ከአሸባሪው የኦጋዴን ነፃ አውጭ ግንባር የተነጠለ ቡድን ሕገ መንግስቱን ተቀብሎ ከመንግስት ጋር ለመወያየት አዲስ አበባ ገባ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 15/2005 (ዋኢማ) - ራሱን የኦጋዴን ነፃ አውጭ ግንባር ብሎ የሚጠራው አሸባሪ ቡድን አንድ ክንፍ ህገ መንግስቱን ተቀብሎ በሶማሌ ክልልና በሀገሪቱ ልማት ስራ ላይ ለመሳተፍ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ለመወያየት አዲስ አበባ ገባ፡፡
የክንፉ መሪ አብዲኑር አብዱላሂ ፋራህ የሶማሌ ክልል ህዝብ እንደሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ በፌዴራል ስርዓቱ ተጠቃሚ መሆኑን ማረጋገጥ በመቻላችን የሰላም መንገዱን መርጠናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት ባቀረባቸው የሰላም ጥሪዎች የተለያዩ ቡድኖች በተለያዩ ጊዜ የሰላም ጥሪውን እየተቀበሉ በሀገሪቱ ልማት የራሳቸውን አስተዋፅኦ እያበረከቱ ይገኛሉ፡፡

በኢንጅነር ማኦ እና በሐሰን አብዲ ካሂን የሚመራ አሊታህት ተብሎ ይጠራ የነበረው አሸባሪ ቡድንም የኢትዮጵያን መንግስት የልማትና የሰላም ጥሪ በመቀበል አሁን በሶማሌ ክልል ወደ ልማት ገብቷል፡፡

በታላቁና የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አነሳሽነት በኬኒያ መንግስት አደራዳሪነት በናይሮቢ ከሚገኙ የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጪ ግንባር ብሎ ከሚጠራው የአሸባሪ ቡድን አመራሮች ጋርም ውይይት ተጀምሮ ነበር፡፡

የአሸባሪው የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጪ ግንባር ተደራዳሪዎች ህገ መንግስቱን አንቀበልም በማለታቸው ግን ውይይቱ ተቋርጦ ቆይቷል፡፡

ይህን ተከትሎም በአሸባሪ ቡድኑ ውስጥ ህገ መንግስቱን በመቀበልና ባለመቀበል በተፈጠረ አለመግባባት በመከፋፈላቸው ጥቂቶቹ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን አንቀበልም በሚል ማፈንገጣቸውን ህገ መንግስቱን በመቀበል ለሰላማዊ ድርድር አዲስ አበባ የገቡት አብዲኑር አብዱላሂ ተናግረዋል፡፡

“ህገ መንግስቱን የሚቃወሙት አካላት የህዝብ መሠረት የላቸውም፡፡ በጣም በጣም ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ በአድሚራል መሐመድ ኡስማን የሚመሩ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ አሁን እሱ አስመራ ተደብቋል፡፡ በአውሮፓና በለንደን ከሚገኘው ህዝብ ጋር አይገናኝም፡፡ እኛ ግን ከደጋፊዎቻችን ጋር በመወያየት ህገ መንግስቱን ተቀብለን መጥተናል፡፡”

አብዲኑር አብዱላሂ ፋራህ የአሸባሪውና ራሱን የኦጋዴን ነፃ አውጪ ብሔራዊ ግንባር ብሎ የሚጠራው ግንባር የምስራቅ አፍሪካ ወኪል፣ የማዕከላዊ ኮሚቴ ስራ አስፈፃሚ እና የድርድሩ ቃል አቀባይ እንዲሁም የግንባሩ ምክትል የውጪ ጉዳይ ፀሃፊ ናቸው፡፡

አብዲ ኑር ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን አንቀበልም ማለታችንም ስህተት ነበር ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በሀገሪቱ ባለው ህገ መንግስታዊ ስርዓት የሶማሌ ክልል ህዝብ ተጠቃሚ በመሆኑና እንደ ሌሎች የሀገሪቱ ህዝቦች ራሱን ማስተዳደር በመቻሉ እነሱም ስርዓቱን ለመቀላቀል መወሰናቸውን ነው የተናገሩት፡፡ “ እኛ ህገ መንግስቱን አንቅበልም ማለት አንችልም፡፡ ከሁሉም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ጋር እኩል መብት የሠጠን ነው፡፡ ከአማራው ከኦሮሞው ከትግሬው ከጋምቤላው ከሁሉም ጋር እኩል፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ነን፡፡ የነበረን ስሜት ትክክል አልነበረም፡፡ ህገ መንግስቱን አንቀበልም ማለታችን ትልቅ ስህተት ነበር፡፡”

እንደ ኢሬቴስ ዘገባ በሀገሪቱ በተካሄደው የስልጣን መተካካት የነበረው ፍፁም ሰላምም የአሸባሪው ቡድን ከነበረው አስተሳሰብ ተቃራኒ ነበር ብለዋል፡፡ ይህም ሌላው የሰላም አማራጩን እንዲመለከቱ ያስቻላቸው ምክንያት መሆኑን በመግለፅ፡፡ “ የስልጣን መተካካቱን ተከትሎ ተቃውሞና የፖለቲካ ፓርቲዎች ብጥብጥ ይኖራል ብለን አስበን ነበር፡፡ የሆነው ነገር ግን የተቃውሞ ህልማችንን ነው የገደለው፡፡ ኢትዮጵያውያን ይህን የመሩበትን አግባብ ስንመለከት ከደጋፊዎቻችን ጋር የሰላሙን መንገድ ለመምረጥ ተገደናል፡፡ ይሄን ነው እንግዲህ ወክዬ ከመንግስት ጋር ለመወያየት የመጣሁት፡፡”