ለተፋሰስ ልማቱ የመሳሪያ አቅርቦትና ስልጠና በመከናወን ላይ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 16/2005 (ዋኢማ) -   በቀጣዩ ወር ለሚጀመረው የተፋሰስ ልማት የመሳሪያ አቅርቦትና ስልጠና በመከናወን ላይ መሆኑን ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ::
ባለፉት አመታት በኢትዮÉያ በሚሊዮኖች ሄክታር የሚገመት መሬት ላይ የተለያዩ የአፈርና ውሃ መጠበቂያ ስራዎች የተከናወኑ ሲሆን በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞችም ተተክለዋል::

የአካባቢ ጥበቃ ሰራው እንደየአካባቢው ሁኔታ ቢለያይም የመስኖ ልማትን ጨምሮ ለግብርናው ምርታማነት ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ ነው፡፡

በግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም ዳይሬክቶሬት ምክትል ዳይሬክተር አቶ ተፈራ ታደሰ እንዳሉት በተያዘው አመት የበጋ ወራት በትግራይ፣ አማራ፣ ኦሮሚያና ደቡብ ክልሎች ብቻ 6 ሚሊዮን ሄክታር የሚጠጋ መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ይከናወናል::

እንደ ኢዜአ ዘገባ ባለፈው አመት የታየውን የአመለካከትና ለችግኝ የሚደረግ እንክብካቤ ክፍተት እንዲሁም በእርከን ስራ የሚስተዋሉ የጥራት ችግሮችን ለመሙላትም ከባለሙያ እስከ አርሶ አደር የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በየደረጃው እየተሰጠ ነው፡፡ ለስራው የሚያስፈልጉ መሳሪያዎች ለየክልሎቹ መከፋፈላቸውንም ምክትል ዳይሬክተሩ ተናግረዋል::

እንደ ሚኒስቴሩ መረጃ በዚህ አመት በአራቱ ክልሎች ሰባት ሚሊዮን ሄክታር የተራቆተ መሬት ከሰው እና እንስሳት ንክኪ ነጻ ይደረጋል:: የተፋሰስ ልማቱም በቀጣዩ ወር ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል::