ሂዩማን ራይትስ ዎች የምእራባውያን ሸፍጥ ማራገፊያ (ክፍል 2)

  • PDF

ዮናስ
እውነት ነው፡፡foreign policy የተሰኘው መጽሄት ባለፈው ዓመት " ከአለማችን የውጪ ጉዳይ ፓሊሲ ውስጥ ተጽእኖ አሳዳሪ” ብሎ ከመረጣቸው ግለሰቦች መካከል 69ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት እሳቸው ናቸው፡፡ በሚደነቅ የአመራር ክህሎትና እውቀታቸው የ “ሰብአዊ መብት” ጡንቻ እንዲፈረጥም አድርገዋል ይላል፡፡

መፅሔቱ የመረጠበትን ምክንያት ሲያስረዳ፡፡ ከዚህ ምርጫ አንድ አመት በፊት ግን The new times የተሰኘ መጽሔት በሚያዚያ 26 ቀን 2010 እትሙ ያስነበበው ጽሑፍ Rwanda is Kenneth Roth in love with Genocidaires ? እኚህ ኬኔዝ ሮዝ የሚባሉት ሰው ከጦር ወንጀለኞችና ከነፍሰ ገዳዮች ጋር ፍቅር ይዟቸዋልን ሲል ይጠይቃል፡፡ መፅሄቱ “የነፍሰ ገዳዮች አፍቃሪ" እያለ በኮስታራ ቃላት የሚተቸው ኬኔዝ ሮዝን ነው፡፡ ኬኔዝ ሮዝ ማለት ደግሞ በውጭ ጉዳይ ፓሊሲ እውቀታቸው የዓለማችን 69ኛ ምርጥ ሰው ተብለው ቀደም ብዬ በጠቀስኩት መጽሄት የተመረጡት ሰው ናቸው፡፡

ሌላም ተመሳሳይ ታሪክ አለ፡፡ የመጽሄቱ ምርጫ 4 ወር ሳይሞላው አንድ ደብዳቤ ወደ ኬኔዝ ሮዝ ተላከ “ግልጽ ደብዳቤ ለኬኔዝ ሮዝ” ይላል ርዕሱ፡፡ አፊያዚያ የተባለ ጋዜጠኛ ከ pakistan የፃፈወ ነው፡፡ ፡፡ ለደንቡ ያህል “ውድ ኬኔዝ ሮዝ” ብሎ የሚጀምረው ደብዳቤ ገና ከመጀመሪያው አንቀጽ ሰውዬውን መውቀስ ይጀምራል፡፡

በቅርቡ እሳቸው የሚመሩት ተቋም ያወጣውን ሪፖርት አስመልክቶ የሰጡትን አስተያየት እየጠቀሰ ክፉኛ ያብጠለጥላቸዋል፡፡ “ እርስዎ የሚመሩት እኮ አንድ በሰብአዊ መብቶች ዙሪያ የሚሰራን ተቋም ነው፡፡ ምን ነካዎ” እያለ ይሞግታቸዋል፡፡ እንዲህ አይነት የቅሬታ ደብዳቤዎችን መቁጠር ከጀመርን ጊዜው አይበቃንም፡፡ አዎ እኚህ ሰውና በዋና ሥራ አስፈፃሚነት የሚመሩት ተቋማቸው የበርካታ ውዝግቦች ምንጭ ናቸው፡፡ የሰሉ ሂሶች ይሰነዘርባቸዋል፡፡ በመንግሥት፣ በተቋምና በግለሰብ ደረጃ በተደጋጋሚ ይወቀሳሉ፡፡
ሰውዬውና ድርጅታቸውም የመልስ ምት ይሰጣሉ፡፡ ሙሉ ስም ኬኔዝ ሮዝ ሀኖ ለአጠራር እንዲያመች ይመስላል ኬን የሚሏቸው ይበዛሉ፡፡

ኒውዮርክ Human Rights Watch ዋናው መሥሪያ ቤት በ1987 ከተመሰረተ 9 ዓመት በኋላ ዋና ፀሐፊው አሪዮህ ኔየር አንድ ወጣት አስከትለው ወደ ቢሮአቸው ገቡና “ከዛሬ ጀምሮ ም/ዋና ፀሃፊያችሁ እሱ ነው” ሲሉ ለባልደረቦቻቸው አስተዋወቁ፡፡

ወጣቱ ኬን ሮዝ ሥራ ጀመረ፡፡በየል እና በብራውን ዩኒቨረስቲዎች የህግ ትምህርቱን ተከታትሏል፡ ለጥቂት ዓመታት ያህል በግሉ እየሰራ ሙያውን ካዳበረ በኋላ ፕሬዝዳንት ጂሚ ካርተርን ተከትሎ በ1970ዎቹ በአሜሪካ የተፈጠረውን የሰብአዊ መብት አጀንዳ እያጤነ በጥቂት የመንግሥት ችሮጀክቶች ላይ ሰርቷል፡፡ በኒዮርክ ደቡባዊ ቀጠና የአሜሪካ ጥብቅና ቢሮ ውስጥ እሰከማገልገልም ደረሰ፡፡

