በሕጻናት ጉዳይ ላይ የሚመክር አውደ ጥናት በአዳማ ተካሄደ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ታሀሳስ 15/2005 (ዋኢማ) - በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሕጻናት ከቤተሰቦቻቸው ጋር ተመልሰው እንዲገናኙ የማፈላለግ አሳራር እየዘረጋ መሆኑን የሴቶች ሕጻነትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስቴሩ በሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ክስተት ወላጆቻቸውን በማጣት ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ የተጋለጡ ህጻናትን መታደግ የሚያስችለው መልሶ መቋቋምና ከቤተሰቦቻቸው ጋር የማገናኘት ስራዎችን ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ለማከናወን የሚያስችል የምክክር መድረክ ትናንት በአዳማ ከተማ አካሂዷል። በምክክር መድረኩ ላይ ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዘነቡ ታደሰ እንደገለጹት መንግስት ለህጻናት ልዩ ትኩረት በመስጠት መብትና ደህንነታቸው እንዲጠበቅ እስከ ቀበሌ ድረስ የክብካቤ ፕሮግራም በመቅረጽ ችግራቸውን የሚፈታ ስራ እየሰራ ነው።

አማራጭ የሌላቸውንና በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ የሚገኙ ህጻነትን ለመታደግ ማሳደጊያ ውስጥ ገብተው ክብካቤ እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን ገልጸው የሕጻናቱን ቤተሰቦች በማፈላለግ በተወለዱበት አካባቢ ተቀላቅለው እንዲያድጉ እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል። ወላጆቻቸው በህይወት የማይኖሩ ከሆነም ህጻናቱ በማህበረሰብ ድጋፍና ክብከቤ የሚያድጉበት ሁኔታ ላይ መድረኩ እንደሚመክር ገልጸዋል።

እንደ ኢዜአ ዘገባ በምክክር መድረኩ ላይ ከሀይማኖት ተቋማት፣ ከፍትህ፣መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ተሳትፋወል።