ባለፉት አምስት ወራት ከ61 ሺ በላይ የሚሆኑ ዜጎች የማህበራዊ አገልግሎት መሠጠቱ ተገለጸ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 4/2005(ዋኢማ) - የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለፉት አምስት ወራት 61ሺ ለሚሆኑ አቅመ ደካማ ዜጎች የማህበራዊ አገልግሎት መሥጠቱን አስታወቀ።

የሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነትና ኮሚኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ግርማ ሸለመ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት፤ አገልግሎቱ የተሰጠው ለአረጋዊያን፣ ለህፃናትና ቤተሰቦቻቸው፣ ለጎዳና ተዳዳሪዎች፣ ለአካል ጉዳተኞችና ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ነው።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ 9 ሺ 933 ለሚሆኑ አካል ጉዳተኞች የአካል ድጋፍ ቁሳቁስና የፊዚዮ ቴራፒ አገልግሎት እንዲያገኙ ማስቻሉን ገልፀው፤ ህብረተሰቡ የሚያጋጥመውን የማህበራዊ ችግሮች ለመቅረፍ ከ1 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት መሰጠቱን ተናግረዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል ከፍተኛ ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልፀው፤ ዝውውሩን ለመግታት ከክልል መስተዳድሮች ጋር በትብብር በመሥራት ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
በፌዴራል ደረጃ የሚወጡ ፖሊሶዎችና ደንቦችን በተገቢው መንገድ ተግባራዊ ለማድረግ በክልሎች የተጠናከሩ ሥራዎችን መሥራት እንደሚያስፈልግና ሁሉም ህገ-ወጥ ዝውወርን ለመከላከል የድርሻውን መወጣት እንደሚገባው አሳስበዋል።

ኢትዮጵያውያን ወደ አረብ ሃገራት ከመሄዳቸው በፊት በሃገር ውስጥ የግማሽ ቀን ሥልጠና ብቻ ይሰጥ እንደነበረ የጠቀሱት አቶ ግርማ ወደፊት ግን ከሁለት እስከ ሶስት ወር የሚደርስ ስልጠና እንዲያገኙ እየተደረገ ነው ብለዋል።