ኢትዮጵያ ከስሎቫኪያ ጋር ያላትን ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ እንደምትሻ ፕሬዚዳንት ግርማ አስታወቁ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 04/2005(ዋኢማ) - ኢትዮጵያ ከስሎቫኪያ ጋር ያላትን ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ እንደምትሻ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ገለጹ።

ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ትናንት በብሄራዊ ቤተ-መንግሥት የሥራ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁትን አምባሳደር ሚሊያን ዱብሲክ ባሰናበቱበት ወቅት እንደተናገሩት ኢትዮጵያ ከአገሪቱ ጋር ያላትን ወዳጅነት ለማጠናከር ፍላጎቷ ነው።

አምባሳደር ዱብሲክ በቆይታቸው የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ለማጠናከር ያከናወኗቸው በርካታ መልካም ተግባራት እንደሚያስመሰግናቸውም ተናግረዋል፡፡

መንግሥት አገሪቱን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለማሳለፍ እያደረገ ያለውን ጥረት በማገዝ በኩል የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋት ገልጸው፤ ስሎቫኪያም ድጋፍ እንድታደርግ ጠይቀዋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ የአካባቢ ጥበቃ ጉዳይ ላይ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውንና በተለይ በአፈርና ውሃ ጥበቃ ላይ ተጨባጭ ለውጥ መመዝገቡን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ በተለይ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ያደረገችው ጥረት ውጤት እያስገኘ መሆኑን ፕሬዚዳንት ግርማ አስረድተዋል፡፡

አምባሳደር ዱብሲክ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት በቆይታቸው ተልዕኳቸውን በአግባቡ ተወጥተው ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ያላሰለስ ድጋፍና እገዛ እንዳደረላቸው ገልጸዋል፡፡

ወደ አገራቸው ሲመለሱ የአገሮቹን ግንኙነት በይበልጥ ለማጠናከር በተለይ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴውን ለማሳደግና ባለሃብቶችን ለመሳብ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

አገራቸው በአሁኑ ወቅትም ከኢትዮጵያ የቆላ ዝንብን ለማጥፋት የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተሰናባቹ አምባሳደር አረጋግጠዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአካባቢ ጥበቃ ላይ ለውጥ ያመጡ ተግባራት እያከናወነች መሆኑን መመልከታቸውን አምባሳደር ዱብሲክ ገልጸዋል።

አምባሳደሩ በአየርን ንብረት ጥበቃ ዘርፍ ላይ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ መሆናቸውንና ከዚህ አንፃር ሲታይም በአገሪቱ በዘርፉ እየተከናወኑ ያሉት ሥራዎች አመርቂ ውጤት እያስመዘገቡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ወጣቱ በጥቃቅንና አነስተኛ ሥራዎች ዘርፍ በመሳተፍና ገቢውን በማሳደግ ለአገሪቷ ኢኮኖሚ እድገት የሚያደርገውን አስተዋጽኦ እንደሚያደንቁ አምባሳደር ዱብሲክ መናገራቸውን የዘገበው የኢዜአ ዘገባ ያመለክታል።