ሚኒስቴሩ መሰረታዊ የስራ ሂደት ለውጥን በተሻለ ሁኔታ ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችሉ አቅጣጫዎች አስቀመጠ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 4/2005(ዋኢማ) - መሰረታዊ የስራ ሂደት ለውጥ ወይም ቢፒአርን በተሻለ ሁኔታ ውጤታማ ማድረግ የሚያስችሉ የተለያዩ አቅጣጫዎች መቀመጣቸውን የሲቪል ሰርቢስ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በሚኒስቴሩ የኮሙኒኬሽንና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መሃመድ ሰይድ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት፤ ውጤት ተኮር ስርዓት ወይም ቢኤስሲ ለውጡን በተሻለ ሁኔታ ውጤታማ ለማድረግ የተቀየሰ አንዱ ስልት ነው።

በዚህም አንድ ተቋም የሚሰጠውን አገልግሎት፤ የሚሰጥበት የጊዜ ርዝመትና ከተገልጋዩ የሚጠበቀውን ግዴታ በግልጽ ያሳውቃል ብለዋል።

በየተቋሙ የለውጥ ሠራዊት ማቋቋምም ሌላው አቅጣጫ እንደሆነ የተናገሩት አቶ መሃመድ የለውጥ ሰራዊቱ ሙስናን ጭምር የሚታገል እንደሆነም አብራርተዋል።

ተገልጋዮች በአገልግሎት ላይ ቅሬታ ካላቸው ይህንኑ ለተቋሙ፤ ለመገናኛ ብዙሃን ወይም እንደ ሰብአዊ ኮሚሽንና ህዝብ እንባ ጠባቂ ላሉ ተቋማት ማቅረብ የሚችልበት ስርዓትም ሌላው ለውጡን በተሻለ ሁኔታ ውጤታማ ለማድረግ የተቀመጠ አቅጣጫ ነው ብለዋል።

እንደ አቶ መሃመድ ገለጻ መሰረታዊ የስራ ሂደት ለውጥ ማለትም ቢፒአር ቀደም ሲል በሚፈለገው ደረጃ ውጤታማ ያልሆነው ለሰው ሃብት ተገቢውን ትኩረት ያልሰጠ በመሆኑ ነው ካሉ በኋላ የነበረው አሰራር ቅልጥፍና ላይ ብቻ ትኩረት ያደረገ ነበር ብለዋል።