ጃፓን ለኢትዮጵያ የምትሰጠው ይፋ የልማት ድጋፍ 110 ሚሊዮን ዶላር ደርሷል

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ህዳር 29/2005(ዋኢማ) - ጃፓን ለኢትዮጵያ የምትሰጠው ይፋ የልማት ድጋፍ ባለፈው ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ 110 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር መድረሱን በኢትዮጵያ የጃፓን ኤምባሲ አስታወቀ፡፡

የጃፓን ዓለም ዓቀፍ ትብብር ኤጀንሲ የበጎ ፈቃደኞች 40ኛ ዓመት በዓል ትናንት አዲስ አበባ ውስጥ በተከበረበት ወቅት ኤምባሲው እንደገለጸው፤ የኢትዮ-ጃፓን የሁለትዮሽ ትብብር ከመቼውም ጊዜ በላይ እየተጠናከረ መጥቷል፡፡

የጃፓን መንግሥት የሚሰጠውን ይፋ የልማት ድጋፍ ፖሊሲ በዚህ ዓመት በማሻሻሉ ጃፓን ለኢትዮጵያ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ትግበራ በተለይም ለምግብ ዋስትናና ለኢንዱስትሪ ልማት የምታደርገውን ድጋፍ ውጤታማ እንደሚያደርገው ገልጿል፡፡

የጃፓን ዓለም ዓቀፍ ትብብር ኤጀንሲ የበጎ ፈቃደኞች 40ኛ ዓመት በዓል ሲከበር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርሃነ ገብረክርስቶስ እንደተናገሩት የኢትዮጵያ ጃፓን የሁለትዮሽ ግንኙነት የተጀመረው እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ1930 ነበር፡፡

በሁለቱ አገራት መካከል የሚደረገው ትብብር በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱንና ጃፓን በኢትዮጵያ ለሚካሄዱ የልማት ተግባራት ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እያደረገች መሆኗን አስታውቀዋል፡፡

በተለይም በመቶዎች የሚቆጠሩ የጃፓን ዓለም ዓቀፍ ትብብር በጎ ፈቃደኞች በንጹህ የመጠጥ ውሃ፣ በትምህርት፣ በጤናና በሌሎችም መስኮች የሚያከናውኗቸው ተግባራት ለትብብሩ መጠናከር አንዱ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በጎ ፈቃደኞቹ በኢትዮጵያ የሚያከናውኗቸው ተጨባጭ ተግባራት የሚደነቁ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ለሁለቱ አገራት የጋራ ጥቅምና ትብብር መጠናከር ጠንካራ መሰረት የሚጥሉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

አምባሳደር ብርሃነ እንዳሉት በኢትዮጵያና በጃፓን መካከል የሚደረገው ትብብር ከፍተኛ ደረጃ ላይ ቢደርስም የንግድ ግንኙነቱ ግን የሚፈለገውን ያህል አይደለም፡፡

ይህን ሁኔታ ለመለወጥ የጃፓን ኩባንያዎች መዋለ ንዋያቸውን በማፍሰስ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በማኑፋክቸሪንግና በንግድ የሚደረገውን ትብብር ማጠናከር ይኖርባቸዋል፡፡

ኢትዮጵያ በመጪው መጋቢት ወር ለምታስተናግደው አምስተኛው የቶኪዮ ዓለም ዓቀፍ ጉባዔ ለአፍሪካ ልማት ብሔራዊ ኮሚቴ ማቋቋሟንና ከጃፓን ኤምባሲ፣ ከአፍሪካ ኅብረትና ከሌሎችም ተቋማት ጋር እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አምባሳደር ብርሃነ በኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ስም ለጃፓን ሕዝብና መንግሥት እንዲሁም በኢትዮጵያ የተሰማሩ ጃፓናውያን በጎ ፈቃደኞች ለሚያደርጉት ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ፉአድ ኢብራሂም በበኩላቸው፤ በአሁኑ ወቅት 50 ያህል ጃፓናውያን በጎ ፈቃደኞች በሳይንስና በሂሳብ ትምህርቶች፣ በጤና፣ በኮምፒዩተር ቴክኖሎጂ፣ በውሃ፣ በግብርና፣ በገጠር ማኅበረሰብ ልማትና በሌሎችም መስኮች አገልግሎት እየሰጡ ናቸው፡፡

በተለይም በጎ ፈቃደኞቹ በሳይንስና በሂሳብ ትምህርቶች ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውንና 13 ያህል በጎ ፈቃደኞች በአማራ፣ በኦሮሚያና በአዲስ አበባ በሚገኙ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሳይንስ ትምህርት አሰጣጥን ጥራት ለማሻሻል ከመምህራን ጋር እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ሂሮዩኪ ኪሺኖ በበኩላቸው፤ በሁለቱ አገራት መካከል እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በኅዳር ወር 1971 ስምምነት ከተፈረመ በኋላ በ1972 ዓ.ም. 25 ያህል የጃፓን በጎ ፈቃደኞች ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን አስታውቀዋል፡፡

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስካሁን 600 ያህል ጃፓናውያን በጎ ፈቃደኞች ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በተለያዩ የልማት ተግባራት ላይ መሰማራታቸውን እንደገለጹ ኢዜአ ዘግቧል፡፡