የጽንፈኞች ሰጣገባ የህዝበ ሙስሊሙን እርካታ አያደበዝዝም!

  • PDF

ሲኢድ መሐመድ (ታህሳስ 2/2005)

ሼህ መሐመድ እድሪስ የ67 ዓመት አዛውንት ናቸው። አባታቸው የእስልምና ኃይማኖትን ከሚያስፋፉ የእምነቱ ተከታዮች አንዱ ስለነበሩ ከልጅነታቸው ጀምሮ የመስጂድን ሥነ ስርዓት ይዘው ሊያድጉ ችለዋል፡፡ በዚህም የተነሳ የእስልምና አስተምህሮን ጠንቅቀው አውቀዋል።

በእድሜያቸውም ኢህአዴግን ጨምሮ ሦስት መንግሥታትን አይተዋል። ባለፉት ሁለት ሥርዓታት የነበረው የእስልምና ኃይማኖት የማራመድ ነጻነትን ዛሬ ካለው ጋር እያነጻጸሩ እንዲህ ያወጉናል፡፡ “በመሠረቱ ቀደም ሲል የነበሩ ሥርዓታት ፀረ ኃይማኖት አቋም ነበራቸው። ህዝበ ሙስሊሙ እምነቱን በነጻነት ማራመድ ይቅርና በበዓላት ወቅት በሚሰባሰብበት ጊዜ እንኳን ከሌሎች ፖለቲካ ጉዳዮች ጋር በማያያዝ ሠላሙን ያደፈርሱት ነበር።

ወጣቶች ከመስጂድ እየታፈኑ ወደ ጦር ሜዳ ይወሰዱ ስለነበር የእምነት ቦታዎች የወታደሮች መናኸሪያ እንጂ በጥሞና አላህን የምናመሰግንበትና ከፈጣሪያችን ጋር የምንገናኝበት አልነበረም።”

ሼህ መሐመድ እድሪስ በተለይ በደርግ ሥርዓት ሁኔታው አስከፊ እንደነበር ይናገራሉ። ወጣቶች የእምነት ሥፍራዎች አካባቢ መሰባሰብ የማይችሉበት ብሎም  ኃይማኖታዊ ተልዕኳቸውን ለመፈፀም የማይፈቀድላቸው ፈፅመው ከተገኙም ፀረ ሕዝብ እየተባሉ በማያውቁት ነገር ለእሥር የሚዳረጉበት ሁኔታ ነበር። 

በኢትዮጵያ የኃይማኖት ነጻነት እውን የሆነው በ1987 ዓ.ም ነው። አሁን ያለው መንግሥት ወደ ሥልጣን እንደመጣ የኃይማኖት እኩልነትና ነጻነትን በማወጁ ምክንያት ዜጎች ያለመሸማቀቅ ኃይማኖታቸውን የሚከታተሉበትና የእምነት ተቋሞቻቸውን ማስፋፋትና በየእምነት ሥፍራዎችም ሆነ በየመኖሪያቸው  ኃይማኖታዊ ተልዕኳቸውን ያለምንም መሸማቀቅ በነጻነት መፈፀም የቻሉበት ሥርዓት ተፈጥሯል ይላሉ ሼህ መሐመድ እድሪስ።

እርግጥ ነው ባለፉት ሁለት አሥርተ ዓመታት በአገሪቱ ከተመዘገቡ በርካታ መሠረታዊ ለውጦች መካከል የኃይማኖት ነጻነት መረጋገጥ አንዱ ነው። በዚህ ምክንያት ዜጎች ያለምንም አስገዳጅ ሁኔታ የመረጡትን ኃይማኖት የማምለክና ኃይማኖታዊ ተልዕኳቸውን ያለማንም ተፅዕኖ መፈፀም የሚያስችላቸው ሥርዓት ተፈጥሮላቸዋል። በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት በግልጽ እንደሰፈረው ማንኛውም ሰው የማሰብ፣ የህሊና እና የኃይማኖት ነጻነት አለው።

