ኢንቬስትመንት በጋምቤላ - ስኬትና ተግዳራቶች

  • PDF

በሪሁን  ሽፈራው

ኢትዮጵያ የበርካታ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች አገር ስትሆን በአሁኑ ወቅት 75 የሚሆኑ በፌዴሬሽን ምክር ቤት መቀመጫ እንዳላቸው መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በአገሪቱ ካሉ ዘጠኝ ክልሎች መካከል አራቱ ልዩ ድጋፍ የሚሹ ክልሎች ናቸው፡፡ እነዚህም የሶማሌ፣ የጋምቤላ፣ የአፋርና የቤንሻንጉል ጉሙዝ ናቸው፡፡ እነዚህ ክልሎች ባለፉት ስርዓታት ትኩረት የተነፈጋቸው ስለነበሩ በአገሪቱ ሰፍኖ በነበረው ድህነትና ብስቁልና የበለጠ ተጎጂ እንደነበሩ ይታወቃል፡፡

በክልሎች የሚኖረው  ህዝብ በአመዛኙ አርሶና አርብቶ አደር ሲሆን ምንም እንኳን ሁሉም ኢትዮጵያውያን በድህነት አረንቋ ተዘፍቆ ለእርስ በርስ ግጭትና ብጥብጥ ተዳርጎ የመደብና የብሔር ጭቆና ተንሰራፍቶበት የኖረ ቢሆንም የእንዚህ ክልሎች ሕዝቦች ግን  በከፋ ደረጃ የችግሩ ሰለባ እንደነበሩ  የታሪክ  ማህደር ያሳያል።

የእነዚህ ክልሎች ህዝቦች በአመዛኙ አርብቶና አርሶ አደር ናቸው፡፡ በተለይ ደግሞ በአገሪቱ  ሰሜን ምስራቅ፣ ደቡብ ምስራቅ፣ ደቡብ፣ ደቡብ ምዕራብና ምዕራብ አካባቢዎች ሰፈረው የሚገኙ ሕዝቦች አርብቶ አደሮች መሆናቸው ይታወቃል።  መሰረተ ልማት ያልተዘረጋባቸውና የአገልግሎት መስጫ ተቋማት ያልተገነባባቸው አካባቢዎች በመሆናቸው ሕዝቡ የበለጠ ተጎጂ መሆን ችሏል፡፡

የአርብቶና ከፊል አርብቶ አደር ሕዝቦች   ከሌሎች የአገሪቱ ሕዝቦች ጋር በንጽጽር ሲታዩ በሁሉም መልክ  ተጠቃሚዎች አልነበሩም። እነዚህ ሕዝቦች በተበታተነ አኗኗር በባህላዊ የእንስሳት እርባታ የሚተዳደሩ ነበሩ። 

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የመሰረተ ልማት ግንባታ በፈጣን የእድገት   ላይ ይገኛል። በመላ አገሪቱ የመንገድ፣ የስልክ፣ የመብራትና የመሳሰሉ መሰረተ ልማቶች ተስፋፍተዋል።  በእነዚህ አካባቢዎች ያለው የመሰረተ ልማት ዝርጋት  በተወሰነ ደረጃ መሻሻልን እያሳየ መጥቷል።  እነዚህ ክልሎች ልዩ ድጋፍ የሚሹ መሆናቸውን በመገንዘብ መንግስት በተለያየ ጊዜ የአቅም ግንባታና ሌሎች ድጋፎችን በማድረግ የክልሎቹ ሕዝቦች ከሌላው የአገሪቱ ክልሎች ሕዝቦች ጋር እኩል ተጠቃሚ የሚሆኑበትን መንገድ ቀይሶ እየሰራ ይገኛል።
የአገሪቱ ሕገ መንግስት የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን እኩልነት፣ ነጻነትና እኩል ተጠቃሚነትን ባረጋገጠ ማግስት ክልሎቹ የራሳቸውን አስተዳደር በመመስረት አካባቢያቸውን በማልማት ላይ እንደሚገኙ መረጃዎች ያሳያሉ።

መንግስት ለክልሎቹ ተገቢውን በጀት በመመደብ መሰረተ ልማትን  በማስፋፋትና የአገልግሎት መስጫ ተቋማትን በመገንባትና በሰለጠኑ ባለሙያዎች የአካባቢው ብረተሰብ ተጠቃሚ እንዲሆን በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ የተለያዩ ትላልቅ ልማቶችን በማስፋፋትና የግል ኢንቬስትመንት ይስፋፋ ዘንድ አመች ሁኔታን በመፍጠር የክልሎቹ እድገት ከሌሎች ጋር ለማመጣጠን ጥረት እየተደረገ ነው። የሚከናወነው የመሰረተ ልማት ግንባታ እየተስፋፋ መምጣቱን ተከትል የተለያዩ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት በመስፋፋታቸው በአካባቢው ያለውን የኢንቬስትመንት አማራጭ መጠቀም የሚፈልጉ ባለሃብቶች ቁጥር እያደገ የመጣበት ሁኔታ እንዳለም ለማየት ይቻላል። 

በኢትዮጵያ ያሉትን ልዩ ድጋፍ የሚሹ ክልሎችን ለአብነት አነሳን እንጂ ይህ  ጽሁፍ የዳሰሰው የጋምቤላ ክልል የኢንቬስትመንት እንቅስቃሴ ነው። የጋምቤላ ክልል ሰፊ የኢንቬስተመንት አማራጮች እንዳለው ቢታወቅም ባለፉት ስርዓታት የተፈጥሮ ሃብቱን ወደ ጥቅም መቀየር የተቻለበት ሁኔታ አልነበረም።  ለዚህ በዋናነት የሚወሰደው በአገሪቱ ልማታዊ መንግስት አለመኖሩ ሲሆን ሌላው ደግሞ ክልሉ መሰረተ ልማት ያልነበረውና ትኩረት የተነፈገው ስለነበር እንደሆነ እሙን ነው፡፡ ህዝቡ የትምህርት ማዕድ ተቋዳሽ አልነበረም።

በጤና ረገድም የአገልግሎት መስጫ ተቋማት ባለመስፋፋታቸውና የህዝቡ አኗኗርም የተበታተነ በመሆኑ ህዝቡን ተደራሽ ለማድረግ አስቸጋሪ እንደሆነ ይታወቃል፡፡  የጤና ጣቢያ ባለበት አካባቢም ቢሆን የባለሙያ እጥረት በመኖሩ ሕብረተሰቡ የጤና አገልግሎት ማግኘት የቻለበት ሁኔታ አልነበረም፡፡

በርካታ የተፈጥሮ ጸጋ ያለው ክልል ነው፡፡ ከእነዚህ ጸጋዎች መካከልም የባሮ ወንዝን በአብነት መውሰድ ይቻላል፡፡  ወንዙ ክልሉን አቋርጦ የሚያልፍ በመሆኑም ወንዙን ተከትሎ በርካታ ልማቶችን ማከናወን የሚያስችል አመች ሁኔታ እንዳለ መረዳት ይቻላል።

አንዳንድ አካባቢውን የጎበኙ ሰዎች እንደሚገልጹት የጋምቤላ ክልልን  ምድረ ገነት በማለት ይገልጿታል።  በአኝዋህ ቋንቋ ‘ጂኒና’ ይሉታል።  ‘ጂኒና’ ማለት ገነት ማለት እንደሆነም የአካባቢው አባቶች ይናገራሉ፡፡ ‘ጂኒና’ የማይሰበሰብ የለም፤ ወጣቱ፣ የመንግስት ሰራተኛው፣ ህጻናት ልጆችና አዛውንት ከስፍራው አይለዩም፡፡ ይህ ቦታ የአካባቢው ነዋሪዎች ሻይ ቡና የሚሉበትና ቀዝቃዛውን አየር እየማጉ ከሙቀት  ጫና ተንፈስ የሚሉበት ተመራጭ ስፍራ መሆኑ ይታወቃል፡፡

