የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ የልዑካን ቡድን ከከፍተኛ የመንግስት አመራር ጋር ተወያዩ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ህዳር 28/2005(ዋኢማ) - በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪና የኢንፎርሜሽንና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በቻይና የሀይናን ግዛት የኮሚኒስት ፓርቲ ምክትል ፀሀፊና የማዕከላዊ ኮሚቴ ተለዋጭ አባል ጋር ውይይት አደረጉ፡፡

የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ ሚኒስትሩ ዶክተር ደብረጽዮን በቻይና የሀይናን ግዛት የኮሚኒስት ፓርቲ ምክትል ፀሃፊና የማዕከላዊ ኮሚቴ ተለዋጭ አባል በሆኑት በሊ ሻንሹንግ የተመራ ሰባት አባላት ያቀፈ የልዑካን ቡድን ከትናንት በስትያ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡
ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን የገለጹት የልዑካን ቡድኑ መሪ የሁለትዮሽ ግንኙነቱ ተጠናክሮ መቀጠል በሚችልበት ሁኔታ ላይ ውይይት አድርገዋል፡፡

ኮሚኒስት ፓርቲው ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በተለይም በኢኮኖሚ ዘርፍ ያለውንና ወደፊት የሚኖረው የጋራ ትብብርና ድጋፍ ስራዎች ያተኮረ የሃሳብ ልውውጥና ምክክር ለማድረግ መምጣታቸውን ገልጸዋል፡፡

ሚስተር ሊ እንዳሉት በኢትዮጵያ እየተመዘገበ ያለው የልማትና ዕድገት ለውጥ በቻይና እየተመዘገበ ካለው ለውጥ ጋር ተመሳሳይነት ያለው መሆኑን ጠቁመው፤ ለውጡን በተሻለ ደረጃ ለማስቀጠል በጋራ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

እየተመዘገበ ያለውን ፈጣን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት በከፍተኛ ደረጃ ለማስቀጠልና ዳር ለማድረስ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር፣ መንግስትና የኢትዮጵያ ህዝቦች የሚያደርጉት ርብርብ እንደሚደግፍ አመልክተዋል፡፡

ለዚህም ሚሰተር ሊ ዛንግ ሹንግ የሁለቱ አገሮችና ፓርቲዎች ወዳጅነትና አጋርነት ይበልጥ እንዲጠናከርና እንዲጎለብት በከፍተኛ አመራር ደረጃ በቻይና የስራ ጉብኝትና የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ ግብዣ አቅርበዋል፡፡

የኮሚኒስት ፓርቲው በ18ኛው ጉባኤው የግምገማ፣ ውሳኔና ቀጣይ አቅጣጫዎችን ማሰለፉንና አዳዲስ አመራሮችን በመሰየም መጠናቀቁን ለሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡

ዶክተር ደብረጽዮን በበኩላቸው፤ የኢህአዴግ እና የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ /ሲፒሲ/ የሁለትዮሽ ግንኙነት በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እንደተጀመረ አስታውሰዋል፡፡

የልዕካን ቡድኑ የኮሚኒስት ፓርቲ 18ኛው ጉባኤ በስኬታማነት መጠናቀቁንና ፓርቲው ባካሄደው የአዳዲስ አመራር ሹመት ውጤታማነት የተሰማቸውን ደስታና እንዲሁም በኢትዮጵያ ለመወያየትና ለመመካከር መምጣታቸውን አመስግነዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት በሁለቱ አገሮች መካከል ለማጎልበት የተፈጠረው ግንኙነት ከማጠናከርም በላይ ቻይና በሌሎች የአፍሪካ አገሮች ያላትን ግንኙነትና ወዳጅነት እንደ መሸጋገሪያ ድልድይና የዲፕሎማሲ አቅም በመሆን እንደሚሰሩም አብራርተዋል፡፡

ከሁለቱ አገራት ፓርቲዎችና መንግስታት ወዳጅነት ግንኙነት በተጨማሪ የቻይና ባለሀብቶችና ኩባንያዎች በስፋት እየተሰማሩ እንደሆነና ይህንንም ለማጠናከር በጋራ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።