የሊቢያ ወታደራዊ ፍርድ ቤት ምራመራውን አቋረጠ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 17/2005(ዋኢማ) - እ.አ.አ በ2011 በቀድሞው የሊቢያ መሪ ኮሎኔል ሙአማር ጋዳፊ መንግሥት ላይ የአመፅ እንቅስቃሴ በተጀመረበት ወቅት መንግሥቱን ከድተው አመፁን በተቀላቀሉ የቀድሞ ወታደራዊ ባለሥልጣን ግድያ እንዲያጣራ የተሰየመው ወታደራዊ ልዩ ፍርድ ቤት ሥራውን ያቋረጠ መሆኑን አስታውቋል።

ወታደራዊ ፍርድ ቤቱ ምርመራውን ለማቋረጥ የተገደደው ምርመራው በለውጥ እንቅስቃሴው ሂደት የተመሠረተውን ብሔራዊ የሽግግር ምክር ቤት ሊቀመንበር በመሆን ያገለገሉት ሙስጠፋ አብደል ጃሊል ቀርበው ቃል እንዲሰጡ ማድረጉ ባስከተለው ተቃውሞ ምክንያት እንደሆነ የቢቢሲ ዘገባ አመልክቷል።

ከዚህ ተቃውሞ በመነሳት ወታደራዊ ፍርድ ቤቱ ባለፈው ዓመት የአመፅ እንቅስቃሴውን የተቀላቀሉትን ጀኔራል አብዶል ፋታህ ዩኔኮን ግድያ የሚመለከተውን ጉዳይ ለወታደራዊው አቃቤ ሕግ በመመለስ ምርመራውን አቋርጧል።

በወታደራዊ ፍርድ ቤቱ ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ የተቀሰቀሰው የቀድሞው የሽግግር ብሔራዊ ምክር ቤት ሊቀመንበር ሙስጠፋ አብደል ሻሊል ትሪፖሊ ውስጥ ቃል ለመስጠት በወታደራዊ ፍርድ ቤቱ ዳኞች ፊት ሲቀርቡ ከዳኞች መካከል አንዱ በጣት የድል አድራጊነት ምልክት በማሳየታቸው ምክንያት እንደሆነም የቢቢሲ ዘገባ ጨምሮ ገልጿል።

ኮሎኔል ሙአማር ጋዳፊ እ.አ.አ በ1969 በወታደራዊ መፈንቅለ-መንግሥት ሥልጣን ሲይዙ ከአጋሮቻቸው መካከል አንዱ እንደነበሩ የተነገረላቸው ጀኔራል አብደል ፋታህ ዩኔስ ከቤንጋዚ ከተማ በተጀመረው የአመፅ እንቅስቃሴ ሂደት መንግሥቱን ከድተው አመጹን ቢቀላቀሉም በአንዳንድ ወገኖች ዘንድ በጥርጣሬ መታየታቸው አልቀረም።

በሙአማር ጋዳፊ መንግሥት ውስጥ የአገር አስተዳደር ሚኒስትርነት የሠሩት ጀኔራል አብደል ፋታህ ዩኔስ ባለፈው ዓመት መጋቢት ውስጥ በኮሎኔል ሙአማር ጋፋፊ አገዛዝ ላይ የአመፅ እንቅስቃሴ ሲጀመር የአመፁን ጐራ ለመቀላቀል ከፍተኛው የመንግሥት ባለሥልጣን እንደነበሩ ተገልጿል። ከጥቂት ወራት በኋላ ባልታወቀ ሁኔታ ቤንጋዚ ውስጥ ተገድለዋል። ከመገደላቸው ቀደም ሲል ውጊያ ይመሩባት ከነበረችው ብሬጋ ከተማ ወደቤንጋዚ መጠራ ታቸው ታውቋል።

ግድያውን ተከትሎ ጊዜያዊ የሽግግር ብሔራዊ ምክር ቤቱን ሊቀመንበር ሙስጠፋ አብደል ጃሊልን ጨምሮ በበርካታ ባለሥልጣኖች ጉዳዩን በሚመለከት የተለያዩ መግለጫዎች መሰጠታቸው ታውቋል። የግድያውን ሁኔታ ለማጣራት ወታደራዊ ልዩ ፍርድ ቤት ተቋቁሞ ሴራ ቢጀምርም በተጠቀሰው ተቃውሞ ምክንያት ሥራውን ለማቆም ተገድዷል።

በጀኔራል አብደል ፋታህ ዩኔስ ግድያ እስካሁን 11 ሰዎች ቢጠረጠሩም ከእነዚህ መካከል ግድያውን ፈጽሟል በተባለ አንድ ተጠርጣሪ ላይ ብቻ ክስ መመሥረቱ ታውቋል። ግለሰቡ በቁጥጥር ሥር እንደሆነም ተገልጿል።

እንደ አዲስ ዘመን ዘገባ በዚህ ዓመት መግቢያ ላይ የጀኔራለ አብደል ፋታህ ዩኔስን ግድያ በሚመለከት ምርመራ ያካሂዱ የነበሩ አንድ ዳኛ ቤንጋዚ ውስጥ ወደመስጊድ በመጓዝ ላይ እንደነበሩ ባልታወቀ ሁኔታ መገደላቸው ታውቋል።