የባሮ ወንዝን ለልማት ማዋል ከተቻለ  የህዝቡን ህይወት ማሻሻል እንደሚቻል እሙን  ነው።  ይሁን እንጂ ለዘመናት ለልማት ሳይውል ዘልቋል።  ይልቁንም ክረምት በመጣ ቁጥር ውሃው እየሞላ ህዝቡንና ንብረቱን ለድንገተኛ አደጋ ይዳርገው እንደነበር ይታወቃል፡፡ ይህ ስጋት አሁን ተወግዷል። ባሮ የልማትና የብልጽግና ምንጭ እንጂ የጥፋትና የስጋት ምንጭ የሚሆንበት ሁኔታ ያከተመ ይመስላል። በአሁኑ ወቅት ሁኔታው ሙሉ በሙሉ በመቀየሩ እንደ ሳውዲ ስታር፣ ካራቱሪና ኢዛናን የመሳሰሉ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ማረፊያ ሆናለች፤ ጋምቤላ፡፡ እነዚህ ፕሮጀክቶች ሩዝ፣ ጥጥ፣ ማንጎ፣ ለውዝና መሰል ምርቶችን በሰፊው በማምረት ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ያለሙ መሆናቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡ በመሆኑም  ክልሉ  ለግብርና ኢንቨስትመንት አመች ከሆኑ የአገራችን አካባቢዎች አንዱ ነው፡፡

በቆሎ፣ ዳጉሳ፣ ሰሊጥ፣ ለውዝ፣ አኩሪ አተርና አደንጓሬ በሰፊው ማምረት የሚያስችል ለም መሬትና ተስማሚ የአየር ንብረት እንዳለ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ እንደዚሁም ማንጎ፣ ዘይቱን፣ ብርቱኳንና ሌሎች ፍራፍሬዎችንና እንደ  ቁርንፉድ፣  ኮረሪማና ቁንዶ በርበሬ የመሳሰሉ ቅመማ ቅመሞች በሰፊው   ለማምረት የሚያስችል ሰፊ ለም መሬት አለ፡፡

ከዚህም በተጨማሪ እንደ ቡና፣ ሽንኮራ አገዳ፣ የፓልም ኦይልና የጃትሮፋ የመሳሰሉ ተክሎች በአካባቢው መልማት የሚችሉ ናቸው። እነዚህንና ሌሎች የግብርና ምርቶችን በአካባቢው በማልማት ከአገር ውስጥ ፍጆታ አልፎ ለውጭ አገር ገበያ  በማቅረብ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት የሚቻልበት እድል እንዳለ መረዳት ይቻላል። 

ሌላው የኢቬስትመንት አማራጭ የእንስሳት ሀብት ነው፡፡ የእንስሳት እርባታ ልዩ ትኩረት አግኝቶ ቢሰራበት የአገራችን አጠቃላይ የኢኮኖሚ ለውጥ ላይ የሚኖረው አወንታዊ ሚና ቀላል አይሆንም።  ዘመናዊ የአረባብ ዘዴን ከመጠቀም ጎን ለጎንም ከገበያ ጋር በማስተሳሰር ቀላል የማይባል ገቢ የሚገኝበትም ነው።  ለሥጋና ለወተት ሀብት ልማት ሊውሉ የሚችሉ እንስሳት በበቂ ሁኔታ በመያዝና በማራባት የአካባቢውን ህዝብ ተጠቃሚ ማድረግ የሚቻልበት ህኔታ በመኖሩ በዚህ መልክ መንግስት እየሰራ ቢሆንም  ባለሃብቶችም በዘርፉ ቢሳተፉ ተጠቃሚነታቸው የጎላ ከመሆነም ባሻገር የአካባቢውን ህዝብ በመጥቀም ረገድ የበኩላቸውን ድርሻ ይወጣሉ የሚል እምነት አለ።   
ለወተት ምርት ከሚውሉ ከብቶች በተጨማሪ ለሥጋ ምርት የሚውሉ በርካታ ዝርያዎች መኖራቸውን ከክልሉ የተገኘ መረጃ ያሳያል።   በአራትና አምስት ዓመት ዕድሜአቸው እስከ 400 ኪሎ ግራም የሚደርስ የሥጋ ምርት የሚሰጡ የከብት ዝርያዎችም እንዳሉ ለማወቅ ተችሏል። አካበቢው ንቦችን ለማነብም ተስማሚና ነው።  ከላይ ከተሰጠው ዝርዝር መረጃ በመነሳት በተለያየ ዘርፍ ኢንቬስት ማድረግ ለሚፈልጉ ባለሃብቶች መልካም አጋጣሚ እንደሆነ ለመረዳት ይቻላል።  ከዚህ በተጨማሪ የበርካታ ወንዞች መገኛ በመሆኑ ለዓሳና ለአዞ እርባታ አመችነት አለው። 

