በቴክኒክና ሙያ ተቋማት የሚሠጡ ሥልጠናዎች የአነስተኛና የጥቃቅን ተቋማትን አቅም እያሳደጉ መሆናቸው ተገለፀ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 3/2005(ዋኢማ) - በሃገሪቱ በቴክኒክና ሙያ ተቋማት የሚሠጡት ሥልጠናዎች የአነስተኛና ጥቃቅን ተቋማትን አቅም በማሳደግ ላይ እንደሚገኙ የትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስትር ዲኤታው አቶ ወንድወሰን ክፍሉ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት፤ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ለኢንዱስትሪና ለቴክኖሎጂ  ሽግግር  ቅድሚያ በመሥጠት የድህረ ትምህርትና የሥራ  ላይ ሥልጠና  በመሥጠት ላይ ይገኛል፡፡

በቴክኒክና ሙያ ተቋማት ላይ የሚሠጡት ሥልጠናዎች ሠልጣኞች በቴክኖሎጂና ኢንዱስትሪ ክህሎታቸውን እንዲያጎለብቱ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቁመው፤  የአነስተኛና ጥቃቅን ዘርፉን አቅም በማሳደግ በኩል ጉልህ ሚና ይኖራቸዋል ብለዋል፡፡

የሙያ ጥራት ማረጋገጫ ሥልጠና ለአዲስ ተመራቂዎችና በሥራ ላይ ለተሰማሩ ባለሙያዎች እንደሚሠጥ የጠቆሙት አቶ ወንድወሰን የሚሠጡት ሥልጠናዎች  የሠልጣኙን አቅም ለማሳደግ ይረዳሉ በማለት ገልፀዋል፡፡

በቴክኒክና ሙያ ዘርፉ የሚሠጡት የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎች  የመምህራን  የአቅም ግንባታ፣ የሠልጣኞች ልማትና  የተቋም  አቅም  ግንባታን  የሚያካትቱ መሆናቸውን ገልፀው፤  ሚኒስቴር  መሥሪያ  ቤቱ  ሶስቱን የሥልጠና ፕሮግራሞችን አቀናጅቶ  በማስኬድ ላይ  እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

በዘንድሮ የበጀት አመት ሚኒስቴር መሥሪያ  ቤቱ ከሙያና ቴክኒክ ተቋማት፣ ከባለድርሻ አካላት፣ ከክልል ቢሮዎችና ከተለያዩ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ጋር ተቀናጅቶ በመሥራቱ የተግባር ሥልጠናው ተጠናክሮ እንዲቀጥል አድርጓል ብለዋል።

በተለያዩ  የሙያና የቴክኒክ  ተቋማት  የካይዘን  የሥራ  አመራር  ፍልስፍና ተግባራዊ  መሆን ጀምሯል ያሉት አቶ ወንድወሰን ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ  ለማድረግ ለተቋማቱ አመራሮች የካይዘን ሥልጠ ተሰጥቷል ብለዋል።

ይህም በሀገሪቱ ውስጥ የልማት ሠራዊት ለመገንባት የተያዘውን ራዕይ ለማሳካት  እንደሚረዳ ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል።