ሄንከን በበደሌ ቢራ ስም ከኢትዮዽያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ጋር የስፖንሰርሺፕ ስምምነት ተፈራረመ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 4/2005(ዋኢማ) - ሄንከን በበደሌ ቢራ ስም የኢትዮዽያ ብሄራዊ ቡድን (ዋልያዎቹን) ለቀጣዮቹ 2 አመታት የ24 ሚሊየን ብር የስፖንሰር ድጋፍ ለማድረግ ይፋዊ ስምምነቱን ከኢትዮዽያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ጋር በትናንትናው እለት በሂልተን ሆቴል ተፈራረመ።

ክፍያው በየአመቱ የሚፈጸም ሲሆን፤ በትናንትናው እለት የመጀመሪያውን 1 አመት ክፍያ ማለትም የ12 ሚሊየን ብር ስምምነት ተፈራርሟል።

በኢትዮዽያ እግር ኳስ ፌደሬሽን በኩል የስምምነት ፊርማውን የተፈራረሙት የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ሳህሉ ገብረወልድ ብሄራዊ ቡድናችን ከረጅም ግዜ በኋላ ያሳካውን የአፍሪካ ዋንጫ በጥሩ ዝግጅት እንዲሳተፍ የስፖንሰር ድጋፉ ከፍተኛ እገዛ እንደሚኖረው በመጠቆም፤ ዋልያዎቹ በአፍሪካ ዋንጫ ያልተጠበቀ ነገር ሊፈጥሩ እንደሚችሉ መናገር ይቻላል ብለዋል።

በስምምነቱ መሰረት፤ ዋልያዎቹ በቀጣዮቹ 2 አመታት በሚያደርጓቸው አለም አቀፍ ውድድሮች ሁሉ በደሌ ቢራ በሄንከን ስም በዋና ስፖንሰርነት እንደሚቀጥልና  በዋልያዎቹና በቢራ ፋብሪካው ስም በኮፍያ፣ ቲሸርትና ቁልፍ መያዣዎች ላይ ማስታወቂያ እንደሚሰራ መገለጹን ኤፍ ቢ ሲ ዘገባን ጠቅሶ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።