኢዜአ አስታውሷል።