ባለሃብቶች በዚህ ዘርፍ ቢሰማሩ አዋጭነቱ አያጠራጥርም።  ባለፉት ስርዓታት ትኩረት ተነፍጎት የነበረው ይህ ክልል ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ሕገ መንግስቱ ባረጋገጠለት መብት በመጠቀም የኢንቬስትመንትና የሌሎች ልማቶች መስፋፋት ታይቷል። 

በሆቴሌና ቱሪዝም መስክም ክልሉ እየተለወጠ፣ አየተሻሻለና  እያደገ ስለመሆኑ እማኝ አያሻውም፡፡  በአሁኑ ወቅት በርካታ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች ተገንብተዋል፡፡ ይህ ደግሞ የሚያመላክተው የጎብኚዎች ፍሰት እየጨመረ መምጣቱን ነው፡፡ የገንዘብ ተቋማትም ቀደም ሲል እንዳልነበሩ ይታወቃል፡፡  በጋምቤላ ከተማ የነበረው ብቸኛ ባንክ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነበር፡፡ አሁን ግን ሁኔታው ሙሉ በሙሉ ተቀይሯል።  ዳሽን፣ ቡና ኢንተርናሽናል፣ ህብረት፣ ኮንስትራክሽንና ቢዝነስ የመሳሰሉት ባንኮች  ቅርንጫፎቻቸውን ከፍተው እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ 

በጋምቤላ ክልል ያለው ዘርፈ ብዙ ኢንቬስትመንት በዚህ መልክ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ መምጣቱ የተገኘ መረጃ ያሳያል፡፡ ለዚህ ደግሞ የክልሉ መንግስት ዘርፋን ለማስፋፋት ባደረገው ጥረት የክልሉን የኢንቨስትመንት አማራጮችን በማጥናት ከለየ በኋላ  ሰፊ የማስተዋወቅ ስራዎችን አካሂዷል።  

የክልሉ የኢንቬስትመንት ቢሮ በተለያዩ ዘርፎች መዋእለ ንዋያቸውን ማፍሰስ ለሚፈልጉ ባለሃብቶች ፈቃድ በመስጠትና በአፈፃፀም የሚከሰቱ ችግሮችን መፍታት የሚያስችል አሠራር በመቀየስ ኢንቨስትመንትን ማስፋፋትና ማጠናከር የሚቻልበት ምቹ ሁኔታ  መፍጠር ችሏል፡፡

አርሶ አደሩ  ከባህላዊ አስተራረስ ወጥቶ ዘመናዊ የአስተራረስ ዘዴን በመተግበርና  የተለየዩ የምርት ግብአቶችን በመጠቀም ምርታማነቱን ማሳደግ የቻለበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ከነበረው የከፋ አኗኗር ተላቆ የልማት ተጠቃሚ መሆን የሚችልበት ስትራቴጂ ተዘርግቶ እየተሰራበት ይገኛል።  በእንስሳት እርባታ የሚተዳደረው አርብቶና ከፊል አርብቶ አደርም ቀደሞ ይከተለው የነበረውን ባህላዊ የእንስሳት  አረባብ ዘይቤን በመተው ዘመናዊ የእርባታ ዘዴን በመከተል ምርታማነቱን ማሳደግ  የሚችልበት አሰራር ተዘርግቶለት ልዩ እገዛም እየተደረገለት ይገኛል። 

በቅርቡ በጋምቤላ ከተማ የግብርና ኢንቨስትመንት ስራ እንቅስቃሴን የዳሰሰ መድረክ  ተካሂዶ ነበር። በዚህ መድረክ በርካታ ጉዳዮች ተነስተው በተሳታፊዎች ውይይት ተካሂዶባቸዋል። የኢንቬስትመንት አማራጮችና የባለሃብቶች ተሳትፎ  በጥልቀት ከተዳሰሱት ጉዳዮች ዋናዎቹ ናቸው።  በክልሉ ያለው የመሰረተ ልማት መስፋፋትና የአገልግሎት መስጫ ተቋማት መበራከትን ተከትሎ  ወደ ክልሉ የሚሄዱ ባለሃብቶች ቁጥር እያደገ መጥቷል። 