በ HRW ባልደረቦቹ የነገው ኮከብ እየተባለ የሚሞካሸው ወጣቱ ኬን ሮዝ ለ6 ዓመት ያህል ተቋሙን በምክትል ሃላፊነት ካገለገለ በኋላ በ1993 የዋና ሥራ አስፈፃሚነቱን ቦታ ያዘ፡፡ ወደዚህ ተቋም ያመጡት ዋና ሥራ አስፈፃሚው አሪዮህ ኔየር ሥራ ስለቀየሩ ነው ወጣቱ ኬን የተካቸው፡፡ እንግዲህ እዚህች ጋር የተደረገችው ሽግግር ናት ለ    HRW    የዛሬ ቅርፅና መልክ በምክንያትነት የምትጠቀሰው፡፡

በተለይም ዋና ሥራ አስፈፃሚው አሊዬህ ኔየር የሌላ ተቋም ሃላፊ ለመሆን ሥራቸውን የለቀቁበት ምክንያት የሽግግሯን ወቅት ጉልህ ያደርጋታል፡፡  የ open society Institute። ይህ ተቋም ደግሞ የቢሊየነሩ ጆርጅ ሶሮስ ነው፡፡ ጆርጅ ሶሮስ ማለት ደግሞ ቢሊዬነርና የopen society Institute ባለቤት ብቻም አይደሉም፡፡ ገናና ባለሃብት የበርካታ ግዙፍ ተቋማት ባለቤት ወዘተ በሚሉ መጠሪያዎች ብቻ የሚገለጽ አይነት ግለሰብም አይደሉም ።ጆርጅ ሶሮስ ለየት ያለ ማንነት ያላቸው ሰው ናቸው፡፡ ከ1993 ጀምሮ የያዙትን የዋና ሥራ አስፈፃሚነት መንበር ዛሬም እየመሩት ነው፡፡ ትናንት ያ ለቀዝቃዛው ጦርነት መሳሪያነት በእነሮበርት በርስቴይን ስብሰባ የተወለደው አነስተኛ ተቋም ዛሬ በ8 እጥፍ አድጓል፡፡
በእኚህ ሰው አመራርነት ወደ 80 ሃገራት የሚዘረጉ ቅርንጫፎች አብቀሏል፡፡ ዋናው የNew york    ጽ/ቤት እንዳለ ሆኖ በርሊን፣ ቤይሩት፣ብራስልስ፣ ቺካጎ፣ ጄኔቫ፣ ጁሃንስበርግ፣ ለንደን፣ሎሳንጀለስ፣ሞስኮው፣ፓሪስ፣ሳንፍራንሲስኮ፣ቶኪዮ፣ቶሮንቶ፣እና ዋሽንግተን ውስጥ ቢሮዎች አሉት፡፡

ለሰብአዊ መብቶች እውቅናና መጠበቅ የተጠየኩትን ሁሉ እከፍላለሁ የሚል፣ ከፈለገም የመንግስት ሹም ሽር እስከማካሄድ የደረሰ ጉልበት አለው እስኪባልለት ድረስ አቅሙን ያጎለበተ ተቋም ሆኗል፡፡ ዓለማችን ግዙፍ የምትላቸውን የሚዲያ ተቋማትን ሳይቀር በመዳፉ ያስገባ ተፅዕኖ አሳዳሪ ተቋም ሆኗል፡፡

የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ልዕለ ሃያል ይሉታል፡፡ An NGO Super power ይህ ሁሉ በዋና ሥራ አስፈፃሚው ኬኔዝ ሮዝ መሪነት የተገኘ ነው፡፡ ታዲያ ምነው ወደ ኬኔዝ ሮዝ ቢሮ የሚላኩ የተቃውሞና የትችት መልእክቶች ብዛት ለቁጥር ታከተ ለምን የፖለቲካ ቅጥረኛ፣ በሰብአዊ መብት ጥላ ስር የበቀለ የፖለቲካ ዛፍ የሚሉት በዙ ከመስራች አመራሮቹ ሳይቀር ስለምን የኬኔዝ ሮዝ HRW    ለትቶች ተጋለጠ ትችቶቹ በቀጥታ ከዋና ስራ አስፈፃሚው ኬኔዝ ሮዝ ጋርስ ለምን ተያያዙ እስቲ የሚከተሉትን ሶስት ተመጋጋቢ እወነታዎች በማያያዝ ለጥያቄዎቹ መልስ እንፈልግ
1.    Open Society  ከተባለው የጆርጅ ሶሮስ ተቋም ጋር ያላቸው ቁርኝት
2.    ድርጅታቸው የሚፈፅማቸው አነጋጋሪ ስህተቶችና የሚወስዳቸው አቋሞች
3.    ከመስራቶቹ ዘንድ የሚሰነዘሩ ተቃውሞዎች፡፡
ቀድም ብዬ ለማስታወስ እነደሞከርኩት የኬኔዝ ሮዝ እና የቢሊየነሩ ጆርጅ ሶሮስ ተቋም ዝምድና ራሱን በቻለ አብይ ርዕስ በስፋት የምመለስበት መሆኑን በድጋሚ በማስታወስ ለጥያቄዎቻችን መልስ የሚሆኑ እውነታዎቹን በጥንቃቄ(ሳይደጋገም) እንምዘዝ አንድ ሶስት ሰበዞችን እነሆ፡-
የመጀመሪያው ኬኔዝ ሮዝ የምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚነት ሥራቸውን ሲጀምሩ በአለቃቸው የተሰጣቸው ፕሮጀክት ነው፡፡ መጀመሪያውኑ ወደዚህ ተቋም የመጡት በዋና ሥራ አስፈፃሚው በኩል መሆኑን ሳንረሳ የመጀመሪያውን የኬኔዝ ሮዝ ፕሮጀክት ስም እንጥራ   የ Material ህግ በፖላንድ ያለውን አተገባበር መፈተሽ ይባላል፡፡ ኮሙዩኒስቱ የእነ ጀነራል ቼስላው መንግስት በዴሞክራሲ ስም እያደር የበረቱበትን ተቃዋሚዎች ለመከላከል ፓላንድን   በ Material ህግ ጥላ ሥር ሲያሳርፉት ነው፡፡ ወጣቱ ኬኔዝ ሮዝ የሂውማን ራይትስ ዎች ሰራተኛ ሆነው ወደ ዋርሳው ጎራ ያሉት፡፡ በወቅቱ በፖላንድ ዜጎች እየተጨቆኑ ነው፡፡ መብታቸውን እንዳይገልጹ በ    Material ህግ ሥም አፈና እየተደረገባቸው ነው ብሎ ለዓለም ሪፖርት ማድረግ፡፡ የምስራቅ አውሮፓን ኮሙዩኒዝም ለማዳከም ዋናው መንገድ ነበርና የኬኔዝ ሮዝ ተቋም በትክክል ይህነኑ ፈፀመ፡፡

ኮውዩኒስቶች የአለም መንግሥታት የሚከተሉትን የኢኮኖሚ ስርዓት እየነቀፈ(ወይም በፍፁም መንግስት ጣልቃ የማይገባበት) ገበያ መር ኢኮኖሚ ብቻ ዓለምን ይምራት እያለ በጆርጅ ሶሮስ መሪነት የሚንቀሳቀሰው open society ደግሞ ከነ ኬኔዝ ሮዝ ጀርባ ነበር፡፡ ድንግል ወዳላቸው የኮሙዩኒስት ግዛቶች ጆርጅ ሶሮስ ፊቱን ያዞረበት ወቅት፣ በምንዛሬ ሽፋን ገና ያልተጭበረበሩ በሚሊየን ያልተተረፈባቸው ባንኮችና የቢዝነስ ተቋማት ከዚያ ነበሩና ነው፡፡ ጆርጅ ሶሮስ ባንኮች ላይ ፈፅሟል የሚባለው ሴራ እዚህ ጋር በማብራሪያነት ይቅረብ፡፡ በጥቅሉ ሲቀመጥ open society የተባለው ተቋም አልያም ጆርጅ ሶሮስ ለፈለገው ምሥራቅ አውሮፓዊ ትርፍ እነ ኬኔዝ ሮዝ ከለላ ሆነው አገልግለዋል፡፡ ከአመታት በኋላም ቀደም ሲል ያነሳነው ምዕራፍ ተገለጠ፡፡ ዋና ሥራ አስፈፃሚው አሪዬ ኔየር ወደ open society ሲያመሩ ኬኔዝ ሮዝ ደግሞ ወደ HRW መንበር መጡ፡፡

ተደጋግሞ ይነሳሉ ሰውዬው ጎበዝ የህገ ባለሙያ ናቸው ፡፡ ነገር ግን በተቋማቸው የሚፈፀሙት ስህተቶችና ክፍተቶች ከአንድ በህግ ምሁር ከሚመራ ተቋም የሚጠበቁ አይነቶች አይደለም፡፡

በቀልን፣ የጦር ወንጀለኝነትን የሚመዝንበት ሚዛን ህጋዊ አግባቡ የተዳከመ እንደሆነ፡ collective punishment የተሰኘን የውንጀላ መንገድ በመጠቀም ብቻ ከህግ ጋር በመላተም አባዜው ይወቀሳል፡፡ የተለያዩ ሰዎችን በአንድ አይን ጨፍልቆ በማየት፣ ወይም አንድ አይነት ጉዳዮችን በተለያዩ አተያዮች የመመዘኛ አካሄድ (double standared) የተገዛ ተቋም የሚሉ ወቀሳዎችን መስማት የተለመደ ነው፡፡
"ንጉስ አይከሰስ" ይሉትን ሆኖባቸው እንጂ በርካታ ሃገራት ከተቃውሞአቸው በተጨማሪ የደለበ የክስ አቤቱታቸውን ይዘው ከፍርድ ቤት በቆሙ ነበር፡፡ HRW በኬኔዝ ሮዝ ከቬንዘዌላ እስከ ቻይና፣ከኢትዮጵያ እስከ እስራኤል፣ ከሁንዱራስ አስከ ኪዩባ፣ ከሩሲያ እስከ ሩዋንዳ የተፃፉ መአት የመከፋት ደብዳቤዎች ደርሰውታል፡፡ በፖለቲካዊ አተያይህ፣ በተዛባው ሚዛንህ፣ተከፍተንብሃል ተብሏል፡፡ በደካማና ኢስነምግባራዊ የምርምር ውጤቶቹ ከብዙሃን መገናኛዎች ጋር ተንቋል፡፡ ፖለቲካዊ የኋላ ታሪክ ያላቸውን አባላት በመመልመል ንፁህ የፖለቲካ ተቋም መሆንህን አስመሰከርክ ተብሏል፡፡ የገቢ ምንጮችን በይፋ ባለማሳወቅ ይከሰሳል፤ ከ    CIA    ጋር በአንድ መንገድ ይራመዳል ሲሉ የፃፉት ብዙ ናቸው፡፡ 

የሶስተኛውን ተመጋጋቢ እውነት ፍለጋ ወደ 1980ዎቹ መግቢያ አንመለስ፤ ይህ ታሪክ HRW ላይ የሚሰነዘሩት ተቃውሞዎች ሌላም መልክ እንዳላቸው የሚያሳይ ዋና ምሳሌ ነው፡፡ ወ/ሮ “cathrine Ritpartrick” ን ኬኔዝ ሮዝ ይረሷት ይሆናል፡፡ ተቋሙ ግን በፍፁም አይረሳትም። ወ/ሮ ካትሪን በ1980ዎቹ መጀመሪያ የHRW የምርምር Department ሃላፊ ነበረች፡፡ ከተቋሙ መሰረታዊ ክፍሎች አንዱ ነው የምርምር ዘርፉ፡፡ ማንም ባልጠበቀው ሁኔታ ወ/ሮዋ የሥራ መልቀቂያዋን አስገባች፡፡ ተቋሙም ምነው አላት የበጀት አሰባሰባችሁና አዲስ የቀየሳችሁት የአተያይና የአሰራር መስመሮች ስላልጣመኝ አለቻቸው፡፡ አዲስ ተብለው ከመዝገባችን በሰፈሩ ለጋሾች ማንነት ደስተኛ አይደለሁም ስትል ወ/ሮ ካትሪን በአደባባይ ትናገራለች፡፡ የወ/ሮዋ እርምጃ ለተቋሙ ውስጣዊ ክፍፍል እንደመጀመሪያ ምስክር ተወሰደ፡፡

የ Robert Bernsten    ግን ከዚህኛው መረር ያለ ነበር፡፡ በቅርቡ የመሆኑ ነገር ደግሞ ውዝግቡን ከረር እንዲል አድርጎታል፡፡ 2009 ላይ ነው፡፡ ጥቅምት ውስጥ፡፡ New York times ጋዜጣ ላይ ሮበርት በርስቴይን የተባለው ግለሰብ     HRW    ላይ የሰላ ትችታቸውን ሰነዘሩ፡፡ “ሚዛማዊ አተያዩን እያጣ መጥቷል” ሲሉ ነው ለፅሁፋቸው ርዕስ የሰጡት፡፡ በተለይም በእስራኤል ላይ የሚያወጣቸውን ሪፖርቶች በመጥቀስ፡፡  ሚዛኑን የሳተ ሲሉ ተችተውታል፡፡ በበርካታ የአረብ እና የመካከለኛው ምሥራቅ ሃገራት ላይ የሚያሳየውን ልልነትም እንደማነፃፀሪያ አቅርበው የHRW    ን ፍትሃዊነት ሞግተዋል፡፡ እንደመነሻቸው ሁሉ ጽሑፋቸውን የሚደመድሙት HRW ሚዛናዊነቱን አጥቷል ሲሉ ነው፡፡ ዋናው አስደንጋጭ ነገር ታዲያ HRW መወቀሱ     አይደለም፡፡ ያማ የተለመደ ነው፡፡ ወቃሹ Robert Berstein   መሆናቸው ነው ሁሉንም ያስገረመው። ምክንያቱም ከሄለሲንኪ ዎች ጀምሮ HRW ን የመሰረቱት እሳቸው ናቸውና፡፡ Robert Berstein  


ሂዩማን ራይትስ ዎች የምእራባውያን ሸፍጥ ማራገፊያ (ክፍል 3 )
ዮናስ
የዛሬ ሚዛናችንን በሚከተሉት አጫጭር አገላለፆች እንጀምረው፤ ከየት አንዳገኘኋቸው አስከትዬ እገልፃለሁ፡፡
ነጥብ አንድ፣ የሀብታሙን ሰውዬ ጋዜጣዊ መግለጫ ለመዘገብ ትላልቅ የሚባሉት ጋዜጠኞች አዳራሹን ሞልተውታል፡፡ አንድ ጥያቄ ለሃብታሙ ሰውዬ ቀረበ “ጌታዬ ስለቻይና ምን ታስባለህ” ተጠያቂው ለሰኮንዶች ዝም አለና ከአንገቱ ጎንበስ ብሎ በእርጋታ እንዲህ አለ “አዎ ቻይና - - - በቻይናውያን የተሞላች ናት” በቃ ይሄንን ነው የመለሰው፡፡ ጋዜጠኛው ግን በመደነቅ አጉረመረመ፣ አዎ ምን አይነት ጂኒየስ ነው ተባባሉ፣ጋዜጠኞች፡፡ አዎን ገንዘብ ካለህ እንዲህ አውርተህም ጂንየስ ትባላለህ፡፡
ነጥብ ሁለት፣ አንድ ሀብታም ሰውዬ በዚህ የተከበረ የራት ግብዣ ላይ ለብሶት የመጣው ልብስ በጣም አስቀያሚ ነው፡፡ አስቀያሚ ስለመሆኑ ህፃን ልጅ እንኳን ለይቶ መፍረድ ይችላል፡፡ የከበቡት ሰዎች ግን በእርግጠኝነት እንዲህ ነው የሚሉት “ወይኔ እንደሱ መልበስ ሲገባን እንዲህ አስቀያሚ ሆነን መምጣታችን” አዎን ገንዘብ ካለህ እንዲህ ይባልልሃል፡፡
ነጥብ ሦስት፣ አህያን እስክትንበረከክ የገንዘብ ክምር ብትጭናት ያው     ከአህያነቷ አትለወጥም (“ If you put a pile of cash upon a donkey’s back under neath it, he is still a donkey”)
ሦቱንም ሃሳቦች Jewish world review. com ከተባለ ድህረ ገፅ ነው ያገኘሁት፣ የገረመኝ ወይም በትኩረት እንዲታይልኝ የፈለኩት የሃሳቦቹን መልዕክት ብቻ አይደለም፡፡ ሃሳቦቹ ምን ለማብራራት ጥቅም ላይ እንደዋሉ እንጂ፡፡
ሁሉም ሃሳቦች ስራ ላይ የዋሉት ስለ ቢሊየነሩ የሃንጋሪ ተወላጅ አሜሪካዊ ጆርጅ ሶሮስ በሚያወራ አንድ ጽሁፍ ላይ ነው፡፡ “The story tale of George sorose” ይላል ጽሁፉ፡፡ በግርድፉ "የጆርጅ ሶሮስ ወግ" ልንለው እንችላለን፡፡ ጽሁፉ በደጋፊዎች ዘንድ እጅግ የተከበረውን ቢሊየነር ሰው በሰላ ትችትና ተቃውሞ ያጣድፈዋል፡፡
ባለፀጋ ስለሆነ ብቻ የማይረባ ነገር ቢናገረም  ጋዜጠኞች የሚያጨበጭቡለት አሳዛኝ ሰው፣ “ሃብታም በመሆኑ ብቻ የወደቀ የማይመስለው ሁሌ ትክክል እንደሆነ የሚያስብ ብኩን ሰው፣ “እስኪንበረከኩ ገንዘብ ሲጫኑ ብቻ ማንነታቸውን በካዱ አጃቢዎቹ የሚከበብ” ወዘተ - - - እያለ ያለምንም ርህራሄ ይወቅሰዋል፡፡
ደጋፊዎቹ ግን ደህን አይሉትም ጆርጅ ሶሮስ ለእነሱ በጥልቅ እሳቤዎች የተሞላ ፈላስፋ ነው፡፡ ከልጅነቱ ጀምሮ በሚያስደንቅ ስኬት የተጓዘ ድንቅ የንግድ ሰው ነው፡፡ በዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብ የተሞላ ፓለቲከኛ ነው፡፡ ከማንም ጋር ተወዳድሮ የማሸነፍ ፈጠራ የታደለ ሰው፣ የሚሰራውን የሚያውቅ፣ የማያውቀውን የሚሰራ የአለማችን እጅግ አስፈላጊ ሰው ነው፣ ለደጋፊዎቹ፡፡
ለመሆኑ ሰውዬው ማን ነው እነዚህ ተቃራኒ ሃሳቦች ከየት መነጩ በተለይ ወቀሳዎቹ ለምን ኮስተር ያሉ ሆኑ? ዕድሜ 81፣ ዜግነት፦ሃንጋሪ አሜሪካዊ ፣የሀብት መጠን ፦22 ቢሊየን ዶላር።
በ2011 - በፎርብስ ዘገባ መሰረት የዓለማችን 46ኛ ከአሜሪካ 10 ባለፀጎች ደሞ አንዱ፡፡
በጎ አድራጎት፣ ኢንቨስትመንትና ንግድ  ከስሙ በፊት የሚመጡ ዋና ዋና መገለጫዎቹ ናቸው የጆርጅ ሶሮስ።   “የኢኮኖሚያዊ ጦርነት ወንጀለኛ” “Economic war criminal” የማሌዢያው ጠ/ሚ/ው ማሃቲር ሊን መሀመድ ያወጡለት ቅፅል ስም።  “የአንግሊዝን ባንክ የሰበረ ሰው” “The man Who Broke the Bank of England” አለም በሰፊው የማያውቀው ሌላው ቅፅል ስሙ፡፡
ማንም ሊክድ አይችልም፡፡ ጆርጅ ሶሮስ ማለት ገና በ14 አመቱ በናዚ ተቋማት በቋሚነት ተቀጥሮ ይሰራ የነበረ ታማኛቸው ነበር፡፡ ከተቀጣሪነት አምልጦ ወደ ዛሬ ማንነቱ የተጓዘባቸውን መንገዶች የመረጠባቸው አጋጣሚዎችና አካሄዶችም   የሚያስቀኑ ናቸው፡፡ የታታሪና የአዋቂ ማንነት ምልክቶች፡፡ ተናጋሪና ኃይለኛ ነው ይሉታል፣ ችግሮቹ መገላለጥ የጀመሩት ግን ሶሮስ በጎልማሳነቱ ከመካከለኛ ነጋዴነት ወደ ቢሊየነርነት ሽግግር ባደረገባቸው በእነዚያ ጊዜያት ነው ይሉናል  በርካታ የሶሮስ ተቃዋሚዎቹ፡፡
እርሱ ወደ ብልጽግና መሸጋገር የጀመረበት ወቅት ደግሞ የቀዝቃዛው ጦርነት ግለት የተፋፋመበት፣ የሁለቱ ፓለቲካዊ ርዕዮተ አለም ግብግብ የከረረበት፣ በጥይት ከመታኮስ ይልቅ ጦርነት ወደ ጥይት አልባ ፓለቲካዊ ንዝረትና ፍትጊያ የተቀየረበት ወቅት ነበር፡፡
ከ(1956-63) አማካሪ ሆኖ በኒውዮርክ በሰራባቸው አመታት “Reflexivity” ያለውን ንድፈ ሃሳብ ፈጠረ፡፡ ከዕውቁ ካርል ፑፐር በተወሰዱ የመነሻ ሃሳቦች የተፀነሰው የሶሮስ “Reflexivity” እንዲህ የሚል አስኳል ነበረው፡፡
“በየትኛውም ገበያ አልያም ሸቀጥ የሚሰጠው ሁለንተናዊ መለያ ዋጋና ደረጃ (Valuation) ገበያን ሊጎዳ የሚችል ሌላ አደገኛ ዑደታዊ (pocyclical) የሆነ መልክ ይኖረዋል የሚል ነው፡፡ ይህ ከማህበረሰብ ሳይንሱ የ “Reflexivity” እሳቤ በብዙ መልኩ የተቀዳው የኢኮኖሚክስ ፍልስፍና የሰውዬውን የዛሬ ማንነት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ መስታወት ነው፡፡
በአንዳንድ የአክስዮን ገበያ ውስጥ ያለውን ሂደት በእውቀት፣ በብልጠት ባስ ሲልም በተንኮል አይን እየተከታተሉ ትርፍ የመሰብሰብ፤ ነገ እንዲህ ሊሆን ይችላል በሚል ግምት የዓለምን፣የሀገራትን የኢኮኖሚ አቅጣጫ እያነበቡ ንግድን በሃይለኛ ትርፍ ማጧጧፍ የሶሮስ መለያ ሆነ፡፡ እንግሊዛውያን “ጨለማው ዕሮብ” (Black Wednesday) የሚሉት መስከረም 16 ቀን 1992 ለጆርጅ ሶሮስ ታላቁ የብርሃን ቀን ነበር፡፡
ከጀርመን ውህደትና ከደች ማርክ የገንዘብ አቅም መጠንከር ጋር ተያይዞ ከቀናት በኋላ የእንግሊዝ ፖውንድ የምንዛሪ ጉልበቱ እንደሚንኮታኮት የገመተው ሶሮስ በሁኔታው ግራ በተጋባውና ጥርጣሬ ውስጥ ለነበረው የእንግሊዝ መንግስት የ10 ቢሊዮን ፓውንድ አክስዮኖቹን ሸጠላቸው፡፡
ከቀናት በኋላ “በጨለማው ዕሮብ” የሶሮስ ግምት ልክ ሆነ። ፓውንድ አውሮፓውያን የግብይት ጣሪያ መንካት አቅቶት ከሌሎቹ ጋር መወዳደር ተስኖት ወደቀ፡፡ ዮናይትድ ኪንግደም እስከ 3.4 ቢሊዮን ዶላር ከሰርኩ አለ። ከዚህ ኪሳራ ግን ጆርጅ ሶሮስ 80 በመቶ አትርፏል፡፡
ስለዚህም ነበር እንግሊዛውያን የሶሮስን ስም “ባንኮችን የሰበረ (The man who Broke the Bank of England)”   በሚል የተኩት። ከዚያ ምኑ ቅጡ የሶሮስ እጅ እስከ ኤዥያ ድረስ መዘርጋት ጀመረ፡፡ የ1997ቱ የኤዥያ የፋይናንስ ቀውስ በዋናነት የተመራው በሶሮስ ነው የሚሉት የወቅቱ የማሌዥያው ጠ/ሚ/ር ማሃቲር ቢን መሀመድ  ማይናማርን የደቡበ ምስራቅ ኤዥያ ሀገራት ማህበር (ASEAN) አባል በማድረጋችን የተበሳጨው ጆርጅ ሶሮስ በስሩ ያለውን ግዙፍ ሃብት በመከልከለና እንዳይንቀሳቀስ በማድረግ ከፍተኛ ቅጣት አድርሶብናል ይላሉ፡፡
