የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ መጠናከር ለዘላቂ ልማት

  • PDF

ተስፋዬ ለማ (ታህሳስ 2/2005)

ወይዘሮ አበራሽ የ45 ዓመት እናት ናቸው፡፡ ተወልደው ባደጉባት በራያ አዘቦ በምትገኝ አንዲት መንደር ገና በ15 ዓመታቸው ነበር በወላጆቻቸው ግፊት ትዳር የመሰረቱት፡፡ የመጀመሪያ ልጃቸውንም በ16 ዓመታቸው ወለዱ፡፡

”እኔም ስለ ህክምና የማውቀው ነገር አልነበረኝም፡፡  በአካባቢው የህክምና ሰጪ ሰውና የህክምና መስጫ ተቋምም አልነበረም፡፡ ከሶስት ቀናት ከፍተኛ የምጥ ስቃይ በኋላ ወንድ ልጅ ተገላገልኩ፡፡ መቼስ እናት በወሊድ ጊዜ  የምታየውን የምጥ ጭንቀት ልጇን ስትወልድ ትረሳዋለች፤ በልጇ ትጽናናለች ትደሰታለች፡፡ እኔም እንደዚሁ ስቃዩን ረሳሁት፡፡ በልጄም ተደስትኩ፡፡” ካሉ በኋላ አንገታቸውን ደፍተው መንሰቅሰቅ ጀመሩ፡፡

እናስ? አልኳቸው ለቅሶውን ትተው ቀጣይ ታሪካቸውን ያጫውቱኝ ዘንድ፡፡ “ከዚያ በኋላ ልጄ ገና በስድስት ወሩ ሞተ፡፡ እኔም የሃዘን ሸማ ለበስኩ፡፡ የተደሰትኩትን ያህል ሃዘኑ ይባሱን ጎዳኝ፡፡ በወሊድ ጊዜ ተጎድቼ ስለነበረም በጠና ታመምኩ፡፡ ለስድስት ወራት ያህል ከተኛሁበት መደብ ሳልነሳ ማቀቅኩ፡፡ በአካባቢው ህክምና ብዙም አይታወቅም ነበር፡፡ እናም ታሞ ወደ አቅራቢያው የሚገኝ ከተማ ሄዶ ለመታከምም የአቅምም ሆነ የእውቀት ማነስ ከመኖሩም ባሻገር አመቺ ሁኔታ አልነበረም፡፡

“ከህመሜ እያገገምኩ መጣሁና ትንሽ ሰውነቴ ተመለሰ፡፡ ባለቤቴም የመጀመሪያ ልጁን በማጣቱ ብዙም ደስተኛ አልነበረም፡፡ የወላጆቼ ጉዳይ ሆኖበት እንጂ ወልዳ የማታሳድግ ሴት እድለ መናኛ ናት ተብሎ ይታመን ስለነበር ልቡ ተከፍሏል፡፡ ይሁን እንጂ ለፍች ግን አላሰበም ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ ላይ እያለሁ ሁለተኛ ልጄን ጸነስኩ፡፡

“ልጄ የኔ ታሪክ ዘግናኝ ነው” አሉና እምባ ተናነቃቸው፡፡ ለተወሰነ ደቂቃ ጸጥታ ሰፈነ፡፡ ከዚያም “ልጄ“ በማለት ንግግራቸውን ቀጠሉ፡፡ “ሁለተኛዋ ልጄ ሴት ነበረች፡፡ አሁንም አባቷ ደስተኛ መሆን አልቻለም፡፡ እሱ ይመኝ የነበረው ወንድ ልጅን ነበር፡፡ ወንድ ልጅ ወልዶ ማሳደግ አጋዥና አጋር ማግኘት ነው፡፡ ይህንን ሳውቅ እኔም ውስጤ በጣም ቢጎዳም  እንደምንም ችዬ ልጄን ማሳደግ ቀጠልኩ፡፡ ይሁን እንጂ እሷም አምስት ዓመት ሳይሞላት ሞተችብኝ፡፡ የባለቤቴ ቤተሰቦችና የአካባቢው ሰው በእኔ ጉድ አለ፡፡ እኔም ራሴን ረገምኩ እግዜርን አማረርኩ፡፡ እድለ መናኛ መሆኔንም አወቅኩ፡፡ ከዚያ በኋላ ባለቤቴን ትቼ ወደ አላማጣ ከተማ ገባሁ፡፡