ከክልሉ የኢንቬስትመንት ቢሮ የተገኘ መረጃ እንደሚያሳየው እስካሁን ድረስ ከ800 በላይ ለሚሆኑ አምስት ቢሊየን ብር የሚጠጋ ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሃብቶች በተለያየ የኢንቬስትመንት ዘርፍ ፈቃድ ተስጥቷል፡፡ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቁም 42,800  ቋሚ እና 187,800 ጊዜያዊ የስራ ዕድልን እንደሚፈጥሩም ለማወቅ ተችሏል፡፡

መልክዓ ምድሩ ሜዳማ በመሆኑ ለዘመናዊ እርሻ ስራ ሰፊና ምቹ  የሆነ በመስኖ አለዚያም በዝናብ ሊለማ የሚችል ከአንድ ሚሊዮን አራት መቶ ሺሕ  ሄክታር በላይ ለም መሬት  እንዳለ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የኢንቭስትመንት ቢሮው ለልማታዊ ባለሃብቶቹ የተቀላጠፈ የቅርብ ክትትልና እገዛ ያደርጋል፡፡ በክልሉ በግብርና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ፍቃድ የወሰዱ 352 በላሃብቶች 256 ሺሕ ሄክታር መሬት ተረክበዋል፡፡ ባለሃብቶቹ መሬቱን የተረከቡት በክልሉ በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች ሲሆን ከእነዚህም መካከል ጎግ፣ ኢታንግ፣ ዲማ፣ ጎደሬ፣ መንገሺ፣ ላሬና ጋምቤላ ወረዳዎች ይገኙበታል፡፡ ከእንቬስተሮቹ መካከል ሰባት የውጭ ባለሃብቶች ከ200 ሺሕ በላይ ሄክታር መሬት ተረክበው ወደ ስራ መግባታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡                              ባለሃብቶች ማበረታቻዎች የሚያገኙበትን ሁኔታ የክልሉ መንግሥት በማመቻቸት ምቹ የኢንቨስትመንት አካባቢ ለመፍጠር የሚያስችል አሰራር ዘርግቶ እየሰራ ቢሆንም የተለያዩ ተግዳሮቶች ማጋጠማቸው ግን አልቀረም፡፡

በ2004 ዓ/ም የበጀት ዓመት በተደረገው ክትትልና ግምገማ ለማወቅ እንደተቻለው በርካታ ባለሃብቶች በገቡት ውል መሰረት ሥራቸውን በተገቢው ያለመወጣት ሁኔታ ታይቷል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም የሰለጠነ በቂ የሰው ሃይል አለመኖር መስተዋሉን ግምገማው ያሳያል፡፡

ታላቁ መሪ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በህይወት ዘመናቸው በተለያየ ዘርፍ ከተሰማሩ ባለሃብቶች ጋር ውይይት አድርገው እንደነበር ይታወቃል።  ባለሃብቶችን ባነጋገሩበት አንድ ወቅት ላይም  በበርካቶች አእምሮ የተቀረጸና የማይጠፋ አንድ መልእክት አስተላልፈው ነበር።  “የውጭ አገር ባለሃብቶች  አንድ መቶ ዘጠና ዘጠኝ አገር አላቸው። ጥሩ ገበያና ርካሽ የሰው ሃይልም ሆነ የፋብሪካ ጥሬ እቃ አለው ብለው የሚያምኑት አገር ሄደው ማልማትና መጠቀም ይችላሉ።  እናንተ ኢትዮጵያውያን ባለሃብቶች ግን ያለቻችሁ አገር አንዲት  ብቻ ነች፡፡  ኢትዮጵያ ብቻ ስለሆነች ያለቻችሁ እሷኑ አልሟት” ነበር ያሉት።

መንግስት በሰፊው እየሰራበት ያለው እንደ መንገድ፣ ኤሌክትሪክ፣ ስልክና የመሳሰሉ መሰረተ ልማቶችና የአገልግሎት መስጫ ተቋማት ግንባታዎች የበለጠ በማጠናከር በአካባቢው የባለሃብቶች ተሳትፎ ለማሳደግ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ እንደሀነ መረጃዎች ያሳያሉ።  ከመሰረተ ልማትና የአገልግሎት ተቋማትን ከማስፋት ጎን ለጎን  የሰለጠነ የሰው ሃይል ችግርን ለመቅረፍ እያደረገ ያለው ጥረትም የሚደነቅ በመሆኑ አጠናክሮ በመቀጠል የአካባቢውን ልማት ለማፋጠን እየሰራ ይገኛል፡፡ 

