ለግብርና ምርት አመቺ የሆኑ መሬቶችን በማልማት በኩል የተከናወኑ ስራዎች ውጤታማ መሆን መቻላቸው ተገለፀ

  • PDF

አዲስ አበባ ታህሳስ 12/2005 (ዋኢማ) - በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ መሰረት ለግብርና ምርት አመቺ የሆኑ መሬቶችን በማልማት ረገድ ባለፈው የበጀት ዓመት የተከናወነው ስራ ውጤታማ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

በሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነት ከፍተኛ ባለሞያ አቶ መሀመድ አባሚልኪ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለጹት፤ በበጀት ዓመቱ ከ12 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት በዋና ዋና ምግብ ሰብሎች መሸፈን ተችሏል።

በበጀት ዓመቱ በዋና ዋና የምግብ ሰብሎች ለመሸፈን ታቅዶ የነበረው 11 ሚሊየን 586 ሺ ሄክታር መሬት እንደነበር ያስታወሱት ባለሞያው ክንውኑ 104 ነጥብ 3 በመቶ መሆኑን አስረድተዋል።

በስራ ስር ሰብሎች ከዕቅዱ በላይ 116 ነጥብ 5 በመቶ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ሰብሎች 100 ነጥብ 1 በመቶና ለኢንዱስትሪ ግብዓትነት የሚያገለግ ሰብሎች 126 ነጥብ 2 በመቶ መሬት መሸፈን እንደተቻለም ገልጸዋል፡፡

የምግብ እህል ሰብሎች ምርታማነትን በሄክታር 18 ነጥብ 1 ኩንታል ለማድረስ ታቅዶ 100 ነጥብ 6 በመቶ ማከናወን መቻሉን አቶ መሀመድ ጠቁመዋል።

ለክንውኖቹ ከዕቅድ በላይ መሆን የኤክስቴንሽን ስርዓት ተጠናክሮ መካሄድ፣ የአፈርና ውሃ ጥበቃ እንዲሁም የአነስተኛ መስኖ ልማት በስፋት መከናወኑ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ባለሞያው ጠቁመዋል።