“በከተማው በሴተኛ አዳሪነት ለአንድ አመት ሰራሁ፡፡ ከዚያ ውጭ ሌላ አማራጭ ስላልነበረኝ እንጂ ወድጄው አልነበረም፡፡ በዚህ መካከል  አንድ ሾፌር በወዳጅነት በመያዜ  አዲስ አበባ ወስዶ ሰው ቤት እንዲያስቀጥረኝ ተማጠንኩት፡፡ እሱም እንዳልኩት አደረገልኝ፡፡
“በሰው ቤት መስራት በጣም ከባድ ነው፡፡ የገባሁበት ቤት ባልና ሚስት አንዲት ልጅ ነበረቻቸው፡፡ ቤታቸው ሙሉ ነው፡፡ ሴትዬዋም የዋህና ለሰው የምትራራ ነበረች፡፡ ሁለቱም የየራሳቸው ስራ ነበራቸው፡፡ ህጻኗም ትምህርት ቤት ትውላለች፡፡ ወንድዬው አልፎ አልፎ ህጻኗን ይሸኝና ተመልሶ ወደ ቤት ይመጣል፡፡ እኔንም ለግንኙነት ያስቸግረኛል፡፡ በዚህ መካከል አንድ ሌሊት ባለቤቱን ትቶ መጣብኝ፡፡ እንዳልጮህ ሴትዬዋ ስለምትሰማ በሁለቱ መካከል ከፍተኛ ችግር ይፈጠራል እኔንም በማላውቀው አገር ከቤት ያባሩርኛል፡፡ በዚህ ምክንያት ዝምታን መረጥኩና ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በምስጢር ወዳጅነት ጀመርን፡፡

“ሰውየው ወደ ቤት እንደሚመላለስ ጎረቤቶቿ ይነግሯት ስለነበር መጠራጠር ጀመረች፡፡ ለእኔ የነበራት ሃዘኔታና ርህራሄም እየቀነሰ መጣ፡፡ ለባለቤቷም  ክብርን ነፈገችው፡፡ አብሯት ለመተኛት ሲሞክርም አለመፈለጓን ትገልጽለታለች፡፡ በዚህ የተነሳ አልፎ አልፎ ይጨቃጨቃሉ፡፡  አበባ በጣም ቆንጆ ወጣት ነበረች፡፡ ሃር የመሰለውን ጸጉሯ ትከሻዋ ላይ ስትለቀው የሚሰጣት ግርማ ሞገስ ልዩ ነበር፡፡ አፍንጫዋ ረጅም ሲሆን በረዶ የሚመስለው ጥርሷ ፈገግ በምትልበት ጊዜ ያለማጋነን የወንድን ቀርቶ የሴትን ቀልብ ትስባለች፡፡ ታዲያ ያችን ቆንጆ ትቶ ከእኔ ከባላገሯ ጋር ለመጋፋት ለምን እንደፈለገ ባላውቅም ተገድጀ ስለገባሁበት አማራጭ እንደሌለኝ አውቄ ፍላጎቱን ማሟላት ቀጠልኩበት፡፡

“እንደለመደው አንድ ቀን ልጁን ትምህርት ቤት ካደረሰ በኋላ ተመልሶ መጣ፡፡ ሁሌ እንደሚያደርገው ገፋፍቶ ወደ መኝታ ቤት አስገባኝና ተኛን፡፡ ጎረቤቶቹ እንዳይጠራጠሩ ስጋት ስለነበረው በሩን አይዘጋም ነበር፡፡ ድምጽ ሳታሰማ ወደ መኝታ ክፍሉ  የገባችው አበባ ድንገት ስትጮህብን መግቢያ አጣን፡፡ የአካባቢው ሰው ተሰበሰበ፡፡ አይናችሁ ይፍሰስ ሲልም ረገመን፡፡ እኔም ቤቱን ለቅቄ እንድሄድ አደረጉኝ፡፡ ከዚያ በኋላ የእነሱን ሁኔታ ባላውቅም እኔ ግን ሳልወድ ወደነበርኩነት የሴተኛ አዳሪነት ኑሮ ገባሁ፡፡

