የኦዲት ተቋማትን አቅም ማጠናከር ለተጀመረው ልማት ስኬታማነት ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ታሀሳስ 15/2005 (ዋኢማ) - በኢትዮጵያ የተጀመረውን ሰፊ የልማት እንቅስቃሴ ስኬታማ ለማድረግና ተጠያቂነት በተሞላበት መልኩ ለመፈጸም የኦዲት ተቋማት አቅም ማጠናከር እንደሚገባ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስገነዘበ፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪን ለመቆጣጠር የሚያካሂደውን የክትትልና የቁጥጥር ሥራ ይበልጥ ለማቀላጠፍ የሚያስችል ሥልጠና ለምክር ቤቱ አባላት ትናንት በሶዶሬ ሰጥቷል፡፡

የምክር ቤቱ የመንግሥት ወጪ አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ስብሳቢ አቶ ግርማ ሰይፉ ሥልጠናው በንግግር ሲከፍቱ እንዳሉት ምክር ቤቱ የመንግሥትን ወጪ ለመቀጣጠር ከሚጠቀምባቸው ግብዓቶች አንዱ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የሚያመነጨው የኦዲት መረጃ በመሆኑ የተቋሙን ነፃነትና አቅም ማጎልበት ይገባል፡፡

የአገሪቱ ዋና ኦዲተር ነፃ ሆኖ ከመሥራት አኳያ ከሌሎች አገሮች የተሻለ መሆኑን ጠቁመው በተለይ ተቋሙ አገሪቱ ከምታካሂደው የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥርዓት አንፃር ተጠያቂነትን በማጠናከር ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑ አመልክተዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ በበኩላቸው ተቋሙ የአገሪቷ የዕድገትና የልማት አጋዥ እንዲሆን ለማስቻል ሰፊ የአቅመ ግንባታ ሥራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ የአቅም ግንባታ ጥረቶቹም በዋንኛነት በተቋሙ ውስጥ የሚሰሩ ሥራዎች ቢሆኑም በተወሰነ ደረጃ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትና የሌሎች ባለድርሻ አካላት ግንዛቤን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራበት ነው ብለዋል፡፡

የሥልጠናው ዋና ዓላማም የምክር ቤቱ አባላት ዓለም አቀፉ የዋና ኦዲተሮች ማህበር እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1977 እና በ2007 ያሳለፋቸውን የሊማ እና የሜክሲኮ ውሳኔዎችን ግንዛቤ እንዲይዙ ለማድረግ ነው፡፡ በተለይ የመንግሥታቱ ድርጅት ባካሄደው 66ኛው ጠቅላላ ጉባዔው ላይ የመንግሥት የኦዲት ተቋማትን በተመለከተ ያሳለፈውን ውሳኔ ኢትዮጵያ ተቀብላ ማጽደቅ እንድትችል የጋራ ግንዛቤ ለመፍጠር ያለመ መሆኑን ዋና ኢዲተሩ አስረድተዋል፡፡

የኦዲት ዓላማ ከሕዝብ የሚሰበስብን ገንዘብ የማስተዳደር ሥራ በእምነትና በኃላፊነት የሚሰራው አካል ሥራውን በሕግና በእምነት እየተወጣ መሆኑን መቆጣጠር በመሆኑ የኦዲት ተቋማት ነፃና ገለልተኛ ሆነው እንዲሰሩ የምክር ቤቱ ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡ መንግሥት ያስቀመጠውን ተልዕኮ ተቋማት በአግባቡ መወጣታቸውንና የተመደበላቸውን ኃብት በቁጠባና በትክክል መጠቀማቸውን ቁጥጥርና ክትትል ለማድረግ የኦዲት ተቋማት አደረጃጀት በዘመናዊ መልክ መገንባት አስፈላጊ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

እንደ ኢዜአ ዘገባ የሥልጠናው ትኩረትም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና በዋናው ኢዲተር መካከል ሊኖር ስለሚገባው ግንኙነት እንዲሁም በኦዲት አስፈላጊነት፣ በቅድመና ድህረ-ኦዲት፣ በኦዲት ሕጋዊነትና በክዋኔ ኦዲት ላይ መሆኑን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘገባ አመልክቷል፡፡