ኢትዮጵያ የሚሌኒየም የልማት ግቦችን ከሚያሳኩ የአፍሪካ አገሮች የቀዳሚነት ሥፍራ አገኘች

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 3/2005(ዋኢማ) - የሚሌኒየም የልማት ግቦችን ከሚያሳኩ የአፍሪካ አገሮች መካከል ኢትዮጵያ በቀዳሚነት መቀመጧን የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም አስታወቀ።

የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ከተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም ጋር በመተባበር የድህረ 2015 ሚሌኒየም የልማት ግቦች የግሉ ዘርፍ አገር አቀፍ የምክክር መድረክ አካሂዷል።

በተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም የሚሌኒየም የልማት ግቦች የፖሊሲ ጥናት ባለሙያ አቶ ግርማ ኃይሉ በተለይ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ከስምንቱ የሚሌኒየም የልማት ግቦች አምስቱን በማሳካት ከአፍሪካ አገሮች የቀዳሚነት ሥፍራን ይዛለች።

ሚሌኒየም የልማት ግቦች ሊጠናቀቅ ሁለት ዓመት ተኩል የቀረው ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ያሳየችው ትጋትን አጠናክራ በመቀጠል ቀሪዎቹን ሦስት የልማት ግቦችን ልታሳካ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

ሕዝባዊ ንቅናቄን ጨምሮ የፖሊሲና ስትራቴጂ አቅጣጫዎችን ማስተካከል እንዲሁም የልማት ፋይናንስ ማሰባሰብ ከተቻለ ከዚህ በፊት ከነበረው አፈፃፀም የተሻለ እንደሚሆንም ጠቁመዋል።

አቶ ግርማ እንዳሉት ባለፉት አስርት ዓመታት የጤና ባለሙያዎችን አቅም መገንባትና የጤና ተቋማትን ቁጥር መጨመር ላይ ኢትዮጵያ በርካታ ተግባራትን አከናውናለች።

በተለይ ከእርግዝናና ወሊድ ጋር በተያያዘ የሚሞቱ የእናቶችን ቁጥር በአገሪቱ አለመቀነሱን ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ጠቅሰው፤ የእናቶችን የሞት ቁጥር ለመቀነስ በቀሪዎቹ ጊዜያት ርብርብ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

ሴቶች በፖለቲካ በኢኮኖሚና በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸው ተሳትፎ ውስን በመሆኑና ራሳቸውን በኢኮኖሚ ለማስቻል በሚሌኒየም የልማት ግቦች የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት በርካታ ተግባራት ሊከናወኑ እንደሚገባ አመልክተዋል።

እንዲሁም ከአካባቢ ጥበቃ ጋር በተያያዘ የግልና የአካባቢ ንጽህናን ለመጠበቅ እስካሁን የተደረገው ጥረት እንደሚያሳየው ይበልጥ መሥራት እንደሚገባ የሚያሳይ ነው ብለዋል።

የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አብርሃም ተከስተ እንደገለጹት እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ2000 የሚሌኒየም የልማት ግቦችን ተፈፃሚ ለማድረግ ኢትዮጵያን ጨምሮ ቃል የገቡ አገሮች 189 ናቸው።

ከአገሮቹ መካከል ለድህረ 2015 የሚሌኒየም የልማት ግቦች ማዕቀፍ ዝግጅት 50 አገሮች ለአገራዊ ምክክር የተመረጡ ሲሆን ከእነዚህ አገሮች ውስጥ ኢትዮጵያ አንዷ መሆኗን ገልጸዋል።

ዶክተር አብርሃም እንዳሉት ኢትዮጵያ ዕድሉን ያገኘችው አገሪቱ ከልማት አገሮች ጋር በመተባበር ባካሄደችው ከፍተኛ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራት ውጤት በማስመዝገቧ ነው።

የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማኀበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ወይዘሮ ሙሉ ሰለሞን በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በዓለም ከተመረጡ 50 አገሮች አንዷ በመሆን የራሷንና ለሌላው ዓለም የምታበረክተውን የልማት አጀንዳ እንድታበረክት ለመረጣት አካል ምክር ቤቱ የግብረ ኃይሉ አካል በመሆን እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የድህረ 2015 ሚሌኒየም የልማት ግቦች አገር አቀፍ ምክክር በሦስት ደረጃዎችና በአምስት ማዕከሎች እንደሚካሄድ ቀደም ብሎ የወጣው መርሓ ግብር ያመለክታል።

የመጀመሪያው የክልሎች ምክክር ህዳር 13 እና 14 ቀን 2005 ዓ.ም. በባህርዳር ከተማ የተካሄደ ሲሆን፤ ሁለተኛው የክልሎች መድረክ ህዳር 20 እና 21 ቀን 2005 ዓ.ም. በአዳማ ከተማ ተካሂዷል።

እንዲሁም ሦስተኛው የክልሎች የምክክር መድረክ ህዳር 27 እና 28 ቀን 2005 ዓ.ም. በድሬዳዋ ከተማ የተካሄደ ሲሆን በተመረጡ የትኩረት አካላት ማለትም በሴቶች ህዳር 18 እና 19 ቀን 2005 ዓ.ም. በአዳማ ከተማ ተካሂዷል።

የወጣቶች አገር አቀፍ የምክክር መድረክ ታህሳስ 4 እና 5 ቀን 2005 ዓ.ም. በሀዋሳ ይካሄዳል።