የሥነ- ምግባር ደንቡ ምንነትና የተቃዋሚዎች ጭፍን ሙግት

  • PDF

ዘሪሁን ተገኝ (ታህሳስ 2/2005)

ታላላቅ ታሪኮች ያሉን ህዝቦች ብንሆንም፤ የኢ-ዴሞክራሲያዊ ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ አምባገነንነትን በጫንቃችን ላይ ተሸክመን ኖረናል፡፡ ለዚህ ምክንያቱም በየዘመናቱ አንዱን ብሔር ከሌላው እያላተሙ እና አንዱን ሃይማኖት ከሌላው እያጋጩ፣ ጎራ ለይተው ያስተዳደሩን ያለፉት መንግስታት ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ለዘመናት ከድህነት አረንቋ እንዳይወጡ እና እዚያው እንዲዳክሩ ተደርገዋል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝቦች በገዛ ሀገራቸው እስረኛ ሆነው ዴሞክራሲያዊ እና ሰብዓዊ መብታቸውን ተነጥቀው የግፍ ፅዋን ሲጎነጩ ኖረዋል፡፡ ይህ ኢ-ፍትሃዊ አስተሳሰብ ዛሬም ከእነ ፀረ-ዴሞክራሲያዊ ድርጊቱ ዳግም ላይመለስ ወደ መቃብር ወርዷል፡፡ የህዝቦች የረጅም ዘመናት የትግል ውጤት በሆነው ህገ -መንግስት የሀገራችን ህዝቦች የስልጣን ባለቤት ለመሆን መብቃታቸው የትግላቸው ውጤት ናቸው፡፡

አዲሲቷ ኢትዩጵያ ዛሬ የዜጎቿ ሰላም የተረጋገጠባት እና ከልማቱም በየደረጃው ተቋዳሽ ሀገር ሆናለች፡፡ ህዝባችን መንግስት በነደፋቸው ውጤታማ ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎና ስልቶች እየተመራም ህዳሴውን ለማረጋገጥ ደፋ ቀና እያለ መሆኑን ዓለም እየመስከረ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና እና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር የሚችሉበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ገንብተዋል፡፡ ህገ- መንግስቱ ያጎናጸፋቸው የስልጣን ባለቤትነት መብታቸውም እየተገበረ ይገኛሉ፡፡

በሀገሪቱ ታሪክ ለዘመናት ነግሶ የነበረውን የአንድ የፖለቲካ አስተሳሰብ ተወግዶ ዛሬ በሀገሩ ጉዳይ ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ የሚፈልገውን ነገር ህጋዊ እና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ህገ-መንግስታዊ መብቱን ማራመድ ብሎም ማረጋገጥ የሚችልበት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ የኋላ ታሪካችን እንደሚያሳየን፤ እንኳንስ የተለያዩ የፖለቲካ ሃሳቦችን መያዝና ማራመድ ይቅርና የፖለቲካ ፓርቲ ብሎ ጉዳይ በራሱ በህግ የሚያስቀጣ ነበር፡፡

ይህ መጥፎ የታሪክ ጠባሳ ዛሬ ላይ መቋጫ አግኝቶ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በምርጫ ህግ መተዳደር ከጀመሩ ድፍን አስራ ሰባት ዓመታትን አስቆጥራል፡፡ በዚህም አራት ሀገራዊ፣ ሶስት የአካባቢ እና በርከት ያሉ ዴሞክራሲያዊ የሟሟያ ምርጫዎች አከናውነዋል፡፡

በሀገራችን ባለፉት ጊዜያት የተከናወኑ ምርጫዎች በስኬት እንዲጠናቀቁ መራጩ  ህዝብ፣ የሀገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የሀገሪቱ የምርጫ ቦርድ የተጫወቱት ሚና ለሀገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ማበብ የላቀ አስተዋጽኦ ነበረው፡፡ ምርጫ ቦርድ በሀገሪቱ ሰላማዊ እና ህግን የተከተለ ምርጫ እንዲኖር የቡሉን ሚና ተወጥቷል። ተግባሩንና ኃላፊነቱንም ለማንም የፖለቲካ ድርጅት ሳይወግን እንዲሁም የሀገሪቱን የምርጫ ሥነ - ምግባር ደንብ ባስከበረ መልኩ ማከናወኑ ሊመሰገን የሚገባው ነው፡፡

ከወራት በኋላ በሀገራችን የሚከናወነው የአካባቢ እና የአዲስ አበባ ምክር ቤቶች ምርጫ ነፃ፣ ፍትሃዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና ፍጹም ተዓማኒ ለማድረግ ቦርዱ የተለያዩ ተግባራት እያከናወነ ይገኛል፡፡ ከእነዚህ መካከልም የዜጎች የሥነ - ዜጋ ማስተማሪያ ማንዋልን ቀርፆ ስልጠና እየተሰጠ ነው፡፡ ቦርዱ ከገጽ ለገጽ ስልጠና በተጨማሪ፤ በ13 የተለያዩ ቋንቋዎቸ የሥነ -ምግባር አስተምህሮዎች በስምንት የመገናኛ ብዙሃን እያስተላለፈ ይገኛል። ይህም መራጮች የምርጫ ደንቦችን እና ህጎችን እንዲያውቁና አቅማቸውን ይበልጥ እንዲጎለብቱ የሚያደርግ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የሀገሪቱ የምርጫ ሂደት ከጊዜ ወደ ጊዜ ይበልጥ ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴዎች ማከናወኑን ቀጥሏል፡፡ ምርጫው በስኬት እንዲጠናቀቅም እንደ ወትሮው ለፖለቲካ ፓርቲዎች እየሰጠ የሚገኘው ስልጠና ሳይጠቀስ አይታለፍም፡፡ ምርጫ ቦርዱ ህገ - መንግሥቱ በሚደነግገው መሰረት ከየትኛውም የፖለቲካ ድርጅት ያልወገኑ ገለልተኛ፣ ብቃት ያላቸውን የምርጫ አስፈጻሚዎች የመመልመል፣ ስልጠና የመስጠት፣ በምርጫ ስራ እንዲሰማሩ የማድረግ እና ሌሎች እንቅስቃሴዎችን የማከናውን ስራዎችን ገቢራዊ እያደረገ ይገኛል፡፡ ከዚህም አልፎ ምርጫውን የተመለከተ አንዳንድ ጭፍን አመለካከት የተጠናወታቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ስለ ቦርዱ የሚሰጧቸው መሰረተ- ቢስ መግለጫዎችን ብስለት በተሞላበት አካሄድ ትክክለኛ ምላሽ ከመስጠትም አልተቆጠበም፡፡

የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ‘ከእገሌ ፓርቲ ጋር እሰራለሁ’ በማለት ህገ-መንግስቱን ተፃርሮ የቀመበት ጊዜም ሆነ ታሪክ የለውም። ይልቁንም ሁሉንም በህገ - መንግስቱ ጥላ ስር የታቀፉ ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በእኩል ዓይን በማየት እና ፓርቲዎቹ የሀገራችንን የምርጫ ሥነ - ምግባር ህግ ተከትለው እንዲንቀሳቀሱ ኃላፊነቱን በብቃት እየተወጣ የመጣ ተቋም ነው፡፡

በሀገራችን ያሉ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫው ተሳታፊ ሊሆኑ የሚችሉት የሀገሪቱ የበላይ ህግ የሆነውን ህገ - መንግስት አክብረው እና አስከብረው ሲንቀሳቀሱ ብቻ እንደሆነ ከማንም የተሰወረ ጉዳይ አይደለም፡፡ እስካሁን ካለው ተሞክሮ እንደሚታየው  በህገ - መንግስቱ ታቅፈው በሀገራቸው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ምጣኔ ሀብታዊ ብሎም ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ተሳትፎ የሚያደርጉ ጥቂት የፖለቲካ ፓርቲዎች መፈጠራቸው አይካድም፡፡ እነዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች እርስ በርሳቸው በሰላማዊ እና በሰለጠነ መንገድ ችግሮቻቸውን ሲፈቱ ተስተውሏል፡፡