የምንዛሬ ዋጋ እንዲያሽቆለቁል ሚናውን የተጫወተው አይሁዱ ሰውዬ ነው ሲሉ ጆርድ ሶሮስን በአደባባይ ወቅሰውታል፡፡ በእርግጥ ከአመት በኋላ 2006 ላይ ጠቅላይ ሚንስትሩ እና ሶሮስ በአካል ተገናኝተው ለንግግራቸው ይቅርታ ጠይቀውታል፡፡ ያንተ እጅ የለበትም ብለው አምነዋልም ተብሏል፡፡
ዋናው ጥያቄ ግን የሁለቱ ሰዎች ይቅርታ መባባል አይደለም፡፡ የማሌዢያው ጠቅላይ ሚኒስትር ውንጀላ እንበለው ጥርጣሬም በይቅርታ የሚሸፋፈን አለመሆኑ ነው፡፡ “ልብ በሉ ማይናማርን የማህበራችን አባል ስላደረግን፤ ሶሮስ ተበሳጭቶብን በህልውናችን ላይ ፈርዶ ነው፡፡”  ነው ያሉት ሰውዬው፡፡ ይህ ማለት የጆርጅ ሶሮስን የዛሬ ማንነት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ሌላኛው፤ ምናልባትም እጅግ በጣም ትልቁ መስታወት ነው፡፡
ምክንያቱም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥቆማ ሁለት ነገሮችን በግልጽ ስለሚያሳይ አንደኛው የሶሮስን ፓለቲካዊ ፍላጎት፣ ሁለተኛው የሶሮስን ጉልበተኛነት ወይም የአቅም ግዝፈት። በተለይ የመጀመሪያው ጉዳይ የሶሮስ ፓለቲከኛነት ወደ መጣጥፌ ፍሬ ሃሳብ በቀጥታ ስለሚያስጉዘን እንከተለው፡፡
ሶሮስ ማይናማርን ለምን ጠላት
የመጀመሪያውና ቅልብጭ ያለው መልስ ሶሮስ ኮሙዪኒዝምን አይወድም የሚለው ነው፡፡ የግለሰቦችና የባለሃብቶች ጣልቃ ገብነት የተንሰራፋበት የኢኮኖሚ ስርዓት እንዲስፋፋ፣ ዲሞክራሲያዊ በሚል የአስተሳሰብ ጥላ ስር የህዝቦች ሃሳብን የመግለጽ፣ የመቃወም፣የመደገፍ መብት እንዲጎለብት እፈልጋለሁም፣ እተጋለሁም ይላል ሶሮስ፡፡ ይህ በእርግጥ የማንኛውም ጤነኛና ምክንያታዊ ሰው አመለካከት ነው፡፡ የማንኛውም መንግሥትና ሃገር ግዴታም ጭምር፡፡ ችግሩ ግን ኮሚዩኒዝምና የሶቭየት ህብረት ርዕዮተ ዓለም ይሄንን አያሟሉም ብሎ ማሰቡ ላይ ነው፡፡
ከዚያ ደግሞ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ማለት ይሄ እኔ የማሳያችሁ አቅጣጫ ነው ብሎ መሟገትና ለመርታት ደፋ ቀና ማለቱ ላይ ነው፡፡ ጆርጅ ሶሮሰ የሁለቱም ችግሮች ባለቤት ተብሎ በተደጋጋሚ ይወቀሳል፡፡ ለዚያም ነው open society የተባለውን ግዙፍ ተቋም የመሰረተው።
በትምህርት፣ በሚዲያ፣ በምርምርና ጥናት፣ በዴሞክራሲ ግንባታና በመሰል ዘርፎች የሚሰራ፤ በምድራችን በነፃነት የሚያስቡ በዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ የበለፀጉ ህዘቦች እንዲበዙ የምንቀሳቀስ ተቋም ነኝ ይላል open society፡፡
ይህ ተቋም ባለፉት 20 ዓመታት ብቻ 8 ቢሊዮን ዶላር በእርዳታ መልክ ለተለያዩ ተቋማት ሰጥቷል፡፡ ከሃብቱ አንድ ሶስተኛ በላይ የሚሆነውን ሰጥቷል ማለት እኮ ነው። እናም እንዲህ ሆነ፤
በዴሞክራሲ ግንባታ ስም ከጆርጅ ሶሮስ ክምር ዶላሮች አብዛኛውን የወሰዱት የምሥራቅና የመካከለኛው አውሮፓ ሃገራት ሆኑ፡፡ በግልጽ ሲቀመጥ የቀድሞ የኮሙዩኒስት ሃገራት በምዕራባውያኑ ዘንድ የቀዝቃዛው ጦርነት የድል ሜዳ የነበሩት ሃገራት የሶሮስን እርዳታ በተለያየ ሽፋን ተቀበሉ ማለት ነው፡፡
ሰብአዊ መብትን በሚያቀነቅኑና ዴሞክራሲን በሚሰብኩ ተቋማት ስም እየታሸገ የሶሮስ ዶላር ወደ ምዕራባዊው መንግሥታቸው ካዝና ገባ፡፡ ከሃገሩ ሃንጋሪ ጀምሮ በተለያዩ ሃገራት በ open society ስም የተገነቡ ግዙፍ የትምህርት፣ የምርምር እና ጥናት፣ የሚዲያና የልማት ተቋማት ሁሉ progressive liberal በተሰኘው የሶሮስ ፖለቲካዊ አተያይ መሰረት የታነፁ ናቸው፣ ብለው የሚሟገቱ ወገኖች የመብዛታቸው ምስጢርም በቀጥታ ከዚህ ጋር ይያያዛል፡፡