ይህ መብት ማንኛውም ሰው የመረጠውን ኃይማኖት ወይም እምነት የመያዝ  ኃይማኖቱንና እምነቱን ለብቻ ወይም ከሌሎች ጋር በመሆን በይፋ የማምለክ፣ የመከተል፣ የመተግበር፣ የማስተማርም ሆነ የመግለጽ መብትን እንደሚያካትት ያስረዳል። በተጨማሪም ማንም ሰው እሱ የሚፈልገውን እምነት ሌላውም እንዲከተለው በማስገደድ የሌላውን ነጻነት መጋፋት አይችልም። በኃይል ወይም በሌላ ሁኔታ በማስገደድ መገደብ ወይም መከልከል እንደማይቻል በሕገ መንግሥቱ በግልጽ ሰፍሯል። 

መንግሥት በኃይማኖት ጣልቃ የማይገባበት ኃይማኖትም በመንግሥት ጉዳይና ኃላፊነት እጁን የማይቀላቅልበት ሥርዓት ተፈጥሮ ተግባረዊ መሆን ከጀመረ ሃያ  ዓመታት ተቆጥሯል።  ይህንን  ሕገ መንግሥታዊ መብትን መሠረት በማድረግ በአገራችን የኃይማኖት ነጻነት ከተረጋገጠ ዓመታት አልፈዋል።

ከኃይማኖት ጋር በተያያዘ ጥያቄ ለማንሳት የሚያስችል መሠረት በሌለበት ሁኔታ ከኃይማኖት ጋር በማላከክና የህዝበ ሙስሊሙ ጥያቄ በማስመሰል አክራሪዎች የአገራችንን ሠላም ለመበጥበጥና ለማወክ የማይበጥሱት ቅጠል የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም። በመሆኑም ኃይማኖትን ለድብቅ የፖለቲካ አጀንዳ ማስፈፀሚያ መሣሪያ አድርጎ ለመጠቀም ወቅታዊ ሁኔታዎችን እየተከተሉና ሁነቶቹን ከኃይማኖት ጋር እያዛመዱ አጀንዳቸውን ለመፈጸም  የሚያደርጉትን የትግል ስልት ከጊዜ ወደ ጊዜ በመቀያየር ቀጥለውበታል።  

ከጥቂት ዓመታት ወዲህ  የእስልምና ሃይማኖትን ለምድ ለብሰው  የተነሱ ጽንፈኞች በተለያዩ የሃይማኖት አማኞች መካከል ለዘመናት የነበረውን መቻቻል በማደብዘዝ በመካከላቸው ደም መፋሰስንና ግጭትን ለማቀጣጠል በተለያየ ጊዜ የተለያየ ሙከራ ሲያደርጉ ተስተውሏል። አንዳንድ "ፖለቲከኞችም" ሃይማኖትን በመሳሪያነት ለመጠቀም መሞከራቸው አልቀረም። ከዚህ ጋር በተያያዘም  አንዳንድ የደርግ ስርዓት  አቀንቃኞች ህቡእ የፖለቲካ አጀንዳቸውን በሃይማኖት ሽፋን ለማራመድ በሁሉም የሃይማኖት አማኞች መካከል አማኝ መስለው በመሰግሰግ ሃይማኖትን በመሳሪያነት ለመጠቀም ተንቀሳቅሰዋል።

የከሰሩ ፖለቲከኞች በእምነት ተቋማት እየተገኙ ከእምነቱ አስተምህሮ የተለየ ነገር  በሚያቀርቡበት ወቅት  እንደ ወረደ ከመቀበል ይልቅ የተለያዩ ጥያቄዎችን  ማንሳት የጀመረው ምእመኑ መንግስት  ሃይማኖት ላይ የሚያሳድረው  ምንም ዓይነት ጫና እንደሌለ ስለሚያውቅ የጽንፈኞቹን አካሄድ እየተጠራጠረው መጣ።  በእምነት ቦታዎችና በሃይማኖት ስም  የፖለቲካ ስብከት ለምን ይሰበካል?  ሃይማኖታዊ ተግባራትን ብቻ ለምን አንፈጽምም? የሚሉ አማኞች ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጣ።  በዚህ ምክንያት ህዝበ ሙስሊሙ ከጽንፈኞቹ እየተለየ መምጣት ቻለ። 

