ከመስቀል አደባባይ ቦሌ አየር መንገድ ግንባታ በመፋጠን ላይ መሆኑ ተገለፀ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 16 (ዋኢማ) - ከመስቀል አደባባይ እስከ ቦሌ አየር መንገድ በመገንባት ላይ ያለው መንገድ ግንባታ ለአፍሪካ ህብረት 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዮ ክብረ በዓል ለማድረስ የተፋጠነ ስራ በመከናወን ላይ መሆኑን የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን አስታወቀ።

የባለስልጣኑ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ፍቃደ ሀይለስላሴ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት፤ የመንገዱ ግንባታ በጥር ወር 2004 ዓ.ም ሲጀመር በሁለት ዓመት ከግማሽ ስራውን ለማጠናቀቅ የታቅደ ቢሆንም የመንገዱን አብዛኛውን ክፍል የአፍሪካ ህብረት 50ኛ ዓመት ክብረ በዓል በአዲስ አበባ በሚከበርበት ግንቦት ወር 2005 ዓ.ም ለማጠናቀቅ 24 ሰዓት ስራው እየተከናወነ ነው።

መጀመሪያ ከተቀመጠው ግብ አንፃር የመንገዱ ግንባታ ሂደት በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑን የገለፁት ስራ አስኪያጁ ፕሮጀክቱ ተፋጥኖ የመንገዱ ዋና ዋና ስራዎችን ለአፍሪካ ህብረት ክብረ በዓል ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ይህም ለሃገሪቱ የገፅታ ግንባታ ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ኢንጂነር ፍቃደ ተናግረው፤ በ60 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወጪ በመገንባት ላይ ያለውና 4 ነጥብ 3 ኪሎ ሜትር ርዝመት እንዲሁም 40 ሜትር ስፋት የሚኖረው መንገድ ግንባታ ስራ በአምስት ክፍል ተከፍሎ በመከናወን ላይ ይገኛል።

ለትራፊክ አመቺነት ሲባል ስራው ሲጀመር የመንገዱ አንደኛው ክፍል ግንባታ ከተጠናቀቀ በኋላ የሌላኛው ክፍል ግንባታ ሲከናወን የቆየ ቢሆንም መንገዱን በቶሎ ለማጠናቀቅ ሲባል የስራ ተቋራጩ ሳይገደብ በሁሉም ክፍሎች ላይ ስራዎቹን በፍጥነት እንዲያከናውን መፈቀዱን ስራ አስኪያጁ ተናግረዋል።

ከመስቀል አደባባይ እስከ ፍላሚንጎ ያለው ክፍል በቅርቡ እንደሚጀመር የተናገሩት ኢንጂነር ፍቃደ ስራው እየተጠናቀቀ ያለው ከፍሬንድሺፕ እስከ ካራማራ ያለው ክፍል በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለትራፊክ ክፍት ይሆናል ብለዋል።

የመሬት ውስጥ መተላለፊያን የሚያካትተው የካራማራ ወሎ ሰፈርና ቦሌ ማተሚያ አካባቢ መንገድ ሙሉ በሙሉ ተዘግቶ ግንባታውን ባፋጣኝ አከናውኖ ለመጨረስ እንደሚሰራ ኢንጂነር ፍቃደ አክለው ገልፀዋል።

የቦሌ መንገድ ግንባታን ጨምሮ በከተማው እየተከናወኑ ያሉ የመንገድ ግንባታዎች በህብረተሰቡ ላይ ጫና በማሳደር ላይ መሆኑን የገለፁት ኢነጂነር ፍቃደ ጫናውን ለማቃለል ባለስልጣኑ በከተማው የትራፊክ አስተዳደር ጥናት በማከናወን ላይ ነው በማለት  ተናግረዋል።