የሌሎቹን ሃገራት ትተን ለ gorgia የቀለም አብዮት መሳካት እንደ ጆርጅ ሶሮስ ከፍተኛ ሚና የተጫወተ እንደሌለ በአደባባይ ተሰምቷል፡፡ ሊያውም ከሚገርም አንድ አጋጣሚ ጋር፡፡
አጋጣሚው ምን መሰላችሁ ከ ጆርጂያ የቀለም አብዮት መሪዎች መካከል አሌክሳንደር ዋና ናቸው፡፡ እሳቸው ማለት በቀለም አብዮት ለተወለደችው ጆርጂያ የደህንነት ካውንስል ሃላፊና የሳይንስና የትምህርት ሚንስትር የነበሩ ናቸው፡፡ የሚያስገርመው ነገር ግን ይሄ አይደለም፡፡ ሚንስትር ከመሆናቸው በፊት በጆርጅያ ሶሮስ ፋውንዴሽን ሃላፊ የመሆናቸው ነገር እንጂ፡፡ ሶሮስ እዚህ ድረስ በሃገራት ማንነት ውስጥ ጣልቃ የመግባት አቅም ያለው መሆኑ ዋናው ጉዳይ፡፡
በካዛኪስታን፣  በቱርክና በቤላሩስ የ Sores open society ለምን ተቃውሞ ገጠመው ለምንስ ሳይቋቋም ቀረ ብለን ስንጠይቅ ምላሹ አንድ አይነት ነው፡፡ በሃገራችን ፖለቲካ ጣልቃ አትገባም የሚል ብቻ፡፡
የጆርጂያውን ሚንስትር ጉዳይ ግን ልብ ካላችሁት በክፍል ሁለት መጣጥፌ የነገርኳችሁን  ጉዳይ በግልጽ ያስታውሰናል፡፡ የ HRW አዲሱ ኮከብ ኬኔዝ ሮዝ ወደስልጣን ሲመጡ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ የነበሩት አሪየን ኔይር ወዴት ሄዱ ነበር ያልነው ወደ open society    ፡፡
ኬኔዝ ሮዝም ቢሆኑ ከ HRW    በፊት በምስራቅና በማዕከላዊ አውሮፓ የፀረ ኮሙዩኒዝም ዘመቻ ውስጥ የራሳቸው ተልዕኮ ነበራቸው፡፡ ልክ እንደጆርጅ ሶሮስ open society፡፡
እነሆ ላለፉት 20 ያህል ዓመታት በዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ የተጠቀለሉትን የሶሮስ ፖለቲከኛ ዶላሮች ከተቀበሉ በርካታ ድርጅቶች ዝርዝር ውስጥ የ HRW ስም ከመጀመሪያው ተርታ ተገኘ፡፡ ከቀዝቃዛው ጦርነት ዘመቻ ጀምሮ በጠንካራ ጥምረት ይኸው አብረው እንደዘለቁ ነው፡፡ ሶሮስ በሰፊው ተቆጣጥሯቸዋል በሚባሉት የዓላማችን ሚዲያዎች ላይ በቀረበ ቁጥር ስለ HRW ታላቅ ተቋምነት ይመሰክራል፡፡ እንዳውም ባለፈው አመት ለቀጣይ 5 ዓመታት 500 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ ለ HRW     እሰጣለሁ ብሏል፣ ቱጃሩ ጆርጅ ሶሮስ፡፡ ይህ ልገሳው የ HRWን በጀት ሁለት እጥፉ ከፍ እንደሚያደርገው ልብ ይሏል፡፡ አሁን ማጠቃለያችን ቀለል ያለ ይመስለኛል፡፡
ስለዚህ በሁለት ማጠቃለያዎች  መጣጥፌን ለመዝጋት ፈለኩ፡፡ የመጀመሪያው  HRW ያው ከአመሰራቱ ጀምሮ ፖለቲካዊ መልከ አለው፡፡ በሰብአዊ መብቶች ጥላ ሥር ፓለቲካዊ አጀንዳ ለማራመድ የተቋቋመ ነው ካልነው HRW ጀርባ ጆርጅ ሶሮስ በደማቁ መፃፉን፡፡
ሁለተኛው ማጠቃለያዬ ግን የእኔ አይደለም፡፡ የታዋቂው ኢኮኖሚስት ptklugman ነው፡፡ በአንድ ወቅት የፋይናንሱን ገበያና የሶሮስን ተጽዕኖ የገለጹበት መንገድ ግርምት የሚያጭር ነበር፡፡ “ከቅርብ አመታት ወዲህ ማናቸውንም የቢዝነስ መጽሄት የሚያነብ ሰው የእነዚህን ሰዎች ሥራ በግልጽ ይረዳዋል፡፡
ሰዎቹ በደፈናው ኢንቨስተሮች ይባላሉ፡፡ የፋይናንሱን ውድቀትና መነሳት እየጠበቁ ብቻ አይደለም ሥራቸውን የሚሰሩት፡፡ እራሱ የፋይናንስ ቀውስ እንዲፈጠር ይለፋሉ፡፡ በገበያው ውስጥ አለመረጋጋት እንዲሰፍን ይሰራሉ፡፡
ለእነዚህ አዳዲስ ተዋናዮች እስካሁን ስም አልወጣላቸውም፡፡ በነገራችን ላይ እኔ ግን ሃሳብ አለኝ፡፡ ጆርጅ ሶሮስ መባሉ ቀርቶ ለምን "መከራው (sorrow)"አይባልም?!!