ለዋልያዎቹ የማበረታቻ ሽልማት ተበረከተላቸው

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 17/2005(ዋኢማ) - ለ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የእግር ኳስ ውድድር ተካፋይ ለሆነው የኢትዮጵያ ብሄራዊ የእግር ኳስ ቡድን ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሽልማት ተበረከተለት።

ከ31 አመታት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ለበቁት ዋልያዎቹ ትናንት በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል በመደበኛነት ሁሉንም ለተጫወቱ፣ የተወሰነ ለተጫወቱና በተቀያሪነት ለተሰለፉ እንዲሁም በቡድኑ ውስጥ ለተካተቱ ተጫዋቾች እንደየአገልግሎታቸው ሽልማቱ ተበረክቶላቸዋል።

በዚህ መሰረት የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው 280 ሺ ብር ግምት ያላት ሊፋን አውቶሞቢል ሲሸለሙ፥ ምክትል አሰልጣኝ ስዩም ከበደ 150 ሺ ብር፣ የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ ቅጣው ሙሉ 100 ሺ ብር ፣ የቡድኑ ወጌሻ አቶ ይስሃቅ ሽፈራው 100 ሺ ብር ተሸልመዋል።

የቡድኑ የህክምና ባለሙያ ዶክተር ተረፈ ጣፋ 50 ሺ ብር፣  የቡድን መሪዎች አቶ አፈወርቅ አየለ እና አቶ አሊሚራ መሃመድ እያንዳንዳቸው 25 ሺ ብር፣ የቡድኑ ማናጀር አቶ አበረ ሃብቴ 10 ሺ ብር፣ የቡድኑ የስነ-ምግብ ባለሙያ አቶ ተስፋየ ብርሃኔ 15 ሺ ብር፣ የቡድኑ ስነ ልቦና ባለሙያ አቶ እንዳልክ አሰፋ 15 ሺ ብር እንዲሁም የቡድኑ ሾፌር አቶ ዘውዱ ፋንታየ የ5 ሺ ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

በተጫዋቾች በመጀመሪያው መስፈርትና አንድ ጎል ላስቆጠረ ተጫዋቾች የሚሰጠውን 10ሺ ብር ጨምሮ አዳነ ግርማ 130 ሺ ብር ሲያገኝ፥ ጌታነህ ከበደና ስዩም ተስፋዬ እያንዳንዳቸው 110ሺ ብር ተበርክቶላቸዋል።

ቢያድግልኝ ኤልያስ፣ ምንያህል ተሾመ፣ አስራት መገርሳ፣ አዲስ ህንጻ፣ አበባው ቡጣቆ፣ ሲሳይ ባንጫ፣ ብርሃኑ ቦጋለ እና አሉላ ግርማ እያንዳንዳቸው የ100 ሺ ብር ተሸላሚ ሆነዋል።
ሳልሃዲን ሰኢድ በሁለተኛው መስፈርት እና አንድ ጎል ላስቆጠረ የሚበረከተውን የ10ሺ ብር ሽልማት ጨምሮ፥ 90 ሺ ብር ሲሸለም፣ በሃይሉ አሰፋ፣ አይናለም ሃይሉ፣ ኡመዱ ኡክሪ፣ ሽመልስ በቀለ እና ጀማል ጣሰው እያንዳንዳቸው የ80 ሺ ብር ተሸላሚዎች ሆነዋል።

ፍጹም ገብረማርያም፣ ደረጀ አለሙ፣ ፍጹም ተፈራ፣ ሙሉአለም መስፍን፣ መድሃኔ ታደሰ፣ ዘሪሁን ታደሰ፣ ዳዊት እስጢፋኖስ፣ ያሬድ ዝናቡና አክሊሉ አየነው፤ እያንዳንዳቸው የ50 ሺ ብር ተሸላሚዎች መሆናቸውን የኤፍቢሲ ዘገባ ያመለክታል።