የኮሪያ መንግሥት 300 ለሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን የኮሪያ ዘማች ልጆች ነፃ የትምህርት እድል ሰጠ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ታሀሳስ 04/2005(ዋኢማ) - የኮሪያ መንግሥት 300 ለሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን የኮሪያ ዘማቾች ልጆች ነፃ የትምህርት እድል መስጠቱ ተገለፀ፡፡

ነጻ የትምህርት እድሉን ካገኙት መካከል በመጀመሪያው ዙር ወደ ኮሪያ ለሚሄዱ 60 የዘማች ልጆች ትናንት አሸኛኘት ተደርጎላቸዋል፡፡

ቀሪዎቹ 240 የዕድሉ ተጠቃሚዎች በመጪዎቹ ሁለት ዓመታት ወደ ኮሪያ በመሄድ በኤሌክትሮኒክስ፣ በአውቶሞባይል፣ በኤሌክትሪሲቲ፣ በመረጃ ቴክኖሎጂና በሌሎችም ዘርፎች ለስምንት ወራት የሚሰጣቸውን ትምህርት ይከታተላሉ፡፡

በአሸኛኘቱ ላይ የተገኙት በኢትዮጵያ የኮሪያ አምባሳደር ጃንግ ጊዮን ኪም እንዳሉት ኮሪያ ዛሬ ለደረሰችበት ከፍተኛ እድገት በኮሪያ ጦርነት ወቅት የዘመቱት ኢትዮጵያዊያን ወጣት ወታደሮች ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርገዋል፡፡

በዚያን ጊዜ የተጀመረው የሁለቱ አገሮች ወዳጅነት ለ60 ዓመታት መቀጠሉንና አሁን ላለበት ደረጃ መድረሱን ገልፀዋል፡፡

በትምህርት ሚኒስቴር የውጭ ግንኙነትና ስኮላርሺፕ ቢሮ ኃላፊ አቶ ምትኩ በሬቻ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት የኮሪያ መንግሥት የኢትዮጵያ መንግሥት ለሚያካሂደው የሰው ኃይል ልማት ፕሮግራም የረጅምና የአጭር ጊዜ ስልጠናዎችን በመስጠት ከፍተኛ ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡

ሁለቱ አገራት ባለፈው ዓመት የተፈራረሙትና ለ300 የዘማች ልጆች ነፃ የትምሀርት እድል ያስገኘው ስምምነት ከ1950 እስከ 1953 በተካሄደው ጦርነት ለተሳተፉ ኢትዮጵያዊያን ዘማቾች እውቅና የተሰጠበት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የኮሪያ ዘማቾች ማህበር ፕሬዚዳንት ኮሎኔል መለሰ ተሰማ በበኩላቸው የኮሪያ መንግሥት ጦርነቱ ካበቃ ከ60 ዓመታት በኋላ የኢትዮጵያ ኮሪያ ዘማቾች ያበረከቱትን አስተዋጽኦ በማስታወስ ለልጆቻቸውና ለልጅ ልጆቻቸው ነፃ የትምህረት እድል በመስጠታቸው ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የኮሪያ መንግሥት በሶስት ዙር ለሚሰጠው የነጻ የትምህርት ዕድል 9 ሚሊዮን ዶላር ወጪ እንደሚያደርግ በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ተገልጿል፡፡