የክርስትና ሃይማኖት አማኞችን ከእስልምና ሃይማኖት  አማኞች ጋር  ማጋጨት  ያስችለናል ያሉትን  ስትራቴጂ ነድፈው ተንቀሳቅሰዋል፡፡  የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ የከሰሩ ፖለቲከኞች በእስልምና እምነት አማኞች እንዲሰገሰጉ  የክርስትና ሃይማኖት አማኝ አባሎቻቸው ደግሞ  በክርስትና ሃይማኖት አማኞች  እንዲሰገሰጉ በማድረግ በሁለቱ እምነት ተከታዮች  መካከል መቋጫ የሌለው ግጭት ለመፍጠር ያደረጉት ጥረት ቀላል አልነበረም፡፡

በዚህ መልክ የእስልምና አልባሳትን በመልበስና የእስልምና ሃይማኖት አማኞች የሚጠቀሙባቸውን የእምነት ቃላት አዘውትረው በመጠቀም በቤተክርስቲያኖች እየገቡ በመጮህና በክርስትና ወገን ያሉ አባሎቻቸውም ለምን እንዲህ ይደረጋል በሚል ነገሩን በማጋጋል  በሁለቱ ሃይማኖት አማኞች መካከል መቋጫ የሌለው ግጭት በመፍጠር  ሰላምን ለማደፍረስ ያልተቆጠበ ጥረት አድርገዋል።  

ከ1997 አገራዊ ምርጫ ጋር ተያይዞ ድል ያልቀናቸው ፖለቲከኞች ሃይማኖትን በመሳሪያነት ለመጠቀም ከፍተኛ እንቅስቃሴ አድርገው ነበር። በሃይማኖት ሽፋን ወጣቱን ለስውር የፖለቲካ አጀንዳቸው ማስፈጸሚያ በማሰማራት ሰፊ ዘመቻ አካሂደዋል። ህዝበ ክርስቲያኑ ሃይማኖታዊ ተልእኮውን ለመወጣት በሚሰባሰብባቸው የእምነት ቦታዎች በመገኘት ብጥብጥና ሁከትን ለማስነሳት ደክመዋል።

እነዚህን ኃይሎች ህዝቡ አንቅሮ ቢተፋቸውም አዳዲስ ተያያዥ አጀንዳዎችን በመቅረጽ ሃይማኖት ለበስ የፖለቲካ እንቅስቃሲያቸውን በመቀጠል በተለይ  ‘ከእምነት ጋር ቁርኝት ያላቸው ተቋማት ውስጥ  በሚገኙ ወጣቶች ዘንድ ሰርገው በመግባት ብጥብጥና ሁከት ለመፍጠር ጥረዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በአገሪቱ እየተገነቡ ባሉ ትላልቅ የልማት አውታሮች ላይ በማነጣጠር  የአካባቢውን ማሕበረሰብ ለሐይማኖት ከሚኖረው ቀናኢነት በመነሳት ይከተለናል በሚል የማወናበድ ዘመቻቸውን አሁንም ቀጥለውበታል። ከወልቃይት የስኳር ልማት ጋር ተያይዞ እየተነሳ ያለው ጉዳይ የዚሁ አካል ነው።   ዓላማውም  በአካባቢው የሚካሄደውን ልማት በሃይማኖት ሽፋን ማኮላሸት ነው። እስቲ አንዳንድ አብነቶችን ጠቃቅሰን እንለፍ።

መንግስት ለስኳር ልማት ፕሮጄክት ሲል የዋልድባን ገዳም አፈረሰው በማለት ህዝቡን ለማነሳሳት ያልፈነቀሉት ድንጋይ አልነበረም። የዋልድባ ገዳም የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት  ገዳም ነው። የተከበረና የተቀደሰ የእምነት ስፍራ ነው። በቦታው የሚያገለግሉ መነኮሳትም የተከበሩና የበቁ የሃማኖት አባቶች ናቸው፡፡ በመሆኑም ገዳሙ የሚነካበት ምክንያት የለም። የስኳር ልማቱ ገዳሙን አይነካም። በዚህም የተነሳ ገዳሙ ቀደም በነበረበት ሁኔታ ሃይማኖታዊ ተልእኮውን  ያከናውናል።