“በዚህ መሃል ልጅ ወለድኩ፡፡ አሁንም ሊሞትብኝ ይችላል እያልኩ በጣም እጨናነቅ ነበር፡፡ ሆኖም ግን በህክምና እርዳታ በመውለዴ ልጄ አሁን የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ ነው፡፡  ከአምስት አመት በፊት በጥቃቅንና አነስተኛ በመደራጀት የባልትና ሱቅ ከፍቸ በሰላም መኖር ጀመርኩ፡፡ አሁን እግዜር ይመስገን ስራዬን በማስፋት አስር ሰራተኞች ቀጥሬ ኑሮዬን ተያይዠዋለሁ፡፡ መኖሪያ ቤትም ሰርቻለሁ፤ የመነገጃ ገንዘብም ማጠራቀም ችያለሁ”  እርግጥ ነው ሴቶች ለድርብ ጭቆናና ስቃይ ሲዳረጉ ለዘመናት ኖረዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ የወይዘሮ አበራሽ ታሪክ አንድ ማሳያ ነው፡፡ በአገራችን ተመሳሳይ ችግር የሚያጋጥማቸው ሴቶች ቁጥር በአሃዝ ተጠናቅሮ አለመያዙ እንጂ የት የለሌ እንደሆነ መገመት አያዳግትም፡፡

በቀደሙት ስርዓታት ሴቶች ድርብ ጭቆና ይደርስባቸው እንደነበር ይታወቃል፡፡ እንደ ሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ይደርስባቸው የነበረው የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብታቸው መታፈን አንዱ ነው፡፡  ሌላው ደግሞ በጾታቸው ምክንያት ይደርስባቸው የነበረው ጭቆና ነው፡፡ በዚህም ለበርካታ ዓመታት ለሰቆቃና ለድርብ ጭቆና ተዳርገው እንደነበር ይታወቃል፡፡

ኢትዮጵያ  ድህነትን ታሪክ ለማድረግ የሚያስችላትን የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመንደፍ መንቀሳቀስ ከጀመረች ሁለት አስር ዓመታት ተቆጥረዋል። ፈጣንና ቀጣይነት ያለውን ልማት ለማረጋገጥ በሚደረገው ዘርፈ ብዙ ጥረት  የሴቶች ተሳትፎ የሚኖረው ድርሻ የጎላ ነው። እስካሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታም አገሪቱ እያስመዘገበች ባለችው ኢኮኖሚያዊ፣ ማሕበራዊና ፖለቲካዊ ስኬቶችም  ሴቶች የላቀ ድርሻ እንዳላቸው ለመገንዘብ ይቻላል፡፡

ከልማታዊ መንግስት መምጣት ጋር ተያይዞ በአገሪቱ የተካሄደው መሰረታዊ የፖለቲካ ለውጥ  ምክንያት ለመጀመሪያ ጊዜ የሴቶችን እኩልነት ያረጋገጠ ሕገ መንግስት ጸደቀ።

ከ1983 ዓም ጀምሮ ሴቶች ትርጉም ባለው መልክ በአገራቸው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ሙሉ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ለማስቻል የተለያዩ ተግባራት ተከናውነዋል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ነበር ወሳኝ ሚና መጫወት የጀመሩት፡፡

ቀደም ሲል በማሕበረሰቡ ሰርጾ የነበረው የጾታ ልዩነት ምክንያት ይፈጠር የነበረው የተጠቃሚነት ልዩነትና የአመለካከት ችግር ሙሉ በሙሉ ለማስወገድ ረጅም ጊዜና ከፍተኛ ጥረት የሚጠይቅ ቢሆንም ባለፉት 21 ዓመታት በተደረገው ጥረት መሠረታዊ ለውጦች እየተመዘገቡ መምጣታቸው የማይካድ ሀቅ ነው፡፡

