ምክር ቤቱ በሱዳኖች መካከል የተደረሱት የሰላም የስምምነት ማዕቀፎች ተግባራዊነት መዘግየት እንዳሳሰበው ገለጸ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 8/2005(ዋኢማ) - የአፍሪካ ኅብረት የሰላምና ጸጥታ ምክር ቤት በሁለቱ ሱዳኖች መካከል የተደረሱት የሰላም የስምምነት ማዕቀፎች ተግባራዊነት መዘግየት እንዳሳሰበው ገለጸ።

የሰላምና ጸጥታ ምክር ቤት ሰሞኑን ባካሄደው 349ኛ ስብሰባው በሁለቱ ሱዳኖች መካከል በመስከረም 2005 የተደረሱት ስምምነቶችን አተገባበር መጓተት አሳሳቢ እንደሆነበት ገልጿል።

አገሮቹ አዲስ አበባ ላይ ተስማምተውባቸው ከነበሩት በተለይ ምክር ቤቱ በጸጥታ ጉዳዮች ላይ ያለው አተገባበር መዘግየት እጅግ እንዳሳሰበው አመልክቷል።

ምክር ቤቱ ደቡብ ሱዳንና የሱዳን ሪፐብሊክ ከላይ የጠቀሱትን የስምምነት ማዕቀፎች በአፋጣኝ ገቢራዊ እንዲያደርጉና ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስቧል።

ምክር ቤቱ በሱዳን የአፍሪካ ኅብረት ከፍተኛ የሸምጋዮች ቡድንም በሁለቱ አገሮች መካከል አለመግባባት የፈጠሩ አወዛጋቢ ጉዳዮች በተመለከተ ቡድኑ ለምክር ቤቱ የመጨረሻ ሪፖርት እንዲያቀርብ ጠይቋል።

አገሮቹ ስምምነት የደረሱባቸው በጸጥታ፣ በሌላው አገር ያሉ ዜጎች፣ የድንበር፣ የንግድና ተያያዥ፣ በሁለቱ አገሮች ማዕከላዊ ባንኮች የትብብር ማዕቀፍ፣ የድህረ ክፍያ ጉዳዮች፣ በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ማለትም በሃብት ጥያቄ፣ በዕዳ አከፋፋል፣ በነዳጅና ከነዳጅ ጋር ተያያዥ ጉዳዮች እንደነበሩ መግለጹን የዘገበው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ነው።