ለሆቴሎች ፣ ለሎጅዎች ፣ ለሪዞርትና ለፔንሲዮኖች ደረጃ ሊሰጥ ነው

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ህዳር 28/2005(ዋኢማ) - የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ለሆቴሎች፣ ለሎጅዎች፣ ለሪዞርትና ለፔንሲዮኖች በቅርቡ ደረጃ ሊሰጥ መሆኑን አስታወቀ።
ሚኒስቴሩ በሆቴልና ተዛማጅ የአገልግሎት ዘርፎች ለተሰማሩ ድርጅች የደረጃ ምደባ ለማካሄድ ከ2003 አመተ ምህረት ጀምሮ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል።

ከዛ ጊዜ ጀምሮም የሌሎች አገራት ልምዶች ሲፈተሽ፣ ከክልልና ከከተማ አስተዳደሮች አመራሮች ጋር እንዲሁም  ከሆቴል ባለሙያዎችና ባለቤቶችም ጋር  ውይይት ሲደረግበት ቆይቷል።

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሩ አቶ አሚን አብዱልቃድር ለስራው ከፍተኛ ዝግጅት መደረጉን ጠቁመው፤ ስራውን ለሚሰሩ አካላት ስልጠና ከተሰጠ በኋላ ወደ ደረጃ ምደባው ይገባል ብለዋል።

ይህ እስኪሆን ግን ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የክትትልና የቁጥጥር ስራውን እንዲሰሩ የተደረገ ሲሆን፤ ሆቴሎች ጊዜ ይሰጠን በማለታቸው ምክንያትም ስራው መዘግየቱን ይናገራሉ።

መመዘኛውን ለአለም የቱሪዝም ድርጅት እንዲታይና እንዲዳብር ተደርጓል ያሉት ሚኒስትሩ ፥  ድርጅቱም ባለሙያዎችን ልኮ በተለያዩ ክልሎች ቅኝት በማድረግ አስተያየቱን ሰጥቶበታል ነው ያሉት።

የሆቴል ቤት ባለቤቶችና ስራ አስኪያጆች ለደረጃ አሰጣጡ ዝግጁነታቸውን ገልጸው፤ ደረጃ መሰጠቱ በየትኛውም መስፈርት  ጥቅሙ ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል።

ምደባው ራሳቸውን ለማሻሻልና ክፍተቶቻቸውን ለመፈተሽ ይረዳቸዋል ያሉት ባለቤቶቹ፤ ስራው አገልግሎት አሰጣጥን የሚፈትሽ  እንደመሆኑ መጠን በመለካቱ ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግና በሰለጠነ የሰው ሀይል ሊሰራ ይገባል ማለታቸውን እምርታ አስፋው ዘግባለች።