መልካም ግንኙነት ለጋራ ተጠቃሚነት

  • PDF

ከሃብታሙ

ኢትዮጵያ በመልካም ግንኙነት ላይ የተመሰረተና የኖረ ተሞክሮ ካላቸው አገራት በግንባር ቀደምትነት የምትጠቀስ አገር ናት፡፡ በቅርብ ካሉት አዋሳኞቿ ማለትም በመልክዓ ምድራዊ ድንበርተኞቿ ወይም አጎራባቾቿ የአህጉሩ ወይም ደግሞ የአፍሪቃ አገራት ተጠቃሽ ሆናለች፡፡ የአገራት ለአገራትና የህዝብ ለህዝብ የእህትማማችነትና የወንድማማችነት ግንኙነቷ የጠነከረና በተለይም ከቅርብ አጎራባቾቿ ጋር በመቻቻልና በመልካም ጉርብትና በቀና የትብብር መንፈስ በሰላምና ሰላምን በተመለከቱ ተልዕኮዎች ከየትኛውም የቀጣናው አገራት የተለየ ስፍራ ያላት አገር ናት፡፡

ኢትዮጵያ ዛሬ ዛሬ በዓለም የሰላም መድረኮችና በትብብር መስክ እንዲሁም በአህጉሩ እንደ ኢጋድ የመሳሰሉ የትብብር መድረኮች ጉልህ ሚና ከሚጫዋቱ አገሮች ግምባር ቀደም ናት፡፡ በተለይ በሰላም ማስከበር ተሳትፎዋ ለአህጉራዊና ዓለም አቀፍ ሰላም ሌት ከቀን የምትሰራና ይህም ጽኑ አቋሟ በትውልዶች መካከል በቅብብሎሹ እየተላለፈ የመጣ ነው። በቀደምት ዓመታት በኮሪያና  በኮንጎ፣ በአሁኑ ትውልድ ተሳትፎዋ በሩዋንዳ፣ ብሩንዲ፣ ላይቤሪያና ሱዳን እንዲሁም በሶማሊያ ሰላምን ለማስፈንና ዓለም አቀፍ ሽብርተኝነትን ለማምከን እየተደረጉ ባሉ ዓለም አቀፍና አህጉራዊ የሰላም ማስከበር ተልእኮዎች ባላት ተሳትፎ  ከግምባር ቀደም የዓለም ሃገራት አንዷ፣ከአፍሪካ ደግሞ ቀዳሚ አድርጓታል።

በሌላም በኩል ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ የትብብር ዘርፍ በአገሪቱ ታሪክ ልዩ በሆነ ሁኔታ የተጠናከረ ስራ እየሰራች ትገኛለች። በዚህም እንደ አብነት ሊጠቀሱ የሚችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ሲሆን እንደ አንድ ማሳያም ሊጠቀስ የሚችል ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ የኤሌክትሪክ ኃይል ወደ ጅቡቲ፣በቅርቡም ወደ ሱዳን የመሸጥ ፋና ወጊ ትብብር እያደረገች ነው። በቀጣይም ለኬንያ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ለማድረስ የሚያስችል ስራ በመከናወን ላይ ይገኛል። ኢትዮጵያ ከውስጥ ጉዳይዋ ባልተናነሰ ሁኔታ  የአፍሪካም ይሁን የዓለማችን የሰላም ዋስትና እንዲረጋገጥ በትኩረት እየሰራች ነው፡፡ የአገሪቱ ዜጎች ተቀዳሚ አጀንዳቸው ሰላም እንዲሆንና በዚህም ከማንም በላይ ተጠቃሚዎቹ ራሳቸው ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ግንዛቤ ፈጥራለች፡፡ ለዚህ ያላሰለሰ ሰላማዊ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት መጎልበት ቁልፉን ሚና  የተወጡት ደግሞ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር አቶ መለስ ዜናዊ አመራር ኢህአዴግ መራሹ መንግስትና የአገሪቱ ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ናፋቂ ህዝቦቿ ናቸው፡፡

የአገራት ለአገራት የሰላምና የኢኮኖሚ ግንኙነትን በጠንካራ መሰረት ላይ ለመገንባት የአገራት መሪዎችና ዜጎች ምትክ የሌለው ሚና አላቸው፡፡ እናም መንግስታት የሚመሩትን አገርና ህዝብ ሰላም፣ ልማት፣ እድገትና ብልፅግና ብሎም ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ተግባራዊ ለማድረግ የሚጥሩ መሆን ይገባቸዋል፡፡ ከመንግስታት ግንኙነት ባለፈም የህዝብ ለህዝብ ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ማለትም ለንግድና ኢንቨስትመንት ትብብሮች ሰፋፊ መሰረቶች መጣል አለባቸው፡፡ አገራችን ኢትዮጵያም በዚህ ረገድ በርካታ ፍሬያማ ስራዎችን እያከናወነች ትገኛለች፡፡

ኢትዮጵያ አንዱ ግቧ አድርጋ በጽናት እየተንቀሳቀሰችበት ያለው የጎረቤት አገራትንና  የአፍሪቃን በአጠቃላይም የዓለም ሰላምን የማረጋገጥ ጥረቶቿ ከሰላም ወዳዶች ጎራ አሰልፏታል፡፡ በአሁኑ ወቅት እንደ ኢጋድና ሌሎች ዓለም አቀፋዊና አህጉዊ የትብብር መድረኮች ላይ ያላትን ንቁ ተሳትፎ አጠናክራ እንደምትቀጥል የእስካሁኑ እንቅስቃሴዋና በዚህ ረገድም መንግሥት የያዛቸው ቀጣይ ዕቅዶች አመላካቾች ናቸው። 

በሌላ በኩል መላው አፍሪቃውያን የታቀፉበትና የአህጉሩን የወደፊት ዕጣና ራዕይ በተመለከተ የሚመክሩበት የራሳቸው የአፍሪቃውያን ትሩፋት በሆነው  የአፍሪካ ህብረት ውስጥ ያላት ጉልህ ሚናም እዚህ ላይ ሊጠቀስ የሚገባው ነው፡፡ ለቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መመስረት በሃሳብ አፍላቂነት ብሎም ሃገራቱን ከማስተባበርና በተለያዬ መልኩም ሰፊ ድጋፍ ከመስጠት ጀምሮ ድርጅቱ አሁን እስከደረሰበት የዕድገት ደረጃ እንዲደርስ በተጓዘበት ሂደት ድንቅ ታሪክና ህያው ስም ያላት ናት፡፡ ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት ወደ አፍሪቃ ህብረት ለተደረገው ሽግግር እጅግ ወሳኝና በሳል ሃሳቦችን ከተግባራዊ እንቅስቃሴዎች ጋር ያበረከተች ናት።

ኢትዮጵያ በሁለንተናዊ መልኩ ለኢንቨስትመንት ያላትን ምቹነትና ተመራጭነት፣ በዓለም አቀፍ ደረጃም እያገኘች የመጣችውን ሰፊ ተደማጭነት እንዲሁም የሕዝቦቿን በጎነት የተመለከቱና የተገነዘቡ በርካታ የውጭ ባለሃብቶች አገሪቱን የኢንቨስትመንት መዳረሻቸው እያደረጓት መጥተዋል፡፡  ዛሬ ዛሬ በርካታ አገራት በተለይም ትላልቆቹ የኤሺያ አገራት በአገራችን የኢንቨስትመንት ዘርፍ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አግኝተው አገራችንን በሚጠቅም ስራ ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡

በዚህ በኩል በግንባር ቀደምትነት ተጠቃሽ ከሆኑት የኤሺያ አገራት መካከል ቻይናን ማንሳት ተገቢ ነው፡፡ ታላላቅ የቻይና ኩባንያዎች በአገራችን የተለያዩ  የኢንቨስትመንት ዘርፎች  ለምሳሌ በመንገድ ግንባታና በሌሎች መስኮች በስፋት ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡ ቻይና ዛሬ የዓለማችንን ኢኮኖሚ በሁለተኛነት የምትዘውር ታላቅ አገር ናት፡፡ በአገራችን በኢንቨስትመንት ሰፊ ተሳትፎ ያላት መሆኑም ከሥራ ፈጠራና የውጭ ምንዛሪ ግኝት ባሻገር ለተሞክሮ፣ ለስራ ልምድና ባህል፣  ለዕውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ያለው ፋይዳ ከፍተኛ ነው።፡፡

