በሐፍያ ከተማ ድብደባ መንግሥትና ታጣቂ ቡድኖች ተወነጃጀሉ

  • PDF

አዲስ አባባ፤ ታህሳስ 17/2005 (ዋኢማ) - ሃያ ወራትን ባስቆጠረው የሶሪያ የእርስ በርስ ጦርነት ሂደት በከተሞች ላይ ከተፈፀሙት ከፍተኛ የጥቃት እርምጃዎች መካከል አንዱ እንደሆነ የተነገረለት ጥቃት ከትናንት በስቲያ ሐፍያ በተባለችውና ሀማ በተባለው በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍለ ሀገር በምትገኘው ከተማ ላይ መፈፀሙን የተለያዩ የዜና ምንጮች አስታውቀዋል። ተቃዋሚ ታጣቂ ኃይሎች በተለይም ነፃው ጦር ሠራዊት (ፍሪ – አርሚ) በሚል ስም የሚታወቀው ተዋጊ ኃይል የሐፍያ ከተማ በመንግሥቱ አየር ኃይል ተዋጊ አውሮፕላኖች በቦምብ መደብደቧን ሲያመለክቱ መንግሥቱ ደግሞ ከተማዋ በከባድ መሣሪያ የተደበደበችው በአሸባሪ ቡድኖች እንደሆነ ማመልከቱ ተገልጿል። በከተማዋ ላይ በተፈፀመው ጥቃት ከፍተኛ የሕይወትና የንብረት ጥፋት መድረሱንም ዘገባዎች ጨምረው ገልጸዋል።

ዘገባዎች የተቃዋሚ ኃይሎችን ምንጮች በመጥቀስ እንዳመለከቱት የሐፍያ ከተማ በመንግሥቱ አየር ኃይል ተዋጊ አውሮፕላኖች ከትናንት በስቲያ የተደበደበችው ሙሉ በሙሉ በተቃዋሚ ታጣቂ ቡድኖች በተለይም በነፃው ጦር ሠራዊት ቁጥጥር ስር መዋሏ ከተነገረ በኋላ ነው።

በሐፍያ ከተማ አቅራቢያ የሚገኝ አንድ ከፍተኛ የመንግሥቱ ጦር ሠፈር በተቃዋሚ ታጣቂ ኃይሎች ለመያዝ መቃረቡ ተገልጿል። የጦር ሠፈሩ ከፍተኛ የጦር መሣሪያ ክምችት የሚገኝበት ከመሆኑ አኳያ በታጣቂዎች እጅ መግባቱ በመሣሪያ በኩል አቅማቸውን ለማሳደግ አመቺ ሁኔታ እንደሚፈጥር ዘገባዎች ጨምረው ገልጸዋል።

ኮሶሪያ መንግሥት በኩል የተሰራጨ ደግሞ የውጭ ተዋጊዎች ጭምር የተቀላቀሉባቸው ታጣቂ አሸባሪ ቡድኖች ቢጫ መልክ ባላቸው ቦምቦች ወይም የኬሚካል መሣሪያዎች በመንግሥት ጦር ኃይል አባሎች ላይ ተኩሰዋል። ይህም የእርስበርስ ጦርነቱን ገፅታ ሊለወጥ እንደሚችል ማስጋቱ ታውቋል። ቀደም ሲል መንግሥቱና ተቃዋሚ ታጣቂ ቡድኖች ሕዝብን በብዛት ሊፈጁ የሚችሉ የኬሚካል የጦር መሣሪያዎች ሊጠቀሙ እንደሚችሉ በማመልከት አንደኛው ሌላውን መወንጀሉ ይታወሳል።

በተለይም ፕሬዚዳንት ባሻር አልአሳድ ኬሚካል የጦር መሣሪያዎችን «አሸባሪዎችን ለማጥቃት» በሚል ሽፋን በሕዝብ ላይ ለመጠቀም ቢሞክሩ ዋጋ እንደሚከፍሉ ሊያውቁ እንደሚገባ በቅርቡ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል። በሁለቱም ወገኖች በኩል በኬሚካል ጦር መሣሪያ የመጠቀም አዝማሚያ እንዳለ በሚገለጽበት ወቅት የእርስ በርስ ጦርነት በአደገኛ ሁኔታ እንደቀጠለ መሆኑን ዘገባዎች አረጋግጠዋል። ባለፈው እሁድ በመላ አገሪቱ በተካሄደው ጦርነት የ150 ሰዎች ሕይወት መጥፋቱን ዘገባዎች ገልጸዋል።

