ድርጅቱ የጥራት ሥራ አመራር ስልጠናና የልምድ ልውውጥ አካሄደ

  • PDF

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 3/2005 (ዋኢማ) - የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት የጥራት ሥራ አመራር ስልጠናና የልምድ ልውውጥ መድረክ ትላንት በጊዮን ሆቴል አካሄደ።

የልምድ ልውውጡን ያካሄደው የጥራት ሽልማት ድርጅት ያሳለፋቸውን የአምስት አመት ጉዞ በመቃኘት ለሶስተኛው ዙር ለሚደረገው የጥራት ሽልማት ዝግጅት ለተወዳደሪ ድርጅቶች ግንዛቤ ለማስጨበጥ በማሰብ ነው።

የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት ቦርድ አባልና የዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ሥራ አስኪያጅ አቶ ተተካ በቀለ በመክፈቻው ባደረጉት ንግግር የደንበኞች ፍላጎትና ምኞት በየጊዜው እያደገና እየተለወጠ ስለሚሄድ ይህንን በመገንዘብ ቀጣይነትና ተከታታይነት ባለው አግባብ የደንበኞችን ፍላጎት እያጠኑ መንቀሳቀስ ደንበኞችን በዘላቂነት ይዞ ለመቆየት ያስችላል ብለዋል፡፡

ከተቋቋመ አምስት ዓመታትን ያስቆጠረውና በሀገራችን በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነው የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት በምርትና አገልግሎት ጥራት ዘርፍ ዕድገት ለማምጣትና ሀሳቡን ለማስረፅ ትኩረት ሰጥቶ ሲሰራ ቆይቷል፡፡
ድርጅቱ ባሳለፋቸው ሁለት የውድድር ጊዜያት በሶስት ዘርፎች ማለትም በአገልግሎት፣ አምራችና በኮንስትራክሽን ዘርፎች አወዳድሮ ሸልሟል፡፡

የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ሚካኤል መላኩ የጥራት ሽልማት ድርጅቱን የአምስት ዓመት ጉዞና ዕድገት አስመልክቶ ባደረጉት ገለፃ የጥራት ሽልማት መደረጉ ለሀገራችን የሚሰጠውን ከፍተኛ ጠቀሜታ በመገንዘብ ፅንሰ ሀሳቡን በሚገባ ለማስረፅና ድርጅቱ የተቋቋመለትን ዓላማ ለማሳካት ያለሰለሰ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል ብለዋል፡፡

የዛሬ አራት ዓመት የመጀመሪያ ዙር የጥራት ሽልማት ሲሰጥ ለውድድር ያመለከቱት ድርጅቶች አነስተኛ እንደነበሩ አውስተው በሁለተኛው ዙር ከ150 በላይ ድርጅቶች ፈቃደኝነታቸው አሳይተው 52 በውድድሩ ተሳታፊ እንደነበሩ አስታውሰዋል፡፡

ሶስተኛው ሀገር አቀፍ የጥራት ሽልማት ውድድር የመወዳደሪያ ዘርፎችን በመጨመር በርካታ ድርጅቶች ይሳተፋሉ ተብሎም እንደሚጠበቅ አቶ ሚካኤል ተናግረዋል፡፡

“ጥራት፣ የጥራት አመራርና ደረጃዎች’’ የሚል ፅሑፍም በውይይቱ ወቅት ያቀረቡት  የኢትዮጵያ ደረጃዎች አጄንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ አልማዝ ካህሳይ አንደተናገሩት የሀገራችን አምራች አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ደንበኛና ገበያ ተኮር የሆነ በጥራት ላይ የተመሰረተ የሥራ አመራርና የሥራ አፈጻጸም ስርዓት ሊኖራቸው ይገባል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት በሁለት ዙር ውድድር ጥሩ ውጤት በማምጣት ለሽልማት ከበቁት ከቀድሞ ተሸላሚዎች መካከል የሰነድ ምዝገባና ማረጋገጫ ጽህፈት ቤት፣ የሀረር ቢራ አክሲዎን ማህበር እንዲሁም የኮምቦልቻ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ መልካም የሆኑ ልምዶቻቸውን ለታዳሚዎች አካፍለዋል፡፡

በመድረኩ ላይ በሀገሪቱ የሚገኙ አምራቾች አገልግሎት ሰጪዎች በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰማሩ ድርጅቶች ተሳትፈዋል፡፡

ድርጅቱ እንደሌሎች ሀገሮች ሁሉ በአገሪቱ የሚገኙ አምራቾችን አገልግሎት ሰጪዎችንና የኮንስትራክሽን ዘርፍ ኢንዱስትሪዎችን በጥራት አመራር ዙሪያ እያወዳደረ ዕውቅና በመስጠት ራሳቸውን እንዲያሻሽሉ ከማድረግ ባሻገር ለድርጅቶቹ ቀጣይነት ያላቸው ስልጠናዎችን የልምድ ልውውጥ መድረኮችን በማዘጋጀት እንዲሁም የምክር አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ ብቁ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