በይልማና ዴንሳ ወረዳ በእንስሳት ማድለብ ስራ የሚሳተፉ አርሶ አደሮች ቁጥር እያደገ ነው

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ታሀሳስ 15/2005 (ዋኢማ) - በምዕራብ ጎጃም ዞን በይልማና ዴንሳ ወረዳ በእንስሳት ማድለብ ስራ የሚሳተፉ አርሶ አደሮች ቁጥር በየአመቱ እያደገ መምጣቱን የወረዳው ግብርና ጽህፈት ቤት ገለጸ። በያዝነው ዓመት አርሶ አደሮቹ 63 ሺህ እንስሳት አድልበው ለገበያ ለማቅረብ ታቅዶ እየሰሩ ነው፡፡

የጽህፈት ቤቱ የእንስሳት ሃብት ልማት ማስፋፊያ የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ቢያዝን አየለ ሰሞኑን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት በወረዳው አርሶ አደሩ ከሚያደልባቸው እንስሳት በሚያገኘው ገቢ ኑሮውን እያሻሻለ ነው።

በያዝነው ዓመት ከ37ሺህ የሚበልጡ አርሶ አደሮች 63 ሺህ እንስሳት አድልበው ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል ጽህፈት ቤቱ አቅዶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ባለፉት አምስት ወራት ከ19 ሺህ የሚበልጡ እንስሳት ደልበው ለገበያ ሲቀርቡ በቀሪው በጀት ዓመት በዕቅድ የተያዙ እንስሳትን አርሶ አደሩ አድልቦ ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ እንዲሆን ባለሙያውና አመራሩ ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

በዓመቱ ይደልባል ተብሎ የሚጠበቀው እንስሳት ከቀዳሚው ዓመት ከአራት ሺህ በላይ ብልጫ እንዳለው አመልክተው በዓመቱ ከሚደልቡት እንስሳት መካከል ከ26ሺህ የሚበልጡ የዳልጋ ከብቶች መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ በወረዳው እንስሳት ማድለብ ስራ እየተሳተፉ የሚገኙ አርሶ አደሮች በበኩላቸው እንስሳት ማድለብ ከጀመሩ ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ እስከ 10ሺህ ብር የተጣራ ትርፍ በማግኘት ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን ገልጸዋል፡፡

እንደ ኢዜአ ዘገባ የማድለብ ስራውን ይበልጥ አስፋፍተው በመቀጠል በሚያገኙት ተጨማሪ ገቢ ተጠቃሚ መሆን የሚያስችላቸውን ስራ ከወዲሁ እየሰሩ እንደሚገኙ አርሶ አደሮቹ አስረድተዋል፡፡ ባለፈው ዓመት በወረዳው በእንስሳት ማድለብ ስራ የተሳተፉ ከ35ሺህ 600 የሚበልጡ አርሶ አደሮች አድልበው ለገበያ ካቀረቧቸው እንስሳት ከ71 ሚሊዮን ብር በላይ የተጣራ ትርፍ በማግኘት ተጠቃሚ መሆናቸውንም ገልጿል፡፡