አሸናፊና ተሸናፊውን ለመለየት በማይቻልበት ሁኔታ የእርስ በርስ ጦርነቱ በቀጠለበት ወቅት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና የዓረብ ሊግ የሶሪያ ጉዳይ ልዩ መልዕክተኛ ከትናንት በስቲያ በሊባኖስ በኩል ወደሶሪያ መግባታቸው ተገልጿል።

አልጀሪያዊው የቀድሞ ዲፕሎማት ላክዳር ብራሂሚ ተልዕኳቸውን በሚመለከት በሰጡት አስተያየት፤ በተፋላሚ ኃይሎች ዘንድ የእርስ በርስ ጦርነቱን የማቆም ፍላጐት ያለ መስሎ ባይታይም ጦርነቱ ከደረሰበት አደገኛ ሁኔታ አኳያ ተኩስ የሚቆምበትና በሁሉም ኃይሎች መካከል የፖለቲካ ውይይት የሚከፈትበትን መንገድ ማፈላለግ መቋረጥ እንደማይኖርበት ማመልከታቸው ተገልጿል። የአሁኑ የሶሪያ ተልዕኮዋቸውም በእዚህ ላይ የተመሠረተ እንደሆነ ገልጸዋል።

ላክዳር ብራሂሚ ከእዚህ ቀደም በሶሪያ ውስጥ ጉዳዩ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከሚመለከታቸው አገሮች ባለሥልጣኖች ጋር ጦርነቱ በሚቆምበት ሁኔታ ላይ ውይይት ቢያካሄዱም ውጤት እንዳልተገኘ ይታወቃል።

ልዩ መልዕክተኛ ላክዳር ብራሂሚ አሸናፊና ተሸናፊውን ለመለየት አስቸጋሪ በሆኑበት ሁኔታ በመካሄድ ላይ የሚገኘው የእርስ በርስ ጦርነት እልባት ሊያገኝ የሚችለው በተፋላሚ ኃይሎች መካከል በሚደረግ የተኩስ ስምምነትና የፖለቲካ ውይይት እንደሆነ እንደሚታመን በተደጋጋሚ ገልጸዋል። እስከአሁን ግን ይህን የሚያመለክት ፍንጭ አልታየም።

በሶሪያ ጉዳይ ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ በተለይም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ፀጥታ ምክር ቤት ቋሚ አባሎች (አሜሪካ፣ ሩሲያ፣ ቻይና፣ ብሪታኒያና ፈረንሳይ) የሶሪያ ጦርነት በሚቆምበት መንገድ ላይ አንድ አቋም ለመያዝ አለመቻላቸው ለጦርነቱ መቀጠል ድርሻ እንዳበረከተ ተገምቷል። የፕሬዚዳንት ባሻር አልአሳድ መንግሥት በከተሞች ሕዝብ ላይ በከባድ ጦር መሣሪያዎች በታገዘ ጦር ኃይል መጠቀሙን የሚያወግዝ ውሳኔዎች ሁለት ጊዜያት ተላልፈው ውሳኔን በድምፅ የመሻር ሥልጣን ባላቸው ሩሲያና ቻይና ውድቅ መደረጋቸው ይታወቃል።

እንደ አዲስ ዘመን ዘገባ ከተጀመረ ሃያ አንድ ወራት በሆነው የሶሪያ የእርስ በርስ ጦርነት ሂደት ከ44,000 በላይ ሕዝብ ሕይወት እንደጠፋ ሲገመት፤ የተሰደደው ሕዝብም ከ700,000 እንደሚበልጥ ታውቋል። ጦርነቱ በአገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ ማኅበራዊ ቀውስ ያደረሰና በማድረስም ላይ እንደሆነ ተገልጿል።