በአካባቢው ሰላም እንዳይሰፍን በአንዳንድ  ግለሰቦችና ቡድኖች የሚደረገው ጥረት በተገቢው መንገድ በማክሸፍ ባለሃብቶ ያለምንም ስጋት ልማታቸውን እንዲያከናውኑ የማድረጉ ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል።   በአካባቢው  ሰላምን ለማደፍረስና  ልማትን ለማደናቀፍ የሚንቀሳቀሱ  ሃይሎችን እንቅስቃሴ  የክልሉ መንግስት ከፌደራል መንግስትና  ከመከላኪያ ሰራዊት ጋር በመቀናጀት በአስተማማኝ መልክ እንዲነጥፍ አድርጎታል፡፡

በጋምቤላ ያለውን ኢንቬስትመንት ለማስፋፋትና በቂ የሆነ የመሰረተ ልማትና የአገልግሎት መስጫ ተቋማት ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ  እየተሰራ ነው።  ህዝቡ ተጠቃሚ መሆን የሚችለው አሁን ያለው የተበታተነ የአኗኗር ሁኔታ መቀየር ሲቻል እንደሆነ እሙን ነው። በተበታተነ መልኩ የሚኖርን ህዝብ የልማትና የአገልግሎት ተቋማት ተጠቃሚ ማድረግ ስለሚያስቸግር ተበታትኖ የሚኖረውን ህዝብ ማሰባሰብ የግድ ነው።  በዚህ መልክ ህዝቡን  የመሰረተ ልማት ተጠቃሚ ለማድረግና በመካከሉ ያለውን ማሕበራዊ ሁኔታ ለማጠናከር በመንደር ማሰባሰብ አማራጭ የሌለው ተግባር ሆኖ በመገኘቱ  በዚህ ረገድ ሰፊ ሰራ እየተከናወነ ይገኛል፡፡

የባለሃብቱን ችግር ለመፍታት መልካም አስተዳደርን በመዘርጋትና በአፈጻጸም የሚያጋጥሙ አንዳንድ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት የተለያዩ መድረኮችን በማዘጋጀት  ረጅም መንገድ መሄድ ተችሏል፡፡ እሰካሁን ከቀረበው አስረጂ በመነሳት በአገሪቱ የሚገኙ ልዩ ድጋፍ የሚሹ  ክልሎችን የልማት ተጠቃሚ ለማድረግ መንግስት የተለያዩ እርምጃዎች እየወሰደ መሆኑን ለመረዳት ይቻላል፡፡ እነዚህ እቅዶች በአጭር፣ በመካከለኛና በረጅም ጊዜ ተከፍለው የተያዙ እንደሆነም ይታወቃል፡፡

መንግስት ከሚገነባቸው መሰረተ ልማቶችና አንዳንድ  የልማት ተቋማት ጎን ለጎን የግል ኢንቬስትመንት እንዲስፋፋ በማድረግ በክልሉ የሚኖሩ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ በተቀናጀ መልክ እየሰራ ነው፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች የሚኖሩ ህዝቦች በአገሪቱ እየተመዘገበ ካለው ልማት ተቋዳሽ ይሆኑ ዘንድ ያላሳለሰ ጥረት በመደረግ ላይ ይገኛል፡፡
በዚህ መልክ በክልሉ የሚኖሩ ህዝቦች በሌላው የአገሪቱ አካባቢ እንዳሉት ሁሉ ተጠቃሚነታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ይመጣል፡፡ ክልሉም ከሌሎች ክልሎች ጋር የተመጣጠነ እድገት እንዲኖረው ያስችላል፡፡  ለዚህ ግን በክልሉ ባለሃብቶ በሰፊው መዋእለ ንዋያቸውን ያፈሱ ዘንድ አመች ሁኔታዎችን መፍጠርና ተግዳራቶቹን ደረጃ በደረጃ መቅረፍ የግድ ይላል፡፡ በክልሉ ያለው ኢንቬስትመንት ብጥሩ ሁኔታ እያደገ ቢመጣም መሬት ከወሰዱ በሀላ ፕሮጀክቱን የማጓተትና ለታሰበለት ልማት ያለማዋል ትግባራትን በመከታተል በተገቢው ወቅት ልማቱ ይካሄድ ዘንድ እጅና ጓንት ሆኖ መንቀሳቀስ የግድ ይላል፡፡