ቢሮው 3 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ሰጠ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 4/2005(ዋኢማ) - የኦሮሚያ ኢንቨስትመንት ቢሮ 3 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መስጠቱን አስታወቀ።

የቢሮው የመንግስት ኮሙኒኬሽን ኮሙኒኬተር አቶ መኮንን ፉፋ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት፤ የኢንቨስትመንት ፈቃድ የወሰዱት 96 ባለሀብቶች በግብርና፣ በአግሮ ኢንዱስትሪ፣ በማኑፋክቸሪንግና በአገልግሎት ዘርፍ ለመሰማራት ነው።

ባለሀብቶቹ የሚሳተፉባቸው የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለበርካቶች የስር እድል የሚፈጥር ከመሆኑም በላይ ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት በኩል ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል ብለዋል።

ባለሀብቶቹ በአሁኑ ወቅት 2ሺ 463 ሄክታር መሬት መውሰዳቸውን አቶ መኮንን ጠቁመው፤ ባለሀብቶች ሙሉ ለሙሉ ወደ ስራ ሲገቡም 20ሺ 967 ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል እንደሚፈጥሩ ተናግረዋል።

የኢንቨስትመንት ፈቃድ የወሰዱት ባለሀብቶች ቁጥር ከባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የዘንድሮው በእጥፍ ብልጫ እንዳለው ገልፀው፤  ያስመዘገቡት የካፒታል መጠንም ከእጥፍ በላይ መሆኑን አቶ መኮንን መናገራቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።