ከማሕበረሰባችን ግማሽ ቁጥር የያዙት ሴቶች ልዩ ትኩረት ተሰጥቷቸው በአገራቸውና በራሳቸው መብቶች ዙሪያ ሙሉ ተሳታፊና የችግሮቻቸው የመፍትሔ አካል መሆን የሚችሉበት ሁኔታ መፍጠር ተችሏል፡፡ የሴቶች ተጠቃሚነትና ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል፡፡ መንግስት በወሰዳቸው የተለያዩ የልማት፣ የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር እንቅስቃሴዎች የሴቶችን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ረገድ የሚበረታቱ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡

የሴቶች መብት ሕገ-መንግስታዊ መብት እንዲሆን መደረጉ በቀዳሚት ሊጠቀስ የሚችል ጉዳይ ነው፡፡ በአገሪቱ ሕገ-መንግስት አንቀጽ 35 ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው ሴቶች ከወንዶች ጋር እኩል መብት አላቸው፡፡ ቀደም ሲል በሴቶች ላይ ይደርስ የነበረውን ጾታዊ ጭቆና ሙሉ በሙሉ እንዲነሳ የሚያስችል ሕጋዊ ከለላ አግኝተዋል፡፡ እንደሚታወቀው የበታችነት ስሜትት የኢኮኖሚ ጥገኝነትና ሌሎች ተመሳሳይ ችግሮች ለዘመናት የነበሩባቸው ቢሆንም የአገሪቱ ሕገ-መንግስት እነዚህን ድርብ ጭቆናዎች ለማስወገድ እኩል ተጠቃሚነታቸውን አረጋግጦላቸዋል፡፡

ሴቶች በመንግስትና በግል ተቋማት በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና ማሕበራዊ ጉዳዮች ከወንዶች ጋር እኩል ተወዳዳሪ እና ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማስቻል ሕገ-መንግስቱ የመጀመሪያው ትልቅ እርምጃ ነበር፡፡ በሕገ-መንግስቱ የተረጋገጠው የሴቶች እኩልነት ሴቶች የነበረባቸውን ተጽእኖ በማስወገድ በአመራርና በውሳኔ ሰጭነት የሚኖራቸውን ሚና ለማሳደግ እንዳስቻለ ይታመናል፡፡

ሕገ መንግስቱ ያረጋገጠውን መብት ተከትሎ የወጣው የቤተሰብ ሕግ ማሻሻያ የሴቶች ተጠቃሚነት እያደገ እንዲመጣ ቀላል የማይባል አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ሴቶች የንብረትና  የመሬት ባለቤት መሆን ችለዋል፡፡
የሴቶች ተጠቃሚነት በተቀናጀ መልኩ ማረጋገጥ እንዲቻልና ሁለንተናዊ ተሳትፏቸውን ለማረጋገጥ ብሔራዊ የሴቶች ፖሊሲና የኢትዮጵያ ሴቶች የልማትና የለውጥ ፓኬጅ እንዲነደፍና እንዲጸድቅ ተደርጎ እየተተገበረ ይገኛል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም የጤና፣ የትምህርትና የባህል ፖሊሲዎች በመውጣታቸው የሴቶች የልማት ተጠቃሚት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱ በተጨባጭ ታይቷል፡፡

የሴቶችን እኩልነት ማረጋገጥ ሲባል ሁለንተናዊ ተሳትፏቸውንና ተጠቃሚነታቸውን ማሳደግ ማለት ነው። በተለይ ደግሞ የአመራርና ውሳኔ ሰጭነት ክህሎታቸውን ማሳደጉና ማጎልበቱ ፋይዳው የጎላ ይሆናል። ይህንን ማድረግ የሚቻለው ደግሞ ሴቶችን ከኢኮኖሚ ጥገኝነት ማላቀቅ ሲቻል ነው፡፡ ሴቶችን በኢኮኖሚ ራሳቸውን የማስቻል ጉዳይ የሴቶችን ፖለቲካዊ ተሳትፎ የማሳደግ ጉዳይ በመሆኑ በዚህ ረገድ መንግስት ቀላል የማይባል እንቅስቃሴ አድርጓል፡፡ 

የሴቶችን እኩልነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና የአመራርና ውሳኔ ሰጭነታቸውን ለማጎልበት በሚደረገው ጥረት ቀላል የማይባል ድርሻ ያለው ሌላው ነገር ሴቶች ትርፍ ጊዜ ማግኘት የሚችሉበትን ሁኔታ መፍጠር ነው። ሴቶች በቤት ውስጥ ያለባቸውን ጫና ሙሉ በሙሉ ለመቀነስ እንዲቻል መንግስት አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን መጠቀም የሚያስችላቸውን የተለያየ እንቅስቃሴ በመደረግ ላይ ይገኛል፡፡  ከዚሁ ጎን ለጎን በግብርና ዘርፍ፣ በጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ሴቶችን በሰፊው ተጠቃሚ የማድረጉ ተግባር ቀጥሏል፡፡

በኢትዮጵያ የማዕከላዊ ስታስቲክስ ባለስልጣን የተጠናቀረ የ2000 ዓም መረጃ እንደሚያሳየው የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር 74 ሚሊዮን ይደርሳል። ከዚህ መካከል 37 ሚሊዮን የሚጠጉት ሴቶች ናቸው፡፡ ይህም ማለት ከአገሪቱ ሕዝብ ግማሽ ያህሉ  ሴቶች መሆናቸውን ነው፡፡ የሴቶች ውሳኔ ሰጭነት ላይ ለዘመናት የነበረውን ክፍተት ለመድፈን በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡

የሴቶችን የፖለቲካ አመራርና የውሳኔ ሰጭነት ተሳትፎ ለማሳደግም ቀደም ካሉ ዓመታት ጀምሮ የተለያዩ ተግባራት በመከናወን ላይ ይገኛሉ፡፡ የሴቶችን ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቸ ለማስከበር በሚደረገው ጥረት ወሳኝ ሚና እንዲኖራቸው የተለየ የሥልጠና ፕሮግራም በማዘጋጀትም በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡

በዚህ ምክንያት የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል። ለዚህ ትልቅ ማስረጃ የሚሆነውም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሴቶች ተሳትፎ እየጨመረ መምጣቱ ነው፡፡ በ1987 ዓ.ም ሕገ መንግስቱ በጸደቀ ማግስት በተካሄደው የመጀመሪያው ታሪካዊ ምርጫ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከነበሩት መቀመጫዎች አስራ አምስቱ የተያዙት በሴቶች ነበር፡፡

በአገሪቱ በሁሉም ዘርፎች የሴቶች ተሳትፎ እያደገ በመምጣቱ ምክንያት በ1992 ዓ.ም በተካሄደው አገራዊ ምርጫ 42 ሴቶች በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተሳትፎ ነበራቸው፡፡ ይህ አኃዝ በሦስተኛው አገራዊ ምርጫ 117 ደርሷል፡፡ ከምርጫ ቦርድ የተገኘ መረጃ እንደሚያሳየው ደግሞ በ2003 ዓ.ም በተካሄደው አራተኛው አገራዊ ምርጫ ፓርላማ የገቡ የሴቶች ቁጥር 159 ደርሷል፡፡ ይህ ከአጠቃላይ የፓርላማ አባላት 29 በመቶውን ይሸፍናል፡፡

የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ በከፍተኛ ደረጃ እያደገ መምጣቱ መንግስት ሴቶችን ለማብቃት የወሰዳቸው የተለያዩ የስልጠናና የአቅም ግንባታ ተግባራት ፍሬ ለመሆኑ አያጠራጥርም፡፡ ይሁንና የሴቶችን ተሳታፊነት ይበልጥ ከማሳደግ አንጻር አሁንም ቀጣይ ስራ ስለሚያስፈልገው በተቀናጀ መልክ እየተከናወነ ይገኛል፡፡

በፌዴራል ደረጃ ካለው የሴቶች የፓርላማ ተሳትፎ አንጻርም በክልሎችም ለምሳሌ በትግራይ 50 በመቶ፣ በኦሮሚያ 37 ነጥብ 7 በመቶ፣  በሐረሪ 33 እና  በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች 20 በመቶ  ደርሷል፡፡

መንግስት የሴቶችን የፖለቲካ ብቃትና የአመራር ክህሎት ለማሳደግ ልዩ ትኩረት በመስጠት በአምስት ዓመቱ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ 30 በመቶ በከፍተኛ፣ 50 በመቶ በመካከለኛና በዝቅተኛ አመራርነት ለማብቃት እቅድ በመያዝ ባለፉት ሁለት የእቅዱ ትግበራ ዓመታት አበረታች ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡ በእቅዱ እንደሰፈረው መንግስት በህግ ተርጓሚው አካልም የሴቶችን ተሳትፎ ወደ 25 በመቶ ለማሳደግ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡

በዚህ መሰረት ባለፉት ሁለት ዓመታት በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡ የሴቶችን ተሳትፎ የበለጠ ለማጠናከር እንዲቻል 1225 የሴት አደረጃጀቶችን ለማጠናከር ተችሏል፡፡

የሴቶችን የኢኮኖሚ አቅም ለማሳደግ ስድስት ሚሊዮን ዮሮ ተዘጋጅቶ በቀጣይ ሊሰራበት ዝግጅት ላይ ነው፡፡ በአስራ ሶስት ዩኒቨርስቲዎች ለሚማሩ 318 ሴት ተማሪዎች የፋይናንስ ድጋፍ ለማድረግ ሁለት ሚሊዮን ብር የሚጠጋ በጀት በፌዴራል ደረጃ ተይዞ ሥራው በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡

ከፌዴራል ሴቶች፣ ወጣቶችና ሕፃናት ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ እንደሚያሳየው ባለፈው የበጀት ዓመት 40 ሴቶች በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ በሁለተኛ ድግሪ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ድጋፍ ተደርጓል፡፡ በተጨማሪ ልዩ ድጋፍ በሚፈልጉ ክልሎች ለሚሰሩ 80  ሴት ሠራተኞች በሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ በክረምት መርሀ ግብር ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ድጋፍ ተደርጓል፡፡

በገጠርም በርካታ ሴት ገበሬዎች ከዝቅተኛ ኑሮ ተነስተው ባለሃብት የሆኑበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ በመስኖ እርሻና በእንስሳት እርባታ በሰፊው እንዲሰማሩ አመቺ ሁኔታ ስለተፈጠረላቸው ዘመናዊ አሰራርን ተግባራዊ በማድረግ ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ ተችሏል፡፡

የትምህርት ተሳትፎን በተመለከተም በአገሪቱ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ለማዳረስ በተነደፈው እቅድ መሰረት የሴቶችን ተጠቃሚነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው፡፡ ትምህርትን ለሁሉም ዜጎች ለማዳረስ በተደረገው ጥረት በአሁኑ ወቅት 20 ሚሊዮን የሚሆኑ ህፃናት በትምህርት ማዕድ ላይ ታድመዋል፡፡ ከነዚህ ውስጥ ግማሽ ያህሉ ደግሞ ሴቶች ናቸው፡፡  ሴቶችን በትምህርት የማብቃት ጉዳይ  የሥርዓተ ጾታ እኩልነትን የማረጋገጥ ጉዳይም እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ከዚህ አንፃር ከሕገ-መንግስቱ መጽደቅ ጀምሮ የተለያዩ የሕግ ማዕቀፎችን በማዘጋጀት በተገቢው መንገድ እንዲፈጸሙ እየተረገ ይገኛል፡፡

አገሪቱ ድህነትን ታሪክ ለማድረግ አገሪቱ የተለያዩ የድህነት ቅስቀሳ ስትራቴጂዎችን በመንደፍ በላቀ የአፈጻጸም ደረጃ ላይ እንዳለች እሙን ነው፡፡ በዚህ በድህነት ቅነሳ ፓኬጅ የሴቶችን ተሳትፎ ለማጎልበትና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችል ስራ ተከናውኗል፡፡

ከተወሰዱት እርምጃዎች መካከል መጠቀስ ያለበት ሌላው ጉዳይ የህፃናት ሞት ነው፡፡ እናቶች ልጆቻቸው ገና በለጋ እድሚያቸው ወደዚህች አለም በተቀላቀሉበት ማግስት ለህልፈተ ህይወት ሲዳረጉባቸው ለከፋ ጉስቁልናና ለመረረ ሃዘን ይዳረጋሉ፡፡ እናቶችን ከሚጎዱ ነገሮች የህጻናት ሞት አንዱና ዋናው ነው፡፡ ከእናቶች አንጻር ስናየው የህጻናትን ሞት ለመቀነስ የተኬደበት ርቀትና የተመዘገበው ስኬት የጎላ ድርሻ እንዳለው ለመገንዘብ አያዳፍትም፡፡

በአገሪቱ ለህፃናት እድገትና ጤንነት መሰናክል የሆኑ የተለያዩ በሽታዎች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያሳየው ከበሽታዎቹ መካከል 20 በመቶ ወባ፣ 28 በመቶ የሳምባ ምች፣  20 በመቶ  ውሃ ወለድ በሽታዎችና 25 በመቶ ደግሞ የጨቅላ ህፃናት የጤና ችግሮች ናቸው፡፡ በእነዚህና ሌሎች ተመሳሳይ በሽታዎች  ምክንያት በ1993 ዓ.ም የመጀመሪያ ዓመት ልደታቸውን ሳያከብሩ ከአንድ ሺሕ ህፃናት 97 ይሞቱ ነበር፡፡ ይህ አኃዝ በ1997 ዓ.ም ወደ  77 ዓ.ም ዝቅ ካለ በኋላ በ2003 ዓም ደግሞ ወደ 45 ወርዷል፡፡

በተመሳሳይ መልኩ በ1993 ዓ.ም ከአምስት ዓመት በታች ከአንድ ሺህ ህፃናት ውስጥ 167ቱ ይሞቱ ነበር፡፡ በ1997 ዓ.ም ወደ 123 ከወረደ በኋላ  በ2003 ዓ.ም ወደ 101 ዝቅ ብሏል፡፡ በመሆኑም የእናቶችን ስቃይ ለመቀነስ የልጆቻቸውን ጤንነት መጠበቅ  ተጠቃሚ ከሚያደርጓቸው ነገሮች መካከል ዋንኛው ነው፡፡ ሕጻናቱ የነገይቱ ኢትዮጵያ ተረካቢዎች በመሆናቸው በዚህ ረገድ የተመዘገበው ስኬት አበረታች ነው፡፡

የህጻናቱን ሞት መቀነስ ብቻ ሳይሆን የእናቶችን ጤና ማሻሻል የተቻለበት ሁኔታ መፈጠሩንም መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በዚህ ረገድም በ1998 ዓ.ም የወጣው የሥነ-ህዝብ ጤና ጥናት እንዳመለከተው በ1987 ዓ.ም በህይወት ያሉ ህፃናትን ከወለዱ አንድ መቶ ሺህ እናቶች 871 ይሞቱ ነበር፡፡ በ2007 ዓ.ም ላይ ይህን ቁጥር ወደ 267 ለማውረድ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል፡፡

ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የሴቶችን ተሳትፎ ለማጎልበትና በአገሪቱ እውን እየሆነ የመጣውን የሰላም፣ የዴሞክራሲና የልማት ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ ለማስቻል በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል፤ስኬቶችም ተመዝግበዋል፡፡ በተለይም ሴቶች በትምህርት፣ በጤና፣ በንግድና በሌሎች ዘርፎች ተጠቃሚዎች መሆን ችለዋል፡፡ በአምስት ዓመቱ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድም የሴቶችን ተጠቃሚነት ትርጉም ባለው መልክ ለማረጋገጥ የሚያስችል ትኩረት ተሰጥቶታል፡፡