የአዳማ ከተማ የአትሌቲክስ ቡድን በኦሮሚያ አትሌቲክስ ክለቦች የአቅም መለኪያ ውድድር አሸናፊ ሆነ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 2/2005 (ዋኢማ) - በሻሸመኔ ከተማ ለአምስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው አንደኛው የኦሮሚያ አትሌቲክስ ክለቦች ውድድር እሁድ ህዳር 30/2005 ተጠናቀቀ።

በውድድሩ የአዳማ ከተማ አስተዳደር የአትሌቲክስ ክለብ በሁለቱም ጾታዎች አሸናፊ ሆኗል።

በውድድሩ የኦሮሚያ ውሃ ስራዎች፣ የኦሮሚያ መንገድ ስራዎችና የኦሮሚያ ደንና ዱር አራዊት ድርጅትን ጨምሮ 11 የክልሉ ከተማ መስተዳድሮችተካፍለዋል። ለመጀመሪያ ጊዜ በተከናወነው በዚህ ውድድር ላይ ከቢሾፍቱ፣ ዱከም፣ ሰበታና ጅማ ከተማ መስተዳድሮች በስተቀር ሁሉም የከተማ መስተዳደሮች ተሳትፈዋል። 3ሺህ ሜትርና ከዚያ በታች ባሉ ርቀቶች በተከናወነው በዚህ ውድድር ላይ 451 አትሌቶች ተሳታፊ ሆነዋል።

የአዳማ ከተማ አትሌቲክስ ቡድን በወንድም በሴትም የወርቅ ሜዳሊያዎችን በሙሉ በመውሰድ አሸናፊ ሆኗል።

በሴቶች አዳማ በ160 ነጥብ አሸናፊ ሲሆን ቡራዩ በ85፣ አሰላ በ68 ሁለተኛና ሶስተኛ ሆነዋል። በወንዶችም አዳማ በ155፣ ቡራዩ በ150 እና ኦሮሚያ ደንና ዱር አራዊት ድርጅት በ47 ነጥብ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ያለውን ደረጃ አግኝተዋል።

እንደ ኢሬቴድ ዘገባ  በአጠቃላይ የአዳማ ከተማ መስተዳድር በ315 ነጥብ በከፍተኛ ልዩነት አሸናፊ ሆኗል። ቡራዩ በ185 2ኛ ፣አሰላ ደግሞ በ111 ነጥብ 3ኛ ሆነዋል።

የአምቦና የነቀምቴ ከተማ አትሌቲክስ ክለቦች የፀባይ ዋንጫ ተሸላሚ ሆነዋል። የአቋም መለኪያ ውድድሩ በርካታ ተስፋ የሚጣልባቸውን አትሌቶች አሳይቷል።