የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኪሚቴ ስብሰባ ውሳኔዎችን በማሳተላለፍ ተጠናቀቀ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ታሀሳስ 14/2005 (ዋኢማ) - የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኪሚቴ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን በማስተላለፍ ተጠናቀቀ፡፡

የግንባሩ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ዛሬ ለዋልታ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው የሁለት ቀናት ስብሰባውን የጀመረው የፌዴራል መንግስት ተቋማትን የ2005 የዕቅድ ዝግጅት ምዕራፍና ዋና ዋና የመንግሥትና የድርጅት ሥራዎችን በማስቀደም ነበር፡፡

በ2004 የበጀት ዓመት አፈጻጸም ግምገማ ከተለዩት ደካማና ጠንካራ የአፈጻጸም ውጤቶች በመነሳት የተካሄደውን የዕቅድ ዝግጅትና ፈፃሚ የማዘጋጀት ሂደት መፈተሹን መግለጫው ጠቁሟል፡፡

በዝግጅት ምዕራፍ ፈጻሚ የማዘጋጀት ሂደት የድርጅትን፣ የመንግስትንና ዋናው ፈጻሚና ተጠቃሚ የሆነውን የሕዝብ አቅም በዝርዝር ለይቶ ለመገንባት የተደረገው ጥረት ከወትሮው የተሻለ አፈጻጸም የታየበት እንደሆነ አረጋግጧል፡፡

በተለይም በእያንዳንዱ ዘርፍ ከተልዕኮው አንጻር ተጠቃሚ ወይም ተገልጋይ የሆነውን የሕዝብ ወገን በዝርዝር ለይቶ ቀጣይነት ያለውና በተጠያቂነት ላይ የተመሰረተ የተሳትፎና የግንኙነት ሥርዓት ለመገንባት የተጀመረው ጥረት መልካም አስተዳደርን ለማስፈንና የመንግስትን አገልግሎት ጥራትና ቅልጥፍና ለማረጋገጥ የሚያስችል በመሆኑ በእስካሁኑ የተሻለ ርቀት ከሄዱት ዘርፎች ልምድ በመነሳት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም በአጽንኦት አሳሰቧል፡፡

በዝግጅት ሥራው ተመስርቶ በየዘርፉ የተከናወኑትን አባይት የልማት ሥራዎችን የፈተሸው የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ፈጣኑ የኢኮኖሚ ዕድገት ይበልጥ ጤንነቱን ጠብቆ በመቀጠል ላይ መሆኑን መገምገሙንም መግለጫው ጠቁሟል፡፡

የከተማውን ነዋሪ በተለይም አነስተኛ ገቢ ያለውን የህብረተሰብ ክፍል በመፈታተን ላይ የነበረው የዋጋ ግሽበት ቀደም ሲል ከ39 በመቶ በላይ ከነበረበት በከፍተኛ ፍጥነት እየቀነሰ መጥቶ በህዳር ወር 15 ነጥብ 6 በመቶ ላይ እንደደረሰ ያመለከተው መግለጫው በሚቀጥሉት ጥቂት ወራት ወደ ነጠላ አሃዝ እንዲወርድ የተጀመረው ጥረት እንደሚቀጥል ኮሚቴው ማረጋገጡን ገልጿል፡፡

መንግስት የሕዝቡን የገቢ አቅም ለመጨመር ከሚያደርገው ጥረት ባሻገር የምርት አቅርቦቱ አሁን በተጀመረው ሁኔታ ይበልጥ እያደገ እንዲሄድ በየደረጃው ያላሰለሰ ርብርብ መደረግ እንዳለበትም አሳስቧል፡፡

መግለጫው አያይዞም የጤፍ ምርት በተለይም በትግራይና በአማራ ክልሎች በመስመር የመዝራት ባህል እያደገ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ በከፍተኛ መጠን እየጨመረ ሲሆን በያዝነው ዓመት በተቀሩት ክልሎች ይህ ዘመናዊ አሰራር በስፋት ሲተገበር ትርጉም ያለው ለውጥ እንደሚመጣ አመልክቷል፡፡

የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ግኝት እየጨመረ መምጣቱን የገመገመው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው እየተመዘገበ ያለው ፈጣን ልማትና አስተማማኝ ሰላም ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በዓለም ዓቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ ይበልጥ መተማመን እየተፈጠረ መሆኑን አስገንዝቧል፡፡

