የሩዋንዳ አርበኞች ግንባር 25ኛ ዓመት የብር እዩቤልዩ በዓል ተከበረ

  • PDF

አዲስ አበባ፣  ታህሳስ 13/2005 (ዋኢማ) - እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1987 በሩዋንዳ ባለው የእርስ በእርስ ጥላቻ ተማረው ዩጋንዳ በተሰደዱ የቱቱሲ ጎሳዎች የተመሰረተው የሩዋንዳ አርበኞች ግንባር 25ኛ ዓመት የብር እዩቤልዩ በዓሉን አክብሯል፡፡

“ብልፅግናና ክብር ለሩዋንዳውያን” በሚል መርህ የተከበረው የግንባሩ እዮቤልዩ በዓል ላይ ተባብሮ ማደግ የብሔራዊ ፖሊሲያቸን መርህ ነው ያሉት የሩዋንዳ ፕሬዚደንት ፖልካጋሜ ለሩዋንዳ እድገት የግንባሩ አባላት በቁርጠኝነት መስራት ወጣቶች ደግሞ የተጀመረውን እድገት አስቀጥሎ የሀገሪቱን ራዕይ በማሳካት ረገድ ግንባር ቀደም ይሆናሉ ብለዋል፡፡

የሩዋንዳ አርበኞች ግንባር ሀገሪቱን ማስተዳደር ከጀመረ ወዲሀ ለተከታታይ እድገት፣ለሰላምና መረጋጋት ምሰሶ የሆነ ዴሞክራሲ በመገንባታችን ተጨባጭ ለውጥ ማሰመዝገብ ችለናል ብለዋል፡፡

”ሀገሪቱን አየመራ ያለው የሩዋንዳ አርበኞቸ ግንባር በርካታ ችግሮች አልፎ ሀገሪቱ በእድገት ጎዳና እንድትጓዝ እያደረገ ነው፡፡ሰብአዊ ክብራችንና ነፃነታችንን ጠብቀን በተጀመረው የልማት ጎዳና ወደፊት መገስገስ ነው እንጂ ወደ ኋላ መመለስ ከአሁን በኋላ አይታሰብም፡፡ ምንም እንኳን አሁንም የተለያዩ ተግዳሮቶች ቢኖሩብንም ቀድሞ ከገጠመን አይብስምና እንዴት መወጣት እንዳለብን እናውቃለን፡፡”

የሀገሪቱ ነዋሪዎች በበኩላቸው የሩዋንዳ አርበኞች ግንባር የሀገሪቱን ዜጎች አንድ ማድረግ የቻለ በገጠርና በከተማ ያሉ ነዋሪዎችን እኩል ተጠቃሚ ያደረገ ፣ሰብአዊ ክብርን ያረጋገጠ ነው ብለዋል፡፡

በሀገሪቱ እየተመዘገበ ያለውን ውጤት ለማስቀጠልም ከግንባሩ ጎን እንደሚቆሙ አረጋግጠዋል፡፡

”ሴቶች ድምፃችን መሰማት ጀምሯል ሀብት ማፍራትም ችለናል፡፡ሰብአዊ ክብራችንም ተጠብቋል፡፡በየአካባቢያችን በተሰሩ የጤና ፣የትምህርትና የመሰረተ ልማት ተጠቃሚ ሆነናል፡፡ይህን ለማስቀጠልም ቁርጠኞች ነን” ብለዋል፡፡ በበዓሉ ላይ የተሳተፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ኢትዮጵያና ሩዋንዳ መንግስትና ህዝብን ማዕከል ያደረገ ልማት በማከናወን በፍጥነት ለማደግ ያላቸው ቁርጠኝነትና የህዝብ ወገንተኝነት ያመሳስላቸዋል ነው ያሉት፡፡

ሩዋንዳ ከጅምላ ጭፍጨፋ ወጥታ ከአፍሪካ ፈጣን እድገት እያስመዘገቡ ካሉ ሀገራት ተርታ መሰለፏ የሚደንቅ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ከሩዋንዳ ተሞክሮ መቅሰም ይገባል ብለዋል፡፡