የከሰሩ ፖለቲከኞችና ጽንፈኞች ሃይማኖትን ለድብቅ የፖለቲካ አጀንዳ ማስፈጸሚያ  በመሳሪያነት መጠቀምን  ለምን መረጡ?  ተግባራቸው በተደጋጋሚ እየተጋለጠ ለምን መቋጫ አላገኘም?  አማኞች እምነቱ ከሚያዘው ውጭ የተለያየ እንቅስቃሴ    ሲያጋጥማቸው ለምን አፋጣኝ እርምጃ አይወስዱም? የሚሉትንና  ተዛማጅነት ያላቸው ሌሎች ጥያቄዎችን መመለስ ተገቢነት ይኖረዋል።

እነዚህ ኃይሎች ሃይማኖትን በመሳሪያነት መጠቀም  የፈለጉት የኢትዮጵያ ህዝብ ለሃይማኖቱ ቀናኢ ለእምነቱ ሟች መሆኑን ስለሚያውቁና የእስልምናም ሆነ የክርስትና ሃይማኖት አማኞች ለለሃይማኖታቸው ህይወታቸውን አሳልፈው ለመስጠት እንደማያመነቱ በመገንዘብ ነው። ከዚህ አንጻር ሃይማኖታዊ የመሰሉ ጥያቄዎችን በማንሳት አማኞች ውስጥ ሰርጎ በመግባት በመርዝ የተለወሰ ማር  ለማጉረስ ጥረት ማድረግ ያዋጣል የሚል እምነት በማሳደራቸው ነው።

ሌላው ደግሞ በሃይማኖት ምክንያት የሚነሱ ግጭቶች መቋጫ አይኖራቸውም የሚል እምነት በማሳደር  ህዝቡን ፍጻሜ ወደሌለው ግጭትና ሁከት ለማስገባት በማቀድ ነው። ለዚህም ነው  አንዴ በእስልምና  በሌላ ጊዜ  ደግሞ በክርስትና ሃይማኖት ሽፋን  ረዘም ላለ ጊዜ እየተንቀሳቀሱ ሳይጋለጡ  መቆየት ችለዋል። ትክክለኛ የሃይማኖት ጉዳይ የሚያነሱ መስለው ድብቅ አጀንዳቸውን በየወቅቱ ከሚከሰቱ ሁነቶች ጋር እያቆራኙ  ከማቅረባቸው በላይ በእያንዳንዱ እምነት ውስጥ ለተሰገሰጉ አባሎቻቸው ከፍተኛ ገንዘብ በመመደብ አንዳንድ ፍሪሃ እግዚአብሄር የራቃቸው አማኞችን  በገንዘብ ሃይል በማታለል የእነሱን ፍላጎት እንዲያራምዱ ስለሚያደርጉ ነው። ምንም እንኳን በተለያየ ጊዜ ያነሷቸው ጥያቄዎች ሃይማኖታዊ ተልእኮ እንደሌላቸው እርቃናቸው የወጡበት ሁኔታ ቢኖርም ከውጭ በሚያገኙት ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ በመታገዝ የተለያዩ እቅዶችን በመንደፍና ስልታቸውን በመቀያየር  አፍራሽ ተልእኳቸውን ለማሳካት ጥረት ስለሚያደርጉ  እንደሆነ ይታመናል።


ውሸትና ስንቅ እያደር ይቀላል እንደሚባለው ግን እያደር እውነታው በተለያየ መልክ መውጣት ሲጀምር ድብቅ የፖለቲካ አጀንዳን ለማስፈጸምና የአገሪቱንም ሰላምና ልማት ላይ አሉታዊ ጫና ለማሳደር ታቅዶ የተቀነባበረ ተግባር መሆኑን ህዝበ ክርስቲያኑ መገንዘብ የቻለበት ሁኔታ ተፈጥሯል። 

በሃይማኖት ሽፋን የሚነሱ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎችን የሃይማኖቱ አማኞች በፍጥነት የማያስወግዱበት ምክንያት ደግሞ በመካከላቸው ባሉ አንዳንድ ራሳቸውን ለጥቅም አሳልፈው የሰጡ የሃይማኖቱ አማኞች ጉዳዩ ሃይማኖታዊ አስመስለው ስለሚያቀርቡት ነው። አንዳንድ  አማኞች በገንዘብ በመገዛት ሌላውን  አማኝ ለማሳመን ጥረት ስለሚያደርጉ የሃይማኖቱ ተከታዮች የጉዳዩን ውስጠ ምስጢር ለማወቅ ጊዜ ይወስድባቸዋል።

ተስፋ የቆረጡ ፖለቲከኞች ሃይማኖትን በሁለት መልክ ይፈልጉታል። አንደኛው በሃጥያትና በክፋት የተጨማለቀ ህሊናቸውን ትንሽ ለማሳረፍ ያስችለናል ከሚል  እምነት ነው። ሌላው ደግሞ ለሃይማኖቱ ቀናኢ የሆነ ህዝብ በሚሰበሰብበት የተቀደሰ ስፍራ ሃይማኖት ለበስ ህቡእ አጀንዳቸውን ተግባራዊ ለማድረግ ያግዘናል ብለው ስለሚያምኑ ነው።

የእነዚህ የከሰሩ  ፖለቲከኞች ዓላማ የአገሪቱን ሰላም በማደፍረስ በግርግር ለመጠቀም መሞከር ነው። የከሰሩ ፖለቲከኞች ከሃይማኖትና ከጽንፈኝነት የሚቆራኙትም ከዚህ አንጻር ነው። ይህ በውስጥ ከሰነቀው ህቡእ አጀንዳ ጋር ሲጣመር የጥፋት መንገድን መከተል ዓይነተኛ ስትራቴጂ አድርጎ ይጠቀማል። ‘እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል!”  አይደል ተረቱ።

የከሰሩ ፖለቲከኞች፤ ሃይማኖትና ጽንፈኝነት ያላቸው ቁርኝትም ከዚሁ የመነጨ ነው። ቀደም ሲል ሲነሳ የነበረው የመጂሊሱ ጉዳይ መቋጫ አግኝቷል። መላው የኢትዮጵያ ህዝበ ሙስሊም የሚወክለውን መርጧል።  አዲሱ መጂሊስም  ከእምነቱ ተከታዮች ጋር  በመመካከር አስፈላጊውን ሁሉ እያደረገ ይገኛል።

ህዝበ ሙስሊሙም ሆነ ህዝበ ክርስቲያኑ ማንኛውም ነገር ከፈጣሪ መሆኑን ያምናል። ክፉ የሚሰራ ዋጋውን ከፈጣሪ ያገኛል የሚል እምነት ስላለውም   ይታገሳል። የሚነሳው ነገር ሃይማኖታዊ ሽፋን የለበሰ ፖለቲካ  በመሆኑ ግን አንድ ጊዜ ተነስቶ የሚቆም አይሆንም። በተደጋገመ ቁጥር ሃይማኖታዊ ስርዓቱንና አስተምህሮን እየሳተ ወደዋናው ዓላማው መግባት ይጀምራል። ውሎ ሲያድርም   ሃይማኖታዊ ተልእኮ እንደሌለው  ፈጦ ይወጣል። በተለያየ ጊዜ በሃይማኖት ሽፋን የተደረጉ ሙከራዎች ውጤት የሚያሳየውም ከዚህ የተለየ አልነበረም።

ህዝበ ሙስሊሙ በተካሄደው ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ረክቷል። ይወክሉኛል ያላቸውን ፍጹም ፍትሃዊ በሆነ መንገድ መርጧል። ጽንፈኞች ግን ዓላማቸው የአገራችንን ሰላም ማደፈረስና ልማታችንን ማሳናከል በመሆኑ ጽንፈኛ እንቅስቃሲያቸውን ቀጥለውበታል። እርቃናቸውን መቅረታቸውን  ቢያውቁትም ከመግተርተር ወደ ኋላ አላሉም። ሰጣገባ ቀጥለዋል።