በአዲስ አበባ ከተማ የመሬትና መሬት ነክ ቋሚ ንብረቶች ምዝገባ ሊጀመር ነው

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 04/2005(ዋኢማ) - በአዲስ አበባ ከተማ የመሬትና መሬት ነክ ቋሚ ንብረቶች ምዝገባ በቅርቡ ሊያካሂድ መሆኑን የከተማ ልማትና የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በመሬት ልማት አስተዳደር የሰው ኃይል ለማሰልጠን የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ፊርማ ተፈራርሟል።

የከተማ ልማትና የኮንስትራክሽን ሚኒስትር አቶ መኩሪያ ኃይሌ የመግባቢያ ስምምነቱን በፈረሙበት ወቅት እንደገለጹት፤ በአገሪቱ በመሬት ልማት ዘርፍ የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፈራት፣ በዘርፉ የሚታየውን የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት ለማስወገድና ውጤታማና ዘመናዊ አሰራርን ለመከተል ስምምነቱ የላቀ አስተዋጽኦ አለው።

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር የተደረገው የመግባቢያ ስምምነት ዜጎች በነፃ ገበያ በመሬት ላይ ያፈሩትን ሀብት ለመመዝገብ የሚያስችል እውቀት ለማግኘት የሚረዳ መሆኑንም አስረድተዋል።

አቶ መኩሪያ እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው በዘርፉ በመጀመሪያ፣ በሁለተኛና በሦስተኛ ዲግሪ የሰው ኃይል እንዲያሰለጥን የተደረሰው ስምምነት ለአጭር ጊዜያት ብቻ የሚከናወን ሳይሆን ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚቀጥል ነው።

በአዲስ አበባ ከተማ የመሬትና መሬት ነክ ቋሚ ንብረቶች ምዝገባ ለማካሄድ የቴክኖሎጂ፣ የካርታና ሥርዓት የመዘርጋት ሥራዎች የተገባደደ ሲሆን ሥራውን የሚያስፈጽሙ ተቋማት መቋቋማቸውን ገልጸዋል።

በከተማዋ የመሬትና መሬት ነክ ቋሚ ንብረቶች ምዝገባ በጥቂት ወራት በሁለት ወረዳዎች ላይ የሙከራ ሥራ የሚጀመር ሲሆን፤ ምዘገባውን በማጠናከር በመዲናዋ ባሉ 116 ወረዳዎች እንደሚካሄድም ጠቁመዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ የተጀመረው የመሬትና መሬት ነክ ቋሚ ንብረቶች ምዝገባ ሥራ ሲጠናቀቅ በክልል ከተሞች የሚጀመር መሆኑን የገለጹት አቶ መኩሪያ ዜጎች በመሬት ላይ ያላቸው የመጠቀም መብት ይረጋገጣል ብለዋል።
እንዲሁም በከተሞች የተጀመረው ሥራ በአገሪቱ ባሉ የገጠር ከተሞችም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንና መሬት የልማት ኃይል ሆኖ የሚቀጥልበት ሥርዓት የሚዘረጋ መሆኑን ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር አድማሱ ፀጋዬ እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው ከኢንዱስትሪዎችና ከዘርፍ መስሪያ ቤቶች ጋር ተቀራርቦ በመሥራት ለአገር ልማትና ዕድገት አስተዋጽኦ ለማበርከት እየሰራ ነው።

ከሚኒስቴሩ ጋር የተደረገው የመግባቢያ ስምምነት የንድፍ ትምህርትን ወደ ተግባር ለማሸጋገር፣ መምህራንና ተማሪዎች ያላቸውን እውቀት በተግባር እንዲተረጉሙ ለማድረግ ከፍተኛ ዕገዛ ያደርጋል ብለዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በድህረ ምረቃ ትምህርት ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ሲሆን በአሁኑ ወቅት 225 የድህረ ምረቃ ትምህርቶችን ይሰጣል ያሉት ዶክተር አድማሱ ከዚህ ውስጥ 69ኙ የዶክትሬት ትምህርቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።
ዶክተር አድማሱ እንዳሉት ከዩኒቨርሲቲው የሚወጡ የምርምር ውጤቶች ወደ ተጠቃሚው ለማደረስ የሚያስችል የቴክኖሎጂ ማዕከል ለማቋቋም ዝግጅቱ ተጠናቋል።

ዩኒቨርሲቲው እምቅ ሀብትና በርካታ የሰለጠነ የሰው ኃይል ያለው ተቋም በመሆኑ ከኢንዱስትሪዎችና ከዘርፍ መስሪያ ቤቶች ጋር ተቀራርቦ ለመስራት አቅዶ በመንቀሳቀስ ላይ ይገናል ብለዋል።
ሚኒስቴሩ ከዚህ በፊት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በኢትዮጵያ የሕንፃ ግንባታ ዓለም አቀፍ ደረጃን የጠበቀ ለማድረግ የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል።

የከተማ ልማትና የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በመሬት ልማት አስተዳደር የሰው ኃይል ለማሰልጠን በተፈራረመው ስምምነት መሠረት በመሬት ልማት አስተዳደር የመጀመሪያ ስልጠና የሚያገኙት የሚኒስቴሩና የክልል ከተሞች ሰራተኞች ናቸው።

ዩኒቨርሲቲው ለከተማ ልማትና የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ሰራተኞች ከሚሰጠው ስልጠና በተጨማሪ ከመጀመሪያ እስከ ሦስተኛ ዲግሪ ድረስ ተማሪዎችን እንዲያሰለጥኑ በስምምነቱ ተካቷል።

የመግባቢያ ስምምነቱ በምዕራፍ ተከፋፍሎ የሚከናወን ሲሆን፤ በመጀመሪያው ምዕራፍ የሥርዓተ ትምህርት ቀረፃና የሙያ ዓይነትና ብዛት እንዲሁም በመጀመሪያ የሚሰለጥኑ ሙያተኞች የዳሰሳ ጥናት ይካሄዳል።