ፓርቲዎቹ የምርጫ ሂደቱ ምን መምሰል እንዳለበት እንዲሁም አባላቶቻቸው ምን ዓይነት ሥነ - ምግባር ሊያሟሉ እንደሚገባቸው የፈረሙትን የመግባቢያ የምርጫ የሥነ- ምግባር ደንብ መተግበራቸው ለህዝብ ያላቸውን አክብሮት ያሳያል፡፡ ግና ውድ አንባቢዎቼ የዛሬው ጽሑፌ መነሻ ይህ አለመሆኑን እንደምትገነዘቡልኝ ተስፋ አደርጋለሁ። የፅሑፌ አነሳሽ ምክንያት የገዛ ሀገራቸውንና ህዝባቸውን ያለ ምንም ተጨባጭ እውነታ ምርጫ በደረሰ ቁጥር፤ ‘ምርጫው ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ ሊሆን አይችልም፣ የፖለቲካው ምህዳር ስለጠበበ በምርጫው አንሳተፍም’ የሚሉ ፈሊጦቻቸውን እየደረደሩ የጨለምተኝነት ዲስኩራቸውን የሚያሰሙንን ተቃዋሚ ተብዬዎችን ማጋለጥ ነው፡፡

እነዚህ የሀገሪቱን የበላይ ህግ አክብረው የማይንቀሳቀሱ ተቃዋሚዎች መንግስት ዘወትር ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ደግሞ ደጋግሞ ቢነግራቸውም ጆሮ ዳባ ልበስ ማለትን የመረጡ ብቻ ሳይሆኑ በህገ-መንግስቱ ጥላ ስር ሆነው መልሰው ህገ-መንግስቱን በጦር ከጀርባው ለመውጋት ያሰፈሰፉ ወገኖች ናቸው፡፡

ተቃዋሚ ፓርቲዎች መንግስት ከድክመቱ ሊማርበት ይገባል ብለው የሚያነሷቸውን ነጥቦች ማሳየት ተስኗቸው ለመቃወሚያ ይሆነናል ያሉትን ነገር በጨለምተኝነት ውስጥ ተዘፍቀው የሚያነበንቡ ናቸው። ዘወትር የህዝብን ሰላም አደጋ ላይ የሚጥል ተግባር እና የሀገርን ዕድገት የሚያቀጭጭ ሴራ ለመቀመር ሳይተኙ የሚያድሩ ኃይሎች ናቸው ብል ከዕውነታው ብዙም የራቅኩ አይመስለኝም፡፡

የፖለቲካን ትርጉም ሳይረዱ ፖለቲካኞች ነን የሚሉ እነዚህ ተቃዋሚ ተብዬዎች እርስ በርሱ በሚጣረስ ፋይዳ ቢስ አስተሳሰብ እያፈለቁ፤ ምርጫ በመጣ ቁጥር ሲፈልጉ ‘ዴሞክራሲያዊ ምርጫ የለም’ ሲያሻቸው ደግሞ ‘ምርጫው ተጭበርብሯል’ የሚሉ ኢ-ነባራዊና ፀረ-ህገ-መንግስታዊ ትንበያቸውን ህዝቡ በማወቁ አንቅሮ ተፍቷቸዋል፡፡
“ሞኝ ሁሌም አንድ ነው ዘፈኑ” እንዲል የሀገራችን ሰው የእነዚህ ኃይሎች ዓላማ የሁከትና የብጥብጥ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው፡፡ ይህን አስገራሚ ህልማቸውን በዚች ሀገር እንተገብረዋለን ብለው እያሰቡ ከሆነ በእሳት እየተጫወቱ እንደሆነ ማወቅ ግድ ይላቸዋል፡፡ ምክንያቱም የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እንዲህ ዓይነቱን ፀረ-ህገ-መንግስት እሳቤ የሚያስተናገዱበት እንዲሁም መንግስት ምንግዜም የህግ - የበላይነትን ለማረጋገጥ ቁርጠኛ አቋም ያለው በመሆኑ ነው፡፡

ግና ተቃዋሚ ተብዬዎች ሰሞኑን አዲስ የመነጋገሪያ አጀንዳ በመክፈት ‘በመጪው ሚያዚያ ወር ምርጫ አንሳተፍም’ በማለት የወሬ ማራገቢያቸው በሆኑት በሀገር ውስጥ ጋዜጦች እና መጽሔቶች አማካኝነት እያራገቡ ነው። ከዚህ አልፎ ተርፎም “የትግል አጋራቸው” በሆነው የአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ ጣቢያ /በተለይም የአማርኛው ክፍል/ ‘የምርጫ ምህዳሩ ጠብቧል፣ ምርጫው ነጻ እና ዴሞክራሲያዊ ሊሆን አይችልም፤ የሀገሪቱ የምርጫ ቦርድ ለእገሌ ፓርቲ የሚወግን ነው ወዘተ…’ የሚሉ የሀሰት ውንጀላዎችን እየደረደሩ ነው፡፡

እነዚህ ተቃዋሚ ኃይሎች ለሰሚው በሚገርም ሁኔታ እርስ በርሳቸሁ እንኳን ለአንድ ቀን ሳይስማሙ በንትርክ እየዘለቁ የመጡ መሆናቸው ረስተውት፤ ዛሬ የምርጫ  የሥነ - ምግባር ደንቡን ካልፈረመው መድረክ ከተሰኘ ፀረ-ህገ መንግስት ሃይል ጋር እጅ እና ጓንት በመሆን ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ ተጎትተው እየተመሩ ነው፡፡

መድረክ ሀገሪቱ የምርጫ ሥነ - ምግባር ሰነድን ያልፈረመ ፓርቲ ነው፡፡ የፓርቲው ጽንፈኛ አመራሮች በሚያመቻችው ሁኔታ የሀገሪቱን ህገ - መንግስት በኃይል ለመጣል ከብቸኝነት አልፈው 34 ፓርቲዎቹም ወደ ራሳቸው አስተሳሰብ እያመጧቸው በእነሱ መዘውር እንዲራመዱ እያደረጉ ነው፡፡ የሀገራችን የምርጫ ሥነ - ምግባር ደንብ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የዴሞክራሲያዊ ምርጫ መመሪያ ብለው የቀመሩት ሰነድ ነው፡፡ ሰነዱ በቀጥታ ከዓለም አቀፍ የዴሞክራሲና የመረጫ ድጋፍ ሰጪ ተቋም /IDEA/ የተቀዳ ነው።

በዚሁ ሥነ - ምግባር ደንብ የተመራ ምርጫም በማንኛውም መስፈርት ነጻ፣ ዴሞክራሲያዊ እና እንከን የለሽ የሚያደርግ እንደሆነ ጥርጥር የለውም፡፡ ለዚህም ይህን የሥነ - ምግባር ደንብ ፓርቲዎቹ ተስማምተው ከፈረሙበት ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ የተከናወነውን አራተኛውን ሀገር አቀፍ ምርጫ መጥቀስ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ በ2002 ዓ.ም አራት የምርጫ ፓርቲዎች ማለትም ገዥው ፓርቲ፣ መኢአድ፣ ኢዴፓ እና ቅንጅት የምርጫ ሥነ - ምግባሩን ህግ አክብረው ሊንቀሳቀሱ በሚያስችላቸው መልኩ ተስማምተው በተፈራረሙበት ሰነድ ላይ በቁጥር 20 የተጠቀሰውን ማየት ተገቢ ነው፡፡

አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ መስቀል ወፍ ምርጫ በመጣ ቁጥር ብቻ ብቅ እያሉ፤ የትምህክተኝነት እና የጠባብነት አጀንዳቸውን ከማራመድ ውጪ የራሳቸው ወጥ የሆነ አጀንዳ ኖሯቸውም አያውቅም፡፡ ሁሌም ቢሆን በሌላ ፓርቲ አጀንዳ ላይ ተንጠላጥለው የራሳቸው በማስመሰል መደስኮር ልምዳቸው ከሆነ ሰነባብቷል። ለዚህም ነው በቅርቡ የመድረክ ብሔራዊ ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ተመስገን ዘውዴ “መድረክ በነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ተወዳድሮ ማሸነፍ የሚችል ስብስብ በመሆኑ በተለያዩ ሰንካለ ምክንያቶች ለውድድር እንዳይበቃ የማድረግ ሁኔታ አለ” በማለት ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ እንዲሉት ኛይነት ዓይን ያወጣ ተረት-ተረታቸውን እንካችሁ ያሉን።

