የርብ ግድብ ግንባታን በተያዘው የበጀት ዓመት 97 ነጥብ 4 በመቶ ለማድረስ ጥረት እየተደረገ ነው

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 3/2005(ዋኢማ) - በደቡብ ጎንደር ዞን በእብናትና ፋርጣ ወረዳና በፎገራ ሜዳዎች ላይ የሚካሄደው የርብ ግድብ ግንባታን በተያዘው የበጀት ዓመት መጨረሻ ላይ 97 ነጥብ 49 በመቶ ለማጠናቀቅ መታቀዱን የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ብዙነህ ቶልቻ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት፤ በዘንድሮው የበጀት ዓመት ለፕሮጀክቱ ማስፈፀሚያ 270 ሚሊየን 360 ሺ ብር በጀት ተመድቦ ስራው እየተፋጠነ ነው።

ፕሮጀክቱ በ2000 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን፤ በአጠቃላይ ለፕሮጀክቱ ማስፈፀሚያም 1 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ወጪ ተመድቦለት እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ግንባታው በአጠቃላይ 30 ነጥብ 33 በመቶ በላይ ስራው መከናወኑን ጠቁመው፤ ፕሮጀክቱን በተያዘለት የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ይገኛል ሲሉ አቶ ብዙነህ ተናግረዋል።

የፕሮጀክቱ የዋና የግድቡ ግንባታ አጠቃላይ ስራው 15 በመቶ የላይ አፈር ጠረጋና የመሰረት ቁፋሮ፣ 20 ነጥብ 5 በመቶ የመደልደል ስራ፣ 91 ነጥብ 6 በመቶ የአፈርና ድንጋይ ሙሌት ስራ መከናወኑን ገልፀዋል።

የርብ ግድብ 800 ሜትር ርዝመት ሲኖረው 73 ነጥብ 2 ሜትር ከፍታና 234 ሚሊየን ሜትር ኩብ ውሃ የመያዝ አቅም እንደሚኖረው አቶ ብዙነህ ጠቁመው፤ በፎገራ ሜዳ ላይ 14ሺ ሄክታር መሬትን በመስኖ ሊያለማ ይችላል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልፀዋል።