አዲስ ታይምስ እና የአባይ ጥያቄ፤ ይበል የሚያሰኝ ለውጥና ያልተመለሱ የሚመስሉ ግን የተመለሱ ጥያቄዎች

  • PDF

ዮናስ (ታህሳስ 2/2005)

የህዳር 2005 “አዲስ ታይምስ” መጽሄት ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫና የኤዲቶሪያል መልዕክት ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጋር የተያያዘ፣ በተለያየ ዘውግ በቀረቡና የህዳሴው ግድብ ግንባታ ለኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ ስለመሆኑና ምንም አይነት ተፈጥሮአዊም ሆነ ህጋዊ ከልካይ ሊኖርብን እንደማይችል በሚያወሱ መጣጥፎች ተሞልታ ለንባብ በቅታለች፡፡

እንደአጠቃላይ የአዲስ ታይምስ መፅሄት አዘጋጆች፤የፍትህ ጋዜጣ አባላቶች የነበሩ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ የህዳሴው ግድብ የመሰረት ድንጋይ ከተጣለበት ጊዜ አንስቶ በግድቡ ዙሪያ የነበራቸውን አቋምና ሲያስተላልፉ የነበሩትን መልእክቶች ከግምት በመክተት በመጽሄቷ ላይ ያሰፈሩት ሃሳብ በእርግጥም ለእኔ ትልቅ ለውጥና እንደ ዜጋ የልማቱ አካል ለመሆን የሰነዘሩት ሃሳብ በጣሙን ተመችቶኛል፡፡

ሆኖም ግን አሁንም ቢሆን ከህዳሴው ግድብ ጋር በማያያዝ በተለይም በኤዲቶሪያል ማጠቃለያቸው አካባቢ ያቀረቡት ሃሳብ መስተካከል የሚገባው እንደሆነ በማመን እነዚህን ያልተመለሱየአዲስ ታይምስ ባልደረቦች ጥያቄ ለማመላከትና ለመመለስ እሞክራለሁ፡፡

አዲስ ታይምስ በአባይ ጥያቄ ላይ ያሳየችው ለውጥ ምንድ ነው?

ቀደም ሲል ፍትህ ጋዜጣስለታላቁ የህዳሴ ግድብ ስታወሳ "ግድቡ ለይስሙላ የተደረገና በጥናት ያልተደገፈ፤ በአንድ አዳር ኢህአዴግ ያለመው ነው፣"ከሚሉ አጀንዳዎች ጀምሮ ለዚህ "ምናባዊ" ግድብ ህዝቡ ማዋጣት እንደሌለበትና ከኢህአዴግ ጋር አብሮ ከበሮ መደለቅ እንደማይገባው የሚያወሱ፤ በተለይም ደግሞ ግድቡ የታሰበው የአረቡ አለም አብዮት በኢትዮጵያ ይደገማል ከሚል የገዢው ፓርቲ ስጋት በመነሳት በመሆኑ ማንም ከአመጻ  መንገድ ሊዘናጋ እንደማይገባው የሚያወሱ በርካታ አፍራሽ ዘገባዎችን ለንባብ አብቅታ እንደነበር አንዘነጋም፡፡

ሌሎችንም ከህዳሴው ግድብ ጋር የተያያዙ የፍትህ ዘገባዎች ማስታወስ ይቻላል፡፡ የአምስት አመቱ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ውስጥ ያልነበር ነገር ግን አሁን የመጣ የፖለቲካ ማታለያ ነው፤ ስትል የነበረችው ፍትህ ለግድቡ ተብሎ የሚሰበሰበው ገንዘብ ህዝቡንየመዝረፍ ዘዴ ነውም ስትል አስነብባን ነበር፡፡ ለዚህም ዘረፋ አስረጅ ነው ስትል ፍትህ ጋዜጣ ያቀረበችልን አብዛኛው መዋጮ እየተካሄደ ያለው በባለስልጣናትና ካድሬዎች ተጽእኖ ነው ብላን እንደነበር እናስታውሳለን፡፡

ፍትህ መች በዚህ  ብቻ ልታበቃ፤ ሌላም ብላን ነበር፡፡ ህብረተሰቡ በኑሮ ውድነት እና በረሃብ እየረገፈ ይህን ያህል ወጪ ያለው ግድብ መገንባት ቅድሚያ ሊሰጠው አይገባም፤ ስትል አስነብባን የነበረችው ፍትህ ግድቡ የታቀደውና የተጀመረው ያለበቂ ጥናትና ቅድመ ዝግጅት ነው ፤በደለል የመሞላት እድሉም በጣም ከፍተኛ ነው ስትል በግድቡ ዙሪያ ነፃና በቂ መረጃ ለማግኘት አልተቻለም፤ የግድቡን ስራ በተመለከተ ሁሉንም በሚያሳትፍ መልኩ ግልጽ የአሰራር ስርዓት አልተዘረጋምም ብላን ነበር፡፡

የዚህችው ጋዜጣ አዘጋጆችና ከላይ የሰፈሩትን ሃሳቦች ሲያስተላልፉ የነበሩት የፍትህ አምደኞች ዛሬ በአዲስ ታይምስ መጽሄታቸው ላይ የግድቡን እውንነት በማጤን እና የጀመሩት ጉዞ እሾሃማ የነበረ መሆኑን በመገንዘብ፤ አልያም እኛ በማናውቀውና እነርሱ በሚያውቁት ምክንያት ስለግድቡ ስኬት በተለይም በዲፕሎማሲው ረገድ መከናወን ስለሚገባቸው ተግባራቶች፤ እንዲሁም ግድቡ የሉዓላዊነታችን መገለጫ ከመሆኑ አንፃር የሁላችንም ጉዳይ መሆኑን ማመላከታቸው በምንም የመነሻ ምክንያት ይሁን ይበል የሚያሰኝና የሚያበረታታለውጥ ነው፡፡ሆኖም ግን እነዚህ የአዲስ ታይምስ መጽሄት አዘጋጆችና አምደኞች በፍትህ ጋዜጣ ላይ ግድቡን በተመለከተ ሲያስተላልፉ ከነበረው መልእክት አሁንም ያልተቀየሩ ሃሳቦችን ሊያውም በኤዲቶርያል መልእክታቸው አስፍረዋል፡፡

“አሁን እየተገነባ ያለውን ግድብ ለመጨረስ ከአንድ ፓርቲ የፖለቲካ ጥቅም መዝለልና ጉዳዩንም ሀገራዊ እንዲሆን ማድረግ የግድ የሆነበት ደረጃ ላይ ስለደረስን ብዙ ለውጦችን፣ ብዙ ማሻሻያዎችን ከመንግስት እንጠብቃለን፡፡ ስለዚህም ከግድቡ ጋር በማያያዝ ለገዢው ፓርቲ ፕሮፓጋንዳና አንዳንድ ፖለቲካዊ ችግሮችን ማስተንፈሻ የማድረጉን ጉዳይ አጥብቀን እንቃወማለን፡፡ የሀገር ብሄራዊ ጥቅም ከፖለቲካዊ ልዩነትና ከስልጣን ማስጠበቂያነት በላይ እና ውጭ ነው፣" ይላል የአዲስ ታይምስ ኤዲቶርያል፡፡
ይህ የማጠቃለያ መልእክት ለእኔ ቀድሞ የተመለሰና መሞገቻ ለመሆን በማይበቁ መሰረት የለሽ ሃሳቦች  የታጨቀ መሆኑ ነው የሚያመላክተው፡፡ ስለሆነም ስለታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ውጪያዊ ገጽታ በአዲስ ታይምስ መልእክቶች ተስማምቼ ከላይ በሰፈረው ሃሳብ ላይ ግን ሙግቴን እቀጥላለሁኝ፡፡ በተለይም “ግድቡ ለፖለቲካ ፍጆታ ውሏል” የሚለውን ሃሳብ እና “ፖለቲካዊ ችግሮችን ማስተንፈሻ የማድረጉን ጉዳይ እንቃወማለን” የሚለውን የመጽሄቷ መልእክት እኔም በሙግቴ አጥብቄ የምቃወም መሆኔን አስረጅ በማቅረብ እገልፃለሁ፡፡

የግድቡ  ፋይዳ

በአባይ ወንዝ የመጠቀም መብታችን እውን እንዲሆን የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዘመናት ምኞት፤ ፍላጎትና ቁጭት እንደነበር አይዘነጋም፡፡ መንግሥትም ልማትን ለማፋጠን ካለው ቁርጠኝነት የተነሳና ከዚህም ጋር ተያይዞ በተፈጥሮ ሃብታችን የመጠቀምና የመበልጸግ የኢትዮጵያ ሕዝቦችን የዘመናት ጥያቄ ለመመለስ ከዚህ በፊት በነበሩ መንግሥታት ባልተሞከረ ሁኔታ መንግሥት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡   አዲስ ታይምስየአባይ ግድብ ግንባታ"ለፖለቲካ ፍጆታነት ውሏል፣ችግር ማስቀየሻ ሆኗል፣" የምትለው ሃሳብ ውሃ የማያነሳና ፍሬ አልባ መሆኑን መሞገት ተገቢ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ከላይ በተገለጸው የመንግሥትና የሕዝብ አቋም የተነሳ አባይን ለልማት የማዋል እንቅስቃሴያችን የተመሰረተው ሀገራችን ከፍተኛ የልማት ፍላጎት ያላት ሀገር ከመሆኗ እና ህዝቦቿም ከድህነትና ኋላ ቀርነት ለመላቀቅ ያላቸው አማራጭ ልማትን ማፋጠን ከመሆኑ ጋር የተያያዘበመሆኑ ነው፡፡

በአባይ ላይ የመጠቀም መብትን አስመልክቶምከዚህ በፊት የነበረውና  አገራችንን ጨምሮ ሌሎች የላይኛው ተፋሰስ አገራትንያላካተተው የዓባይ ውሃ አጠቃቀም ስምምነት በአዲስ ድርድር የሁሉም የተፋሰሱ ሃገራት ፍትሐዊና የጋራ የውሃው ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ መንግስትጽኑ አቋም በመያዙ  አዲስ ስምምነት እንዲፈረም የበኩሉን ገንቢ ሚና ተጫውቷል፡፡ ምንም እንኳን እስካሁን ባለው ሁኔታ ግብጽ እና ሱዳን በስምምነቱ ላይ ፊርማቸውን ያላሳረፉ ቢሆንም ይህ አዲስ ስምምነት ለቀጣይ ድርድርና የጋራ ተጠቃሚነት መረጋገጥ መሰረት የጣለ በመሆኑ ፋይዳው የጎላ ነው፡፡

የዚህ ግድብ መገንባት አገራችንን ከድህነትና ከኋላ ቀርነት በማላቀቅ ወደፊት እንድንጓዝ የሚያስችለን ከመሆኑም በላይ በአጠቃላይ መንግስት በያዛቸው አላማዎች ላይ ብሄራዊ መግባባትን በመፍጠር ህዝቡ በዘለቄታዊነት ለእድገቱ ተሰላፊ የሚሆንበትን ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ በሌላ በኩል ግብ ፍትሃዊ አጠቃቀምን በተመለከተ መንግስት እያደረገ ያለው  ጥረት አውቆ የተኛ እንዲሉ ካልሆነ በስተቀር ከጊዜ ወደጊዜ በሃገራችን ህዝቦች ብቻም ሳይሆን በአለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ሰፊ ተቀባይነት እያገኘ መምጣቱ አይካድም።

ከግድቡ ግንባታ ጋር ተያይዞ አንዳንድ የውስጥና የውጭ ኃይሎች ከራሳቸው ርካሽ ፖለቲካዊ አመለካከት መነሻነት ያልሆነ ምናባዊ ስዕል ቀርጸው ለማጣጣል ያደረጉትን ያልተሳካ ሙከራ ከማጋለጥ ትግል አኳያም ዜጎች የዚህ ፕሮጀክት ግንባታ ጉዳይ ፖለቲካዊ ይዘት።

የእድገት እና የትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ይፋ ከሆነ ጀምሮ በከተሞቻችን መልካም የሚባሉ እንቅስቃሴዎችና ተስፋዎቸ እየጎለበቱ መምጣታቸው ይታወቃል። በዚህም የከተማና የኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂውም ልማታዊ ፖለቲካል ኢኮኖሚን በከተሞች ማረጋገጥ እንደሚቻል ከማመልከቱም ባሻገር መንግስት እየተከተለ የሚገኘው ልማታዊ አቅጣጫና በየጊዜው ከኪራይ ሰብሳቢነት ጋር በሚያደርገው ግብግብም በህብረተሰቡ ውስጥ የአመለካከት ለውጥ እንዲታይ በማድረግ ላይ ይገኛል።ይህ ትግል ከቀደመው በበለጠ ተጠናክሮ ከቀጠለ የብዙሃኑ ህዝብ ተጠቃሚነት እየተጠናከረ የከራይ ሰብሳቢዎች መንገድ እየተዘጋ እንደሚሄድ ጥርጥር የለውም።

የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ይፋ ከሆነ ጀምሮ ዜጎች በአዲስ መንፈስ መነሳሳታቸውን በመግለፅ ላይ የሚገኙ ሲሆን ከሚያነሷቸው ጉዳዮች መካከልም መንግስት የያዘው እቅድ ሃገራችን ኢትዮጵያን  የሚለውጥ እና ዜጎቿንም ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን፣ ለልማት የቆረጠ መንግስት ያለመሆኑን መገንዘባቸውን፣ መንግስት ባስቀመጠው የቦንድ ግዢ ለሁለተኛ ጊዜ እንደሚሳተፉ፣ ፕሮጀክቱን ስኬታማ ለማድረግ ከቦንዱ ሽያጭ ባሻገር ሌሎች የገቢ ማሰባሰቢያፕሮግራሞች መዘጋጀት እንዳለባቸውና ሕዝቡምእነዚህን ጥረቶች ለማገዝእንደሚረባረብያለውን የማይናወጥ ቁርጠኝነት እየገለጸይገኛል።

ይሁንና በህዝቡ ውስጥ የሚታየው እንቅስቃሴ ግለቱን ጠብቆ እንዳይሄድ ቀደም ብዬ በጠቃቀስኳቸው ምክንያቶች ፀረ ልማት ሃይሉ "የሃሳብ ማስቀየሻ እና የስልጣን ማራዘሚያ" ዝማሬውን አሁንም እንደቀጠለበት የሚገኝ ሲሆን አብረን እንስራ ለሚለው የመንግስት ጥያቄም ጆሮ ዳባ ልበስ ብለው በየመጽሄት ጋዜጣው እንቅፋት የሆኑ ሃሳቦቻቸውን እና መንግስትንና ገዢውን ፓርቲ ያሳጣሉ ብለው የገመቷቸውን ስንኞች በመደርደር ላይ ይገኛሉ።

እነዚህ ሃይሎች ህጋዊውን እና ህገ ወጡን ተግባር እያጣቀሱ የሚሄዱ ተቃዋሚዎችን ከጎናቸው አሰልፈው እየሰሩ መሆናቸውምግልጽ ነው። ህዝቡን ተስፋ ለማስቆረጥ እና ለማደናገር ይጠቅመናል የሚሉትን አጀንዳ በሙሉ በማራገብ የማደናቀፍ ስራ ሲሰሩ የቆዩና በመስራት ላይ ያሉ ከመሆናቸውም በላይ የአረቡ አለም ነውጥ በሃገራችንም እንዲደገም እናደርጋለን በሚል ሲንቀሳቀሱመቆየታቸው አይዘነጋም።

በአሁኑ ሰዓት ደግሞ ህዝቡ በከፍተኛ ደረጃ መነሳሳቱን በሁለተኛው ዙር የቦንድ ግዢ ባደረገው እንቅስቃሴ ሲመለከቱ በውስጣቸው ከፍተኛ መደናገጥ የተፈጠረ ከመሆኑም በላይ የህዝቡን ማዕበል ለማኮላሸት ዘመቻቸውን ጀምረዋል። ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች እንደተጠበቁ ሆነው በሌላ በኩል ግን ሃገራዊ መግባባቱ በተፈጠረበትና የአብረን እንስራ ጥያቄው ቀድሞውኑ ገና ከመነሻው የተመለሰ ሆኖ ሳለ አዲስ ታይምስ ግድቡን ከፖለቲካ ፍጆታ ጋር ማያያዟ እና ከሃሳብ ማስቀየስ ጋር ማነካካቷ ላም ባልዋለበት አይነት አካሄድ መሆኑን ልትገነዘብ ይገባታል።

ነገር ግን አሁንም በድጋሚ በዚህና ትልቅ ሃገራዊ ፋይዳ ባለው ግድብ ላይ በተለይም ከውጭ ግንኙነቱ አንፃር አዲስ ታይምስ አሁን የያዘችውአቋም ተመችቶኛል በማለት አበቃለሁ።