በተያያዥም ወደ አገሪቱ የሚፈሰው ኢንቨስትመንትና ቱሪዝም እንዲሁም ብድርና ዕርዳታ መጠንና ዓይነት እየጨመረ መምጣቱንና ወደ ውጭ ከሚላኩት ምርቶች የሚገኘው ገቢም ይበልጥ መጠናከር የሚገባው መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ እያደገ መምጣቱ ለኢኮኖሚው ጤናማነት አንዱ ዋና  ምክንያት እንደሆነ አረጋግጧል፡፡

በሌላ በኩልም በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ የተጀመሩት ግዙፍ ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተፋጠነ በመሆኑ የሚጠይቁት የውጭ ምንዛሪና የብር መጠንም እየጨመረ የመጣ ሲሆን ይህንኑ በብቃት ለመሸፈን የአገር ውስጥ ቁጠባችን መሻሻል እያሳየ ቢመጣም በላቀ ፍጥነት እንዲያድግ ሰፊ ንቅናቄ ማድረግ ይገባል ብሏል፡፡

ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ወደ ውጭ የምንልካቸው ምርቶች በዓይነትና በመጠን በፍጥነት ማሳደግ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥቶ ተወያይቷል፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞም በቅርቡ በግንባሩ ሊቀመንበርና በጠቅላይ ሚኒስትሩ እና በባለሃብቱ መካከል የተደረገውን ምክክር ቀጣይነት በማረጋገጥ በየዘርፉ የሚያጋጥሙ ማነቆዎች በፍጥነት እየተፈቱ የሚሄዱበት አሰራር ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ወስኗል፡፡

በመልካም አስተዳደር ረገድ በክልሎች ቀደም ብሎ እንቅስቃሴ የተጀመረ ሲሆን የአዲስ አበባ አስተዳደር በአጭር ጊዜ መፈታት የሚገባቸውና በተቀመጠው የሪፎርም ስርዓት ደረጃ በደረጃ የሚሻሻሉትን ጉዳዮች የህዝብ ቅሬታ ከሚበዛባቸው መስኮች በመጀመር በህዝቡ ተሳትፎ ለመፍታት የያዘው ዕቅድ ዘግየት ብሎ የጀመረ ቢሆንም በትክክለኛው አቅጣጫ ለመጓዝ የሚያስችል በመሆኑ በፍጥነት እንዲተገበር አሳስቧል፡፡

የነዋሪውን የገቢ አቅም ለማሳደግና የፈጣን ዕድገታችን ፍትሃዊነት ለማጎልበት የሚያስችለ የሥራ ዕድል ፈጠራ ዕቅድ ባለፈው ዓመት ከተሄደው ርቀት በላይ መፈጸም ያለበት በመሆኑ ነዋሪውን በማሳተፍና በየደረጃው የአመራርና የሠራተኛውን አቅም በማጎልበት ወደ ተግባር እንዲመነዘርና የሚመለከታቸው የፌዴራል ተቋማትም ለዕቅዱ ስኬት ሚናቸውን እንዲወጡ አስገንዝቧል፡፡

ወቅታዊ ጉዳዮችን በዳሰሰበት አጀንዳው የተጀመረውን የአዲስ አበባ ምክር ቤትና የአካባቢ ማሟያ ምርጫ አፈጻጸም የፈተሸ ሲሆን ግንባሩ ባወጣው ዕቅድ መሰረት ምርጫው፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ያስወጠነውን ግብ ለማሳካት በመደረግ ላይ ያለው እንቅስቃሴ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ወስኗል፡፡

በማያያዝም በምርጫው በሰላማዊ መንገድ ለመሳተፍ ከወሰኑትና የስነ ምግባር ኮዱን ከፈረሙ ፓርቲዎች ጋር በራሱ ተነሳሽነት የጋራ ኮሚቴ እንዲፈጠር ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የተጀማመሩት ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስቧል፡፡

በሌላ በኩልም አንዳንድ ፓርቲዎች ለዴሞክራሲ ሥርዓታችን በአጠቃላይና ለአካባቢ ምርጫ በተለይ ያላቸው እምነትና ዝግጁነት አናሳ ሆኖ ሲያበቃ የተለያዩ ምናባዊ ችግሮችን በመደርደር በምርጫው ላለመሳተፍ የሚያሳዩት ማንገራገር የውስጥ ድክመትን ለመሸፈን የሚደረግ እብለት በመሆኑ ተቀባይነት እንደሌለው ገልጿል፡፡

በመጨረሻም በልዩ ልዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን በማሳለፍ የሁለት ቀን ስብሰባውን አጠናቋል፡፡