አዛውንቱ የመድረክ ባለሟል በዚህ ብቻ አላበቁም። ለጥቀውም “ኢህአዴግ ከሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ሲወያይ መድረክን ያገለለው የሚፈራው ነገር ስላለ ነው” ሲሉ ዓይናቸውን በጨው ታጥበው በስተእርጅና ዋሽተውናል፡፡ ለነገሩ የእነ መድረክ ሰንካላ አስተሳሰብ ምን ሊሆን እንደሚችል መናገር ለቀባሪው የማርዳት ያህል ነው፡፡ ነገሩ የአብዬን ወደ እምዬ እንሚባለው ዓይነት መሆኑ ነው።

አቶ ተመስገን  የሰጡትን ቃለ - ምልልስ ከአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ መልሰው ቢያደምጡት ምን ያህል ሊያፍሩ እንደሚችሉ ግልፅ ነው፡፡ ለመሆኑ ሌሎች 34 ፓርቲዎች በፓርቲያቸው መሪነት በምርጫው አንሳተፍም እንዲሉ እያስደረገ ያለው ኢህአዴግ ነው ወይስ የአቶ ተመስገን ተጣማሪ ፓርቲው መድረክ?...እናስ ፈሪው ማን ይሆን?...እንደ እውነቱ ከሆነ መድረክ ህዝቡ ልብ ውስጥ ስለሌለ ገና ለገና የራሱን ፍራቻ በኢህአዴግ ላይ ለማጋባት ያሰበ ይመስላል። ይሁንና “ወጡ ሳይወጠወጥ ወስከንቢያው ቂጢጥ” እንደሚባለው፤ መድረክ ህዝቡ የዛሬ 3 ዓመት ገደማ በተካሄደው ምርጫ አንቅሮ ስለተፋው ዛሬ በስጋት ተወጥሮ ከተጨባጭ ዕውነታው ውጪ ቢያነበንብ የሚደንቅ አይደለም።

ዳሩ ግን መድረክ ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ የሚመራቸው 34 ፓርቲዎች ምንም ሊፈይዱለት አይችሉም። ሁሉም ከመድረክ ጋር በተለያዩ ጊዜያት ለመጣመር ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ነው። ከዚህ ይልቅ መድረክ የአመፅንና የሁከትን መንገድ ከመምረጥ ይልቅ ህግና ስርዓትን አክብሮ ቢንቀሳቀስ የሚበጀው ይሆናል።   ለነገሩ “ህግና ስርዓት” በተሰኘው ጉዳይ ዙሪያ እንዲሁም ከምርጫ ጋር በተያያዙ በወጡ አዋጆችና በአፈጻጸም መመሪያዎች ላይ በገዥው ፓርቲና በተቃዋሚዎች ዘንድ ያሉ አረዳድና ዕውቀት ይህን ያህል የሰፋ መሆኑ ያሳዝናል፡፡ የሀገራችን የተቃውሞ ጎራ አሳፋሪ ጥንካሬንም የሚያመላክት ነው።

እንዲህ ዓይነት ተቃዋሚነት በምን ዓይነት ስሌት ሀገርንና ህዝብን መምራት እንደሚችል የሚያውቁት መድረክና ጊዜያዊ ተጣማሪዎቹ ብቻ ናቸው። በምርጫ 2002 ወቅት በፓርቲዎች ስምምነት ተረቅቆ የሀገር ህግ የሆነው የምርጫ ሥነ - ምግባር ደንብን መድረክ አልፈርምም በማለት ረግጦ መውጣቱ ፖርቲው ምን ያክል ለህግና ለስርዓት ደንታ የሌለው መሆኑን ያስረዳል።

ሀገራዊ ህግን ከመፈረም ይልቅ በአቋራጭ የ“እንደራደር” ሰበብ አስባብን ይዞ እስካሁን ቆይቷል። እርግጥም ኢህአዴግ “መድረክ ህጉን ሳይፈርም ከእሱ ጋር ድርድር ብሎ ነገር አላደርግም” ማለቱ አቋሙን በተደጋጋሚ መግለፁ ተገቢነት ያለው ይመስለኛል። ምክንያቱም ህግን  የሚያውቁ አካላት፤ አንድ ህግ የሀገር ህግ ሆኖ ከወጣ ፈርም፣ አልፈርምም የሚል ክርክር ፋይዳ ስለሌለው ነው፡፡ ለምን ቢባል፤ አንድ ፖርቲ ቢፈርምም ባይፈርም፣ ቢስማማም ባይስማም ህጉን አክብሮ የመጓዝ ጉዳይ ለድርድር የሚቀርብ ባለመሆኑ ነው፡፡

ውድ አንባቢዎቼ ቀደም ሲል የጠቀስኩት የዴሞክራሲ እና የምርጫ አፈጻጸም ድጋፍ ሰጪ ተቋም /IDEA/ በመባል የሚታወቀውን ድርጅት ያዘጋጀውን የምርጫ ወቅት ፓርቲዎች የሥነ - ምግባር ኮድ እንደ መልካም ሰነድ በመውሰድ ገዥው ፓርቲ ጥሪውን ሲያቀርብ፤ ይህንን አክብረው ስምምነቱን ያልፈረመው ፓርቲ መድረክ ነበር ሲባል እንቆቁልሽ እንዳይመስልዎት። በወቅቱ መድረክ ከኢህአዴግ ጋር ለመደራደር ፍላጎት አለኝ ሌሎች ተቃዋሚዎችን ግን እንደ ተቃዋሚ አልቆጥራቸውም ብሎ ጀርባውን አዙሮባቸው እንደነበር ዛሬ ላይ ማውሳቱ ተገቢ ነው፡፡ በተለይም ያኔ የምርጫ ስነ-ምግባር ደንቡን ፈርሞ በሚደንቅ ሁኔታ ዛሬ ከመድረክና ከ34ቱ ፓርቲዎች ጋር የተጣመረው መኢአድን እንደ አባቱ ገዳይ ጠምዶ ይዞት ነበር፡፡ መኢአድ በምርጫ 2002 ወቅት የሀገሪቱ አራት ፓርቲዎች በጋራ ተስማምተው የሥነ - ምግባር ደንብ አክብሮ ሊመንቀሳቀስ ከፈረሙት ፓርቲዎች መካከል አንዱ ነው— የዛሬን አያድርገውና።

ከሰሞኑ የድርጅቱ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ወንድምአገኝ ደነቀ ከአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ ጋር ባደረጉት ቃለ - ምልልስ፤ “ከምርጫው በፊት ሊመለሱ የሚገባቸው ጥያቄዎች ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ጀምሮ ለፍትህ ቢሮዎች እንዲሁም መቀመጫውን አዲስ አበባ ባደረጉ የለጋሽ ሀገራት ቡድን ብናቀርብም ውጤቱን አላየንም ስለሆነም ካቀረብናቸው 18 ጥያቄዎች ከፖሊሲ፣ ከህግ፣ ከአዋጅ እና ከመንግስት አስተዳደራዊ መዋቅር የተገናኙ መሆናቸውን በመግለጽ ምርጫ ቦርዱ በራሱ ሊፈታው አይችልም እና የራሳቸውን ፓርቲ ብቻ ሳይሆን 34ቱ ፓርቲዎች ከምርጫው ልንገለል እንችላለን” ሲሉ ነበር— ቃል በቃል የተናገሩት፡፡  

መኢአድ ትላንት የፈረመውን የሀገሪቱ የምርጫ ሰነድ ገደል ገባ ስላለ እንደምን መጪው ምርጫ ተዓማኒነት ሊጎድለው እንደሚችል የኢንጂነር ሃይሉ ውቃቢ አምላክ ብቻ ነው የሚያውቀው፡፡ ያም ሆነ ይህ፤ የአቶ ወንድምአገኝ መሰረተ- ቢስና ከተረት ተረትነት ያልዘለለ መግለጫ፤ ትላንት የሀገሪቱን የሥነ - ምግባር ደንብ ፈርሞ ዛሬ መሸምጠጡ ከአንድ ነገ ሀገር አስተዳድራለሁ ከሚል ፓርቲ የሚጠበቅ ተግባር አይደለም፡፡ የመኢአድ ዕውነታም ወዲህ ነው።… ይኸውም ልክ እንደ መድረክ ሁሉ የኢንጂነር ሃይሉ ፖርቲም በምርጫው ተወዳዳሪ ሆኖ ማሸነፍ ስለሚሳነው ድክመቱን ለመሸፈን የተጠቀመው ዘዴ ለመሆኑ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡

ዳሩ ግን እነዚህ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች “ሁለት እግር አለኝ ብሎ ሁለት ዛፍ ላይ አይወጣም” የሚባለውን ሀገራዊ ይትብሃል የሚያውቁት አይመስልም። ምክንያቱም  በአንድ በኩል በህጋዊ ማዕቀፍ ተከልለን የፈለግነውን ነገር እንደርጋለን እያሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ህገ - መንግስቱን ተፃርረው መልሰው ህገ-መንግስቱን ቀዳድደው ለመጣል የሚያስችሉ ተግባራትን እናከናውናለን ማለት አንድም ስንዝር የሚያራምዳቸው ስለማይሆን ነው፡፡ ታዲያ የእነዚህ ህገ-መንግስቱን ቀዳዶ የመጣል ህልም ያላቸው ተቃዋሚ ተብዬዎች ሰንካላ እሳቤን ሳስብ ሁሌም በአዕምሮዬ የሚመላለሰውን አንድ ታሪክ ያስታውሰኛል፡፡ ነገሩም ወዲህ ነው።…

….ጊዜው 19ኛ ክፍለ ዘመን መባቻ ላይ ነው። በወቅቱ ጀርመን ውስጥ “የቫይማር ሪፐብሊክ” የተሰኘ ፓርቲ ነበር፡፡ በወቅቱ የቀኝ ክንፍ በመባል የሚታወቀውን የአምባገነኑ አዶልፍ ሂትለር ፓርቲ በሀገሪቱ በተደረገው ምርጫ እኔ አሸናፊ ከሆንኩ የሀገሪቱን የበላይ ህግ የሆነውን ህገ - መንግስት አክብሬ እና አስከብሬ ሀገርንና ህዝብን በስርዓት አስተዳድራለሁ በማለት የውሸት ቃል ይገባል፡፡ ምርጫው ተከናውኖ ሲያበቃ ዴሞክራሲያዊ ህገ-መንግስት የነበረው መንግስት ተሸንፎ የአዶልፍ ሂትለር ፓርቲ ስልጣን ያዘ፡፡ ከምርጫው በኋላ ወዲያውኑ አምባገነኑ የሂትለር ፓርቲ የሀገሪቱ ህገ - መንግስት ቀዳድዶ በመጣል ናዚያዊ ተግባሩን በይፋ አከናውኗል፡፡

ይህ የናዚ ታሪክ የሚያስተመረን ታላቅ ጉዳይ አለ። ይኸውም ህዝብ ናቂ የሀገራችን ተቃዋሚ ኃይሎች የማይገባቸውን ሥልጣን በአቋራጭ ለመጨበጥ ልክ እንደ ሂትለር ፓርቲ የሚመኙ መሆናቸው ነው። ምናልባትም የዚህ ፅሑፍ አንባቢ “የቫይመር ህልመኞች” ሊላቸው ይችላል። እኔ ግን “የሁለት ቢላዋ ተስፈኞች” ብያቸዋለሁ። ለምን ቢባል የእነርሱ ጉዳይ “ሲሞቅ በማንኪያ፣ ሲቀዘቅዝ በእጅ” እንዲሉት ዓይነት በመሆኑ ነው።   

ይሁንና በየትኛውም የፖለቲካ አካሄድ በሁለት ቢላዋ መብላት አይቻልም። ወጥ የሆነ አቋም ብቻ ነው መያዝ የሚቻለው። እናም መድረክና ሰሞነኛ ተጣማሪዎቹ በሰላማዊ መንገድ በምርጫው ከመወዳደር ውጪ ሌላ አማራጭ ያላቸው አይመስለኝም። አሊያ ግን ነገሩ “ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ” መባሉ አይቀሬ ይሆናል። ምክንያቱም በአንድ ሰላማዊ ሀገር ውስጥ ምርጫ በአመፅና በሁከት ሊከናወን አይችልምና።