የኤች አይ ቪ/ ኤድስን ስርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር ሁሉም አካላት የበኩላቸዉን ሊወጡ ይገባል

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 6/2005 (ዋኢማ) ¬- በሀገሪቱ ሁሉም አካባቢዎች ኤች አይ ቨ/ ኤድስ ስርጭትን በመከላከልና በመቆጣጠር ከቫይረሱ ነፃ የሆነ ትውልድ ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ባለድርሻ አካላት የበኩላቸዉን ሚና ሊወጣ እንደሚገባ የፌዴራል ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መከላካያና መቆጣጠሪያ ጽህፈት ቤት አስገነዘበ ።

በሀገሪቱ ሁሉም አካባቢዎች የበሽታውን ስርጭት በመከላከልና በመቆጣጠር ከቫይረሱ ነፃ የሆነ ትውልድ ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል። በሽታውን ሥርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚደረገውን ሥራ አጠናክሮ ለማስቀጠል በሚችልበት ሁኔታ ላይ የሚነጋገር ሀገር አቀፍ ጉባኤ ትናንት በጋምቤላ ከተማ ተጀምሯል።

የጽህፈት ቤቱ ዋና ዳሬክተር አቶ ብርሀኑ ፈይሳ ጉባኤውን ሲከፍቱ እንደገለጡት ባለፉት ዓመታት ለበሽታው ይበልጥ ተጋላጭ በሆኑ አከባቢዎች የአገልግሎቱን ተደራሽነት በማስፋት የበሽታውን ስርጭት ለመግታት በተከናወኑ ስራዎች አበረታች ውጤት ተገኝቷል ለዚህም ማሳያ በአዉሮፓዉያን አቆጣጠር በ2011በተካሄደው የሥነ-ህዝብና የጤና ቅኝት በነፍሰጡር እናቶች በተካሄደ ጥናት አዲስ በኤች አይ ቪ የመያዘ መጠን በ90 ከመቶ በኤድስ የሚሞቱት ሰዎች ቁጥርም ቢቀነስም ወረርሽኙ ከቦታ ቦታና እንደ የማህበረሰቡ አኗኗር የሚለያይ በመሆኑ በተገኙት ውጤቶች ለአፍታም መዘናጋት ሳይገባ የመካላከሉን ሥራ በማጠናከር ዘላቂነቱን ማረጋገጥ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የወረርሽኙ ስርጭት ጎልቱ ከሚታይባቸው አከባቢዎች አንዱ የጋምቤላ ክልል ነው ያሉት ዳሬክተሩ ጉባኤውን በክልሉ ማካሄድ ያስፈለገበት ዓብይ ዓላማ እየተካሄደ ያለውን የመከላከል ሥራ በጋራ በመቃኘት የተሻለ አቅጣጫ ለመቀየስ ነው ብለዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡቦንግ በበበኩላቸዉ እንደተናገሩት በክልሉ ብሎም በሀገር አቀፍ ደረጃ የተነደፈውን የልማት ራዕይ ማሰካት የሚቻለው ከኤች አይ ቨ ቫይረስ ነፃ የሆነ ዜጋ መፍጠር ሲቻል እንደሆነ ገልጠዋል። የበሽታው ሥርጭት በሀገር አቀፍ ደረጃ የመቀነስ አዝማሚያ ቢያሳይም በክልሉ ግን የቫይረሱ ስርጭት እየተስፋፋ ነዉ ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ የቫይረሱን ስርጭት በመግታት ነፃ ትውልድ ለመፍጠር ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ያላሳለሰ ጥረት ይጠበቃል ።

ጉባኤው በክልሉ መካሄዱ በሽታውን ለመካላከልና ለመቀጠጣር የሚካሄደውን ጥረት በተሻለ መልኩ ለመምራት መልካም ተሞክሮና ግብአት የሚገኝባት መድረክ እንደሚሆን ተናግረዋል። በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተቀናጀ የኤድስ መረሃ ግብር የኢትዮጵያ ተጠሪ ዶክተር ዋረን ናማራ በበኩላቸዉ እንደተናገሩት በኢትዮጵያ የቫይረሱን ስርጭት የመከላከሉ ጥረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ መጥቷል።

በሽታውን በመከላከሉ ረገድ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶቹን በመለየት የቫይረሱ ስርጭት በሚታዩባቸው አከባቢዎች መረሃ ግብሩን በማስፈጸም በተቀናጀ ሁኔታ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ከተቻለ ጤናማ ዜጋ ለመፍጠር የተያዘውን ራዕይ ማሳካት እንደሚቻል ገልጠዋል።

በሀገሪቱ በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እየተካሄደ ላለው መልካም እንቅስቃሴ ውጤታማነት ድርጀቱ የጀመረውን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥለም ተጠሪው ተናግረዋል።

የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች የአስቸኳይ ጊዜ የኤድስ መልሶ ማቋቋሚያ እቅድ የኢትዮጵያ ተጠሪ ዶክተር ካርሜላ አባተ በበኩላቸው ኢትዮጵያ አዲስ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከቀነሰባቸው የአፍሪካ አገሮች መካከል አንዷ እንደሆነች ተናግረዋል። የአሜሪካ መንግስት እትየጵያን ጨምሮ ለበርካታ የአፍሪካ ሀገሮች የቫይርሱን ስርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር ለሚደረገው ጥረት መሳካት አስፈላጊውን የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመው በቀጣይም ድጋፍን አጠናከሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ለሁለት ቀናት በሚቆየው ጉባኤ ከ200 በላይ የፌዴራል፣ የሁሉም ክልሎችና ዓለም አቀፍ ድርጅት ተወካዮች በመሳተፍ ላይ ሲሆኑ በጉባኤው ላይ የተለያዩ ጥናታዊ ጹሁፎችና ተሞክሮች ይቀርባሉ ።