ኢትዮጵያ በብልፅግና ማማ አናት ከተፈናጠጡ የዓለማችን ኃያልና ፈርጣማ የኢኮኖሚ አቅም ካላቸው አገራት ጋር ያላት ግንኙነት እጅግ ወሳኝ  ነው፡፡ የመልካም ገፅታ ግንባታና የመልካም ግንኙነት ፋይዳ የሚገባቸውና የሚታያቸው ሰፊ እቅድ፣ ብሩህ ተስፋና ራዕይ የሰነቁ መሪዎችና ህዝቦች በቅንጅት የሚያለሙት አገር እድገቱ የተፋጠነ ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያም ዛሬ የተፈናጠጠችበት  ባለብዙ አክናፍ የዕድገት ፈረስ ደከመኝ ልረፍ፣ ልራገፍን አያውቅም፡፡ ዓላማው የሰላምና የዴሞክራሲ የልማትና የዕድገት ራዕይ ያነገቡትን ህዝቦች በፍጥነትና በአቋራጭ ካሰቡበት ማድረስ ነው፡፡
ይህ ለአገራችን ፈጣን የልማት ግስጋሴና የመልካም ግንኙነት ተምሳሌትነት አንዱማሳያ ሆኗል፡፡ ይህም አገራችን ከቅርብ አጎራባቾቿ የአፍሪካና ሌሎች አገራት ጋር በሁለትዮሽ የጋራ ወዳጅነት ዙሪያ ያላት ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙት  በጠንካራ መሰረት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን አስችሏታል። በመልካም ግንኙነትና ጉርብትና መንፈስ በቁርጠኝነት እየተንቀሳቀሰች በመሆኗም በሰላም በልማት በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ በኢኮኖሚውና በኢንቨስትመንቱ ዘርፍ ላቅ ያለ ሚና በመጫወት ላይ ትገኛለች። ኢትዮጵያ ከድህነት ፈጥና ለመውጣት በተያያዘችው የዕድገት ራዕይ መሰረትም ይኸው ሂደት በቀጣይ አሁን ካለው በላይ ተጠናክሮ ይቀጥላል።

በህዝብ ለህዝብና መልካም ግንኙነት በተለይ በሰላምና በኢኮኖሚያዊ ገፅታዎች ዙሪያ ከምንጊዜውም በበለጠና በላቀ ሁኔታ ጠንክራ እንደምትሰራ እንዲሁም ህዝቦቿ ለዚሁ ፈርጀ ብዙ እቅድና ግብ ወደ ላቀ ደረጃ መድረስ በተለይ ከሌሎች መሰል አገራት ህዝቦች ጋር ትስስርን የመፍጠር ራዕይን እውን የማድረግ ተግባር ማከናወን ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ የሌሎች አገራት ዜጎች በኢንቨስትመንቱም ይሁን በግንባታው ዘርፍ ተሰማርተው በሰላም እንደሚኖሩት ሁሉ የአገራችን  ዜጎች ሰርተን እንለወጣለን፣ የአገራችንን ስም በመልካም ገፅታ እናስጠራለን፣ ለወገኖቻችንም እንተርፋለን ብለው በሚያምኑበት አገር በሰላም እየኖሩ እንዲሰሩና ሃብት እንዲያፈሩ ከዚያም መልስ በአገር ቤት በተለያዩ ልማቶች በመሰማራት እንዲንቀሳቀሱ ለማስቻል የተጠናከረ ስራ መስራት ይገባል፡፡ ለዚህም  መንግስት በፈጠረው ምቹ ሁኔታ ከሁላችንም የሚጠበቀው የዜግነት ድርሻችንን በብቃት በመወጣት አገራዊ ራዕያችንን እውን ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